Wednesday, 13 May 2020

ስለ የኢሳያስ አፋወርቂዋ ኤርትራ ምን እናውቃለን? ክፍል 2

ከወጋሕታ ብርሃን

ግንቦት 2012

ስለ የኢሳያስ አፋወርቂዋ ኤርትራ በሚመለከት በመጋቢት ወር የመጀመርያ ፅሑፌ በዓይጋ ድህረገፅ (http://aigaforum.com/amharic-article-2020/what-do-you-know-about-isaias-afeworki.htm) አቅርቤ ነበር። ክፍል 2 ይቀጥላል ብዬ የተሰናበትኩኝ ቢሆንም እስካአሁን በተለያዩ ምክንያቶች በመዘግየቴ በመጀመሪያ ይቅርታ እጠይቃለሁ።


ኢሳያስ አፈወርቅ በህይወት መቆየት ብቻ ሳይሆን በስልጣን መቆየትም በጣም የተካነበት ችሎታው ነው። በበረሃው ትግል ወቅት በተጋድሎ ሓርነት ኤርትራ (ጀብሃ) በድብቅ ህዝባዊ ሓይልታት የሚባል ቡዱን ፈጥሮ በለኮሰው እሳት በጣም ደማዊ የሚባል የእርስ በርስ ጦርነት በጀብሃና በህዝባዊ ሓይልታት መካከል ተደርጎ ብዙዎች ህይወታቸው ሲያልፍ እሱ ተርፏል። ከጀብሃ ተገንጥሎ በወጣው ህዝባዊ ሓይልታት በኃላም ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕብያ) በተባለው ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት ኢሳያስ አፈወርቂ ምንም ሳያመነታ ብዙ ብሩህ አእምሮ የነበራቸው ታጋዮችን አስሮና አሰቃይቶ ረሽናቸዋል፡፡ ኢሳያስ እነዚህ ሙሁራን የመንካዕ /የሌሊት ወፍ/ እንቅስቃሴ የሚል ስም በመለጠፍ ድርጅታችን ሊያፈርሱ ሲሉ አከሸፍነው በማለት ዕድሜውን አረዘመ። ቀንና ሌሊት ሲመኘውና የንፁኃሃን ታጋይች ሂወት በከንቱ የፈሰሰበት ስልጣን ያዘ፡፡ ነገርግን ከድርጊቱ አልታቀበም፡፡ የስልጣን ማማው ከተቆናጠጠ በኃላም ማንኛውንም ተቃውሞ ያለምህረትና ያለፍርድ ሂደት ራሱ አሳሪ፣ ፈራጅና ፍርድ አስፈፃሚ በመሆን የብዙ ታጋዮች ሕይወት በየጋራውና ሸንተረሩ አንጠባጥቦ ዕድሜውንና ስልጣኑ አስረዝሟል።

ኢሳያስ ዕድሜውን ለማስረዘም የብዙዎችን ዕድሜ አሳጥሯል። የኤርትራ ህዝብ አሁን የዓለማችን አደጋ ሆኖ ባለው ኮቪድ-19 የልኬት ሁኔታ ኢሳያስ አፈወርቂን ኮቪድ-91 የሚል አዲስ ስያሜ አጎናፅፎታል፡፡ ይህ ሳጓ የኢሳያስ ጨፍጫፊነት፣ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶች እስርቤት ማጎሩ፣ የኤርትራ ኢኮኖሚ እንዲላሽቅ በማድረጉ፣ ኤርትራ ከብዙ አገሮች ተነጥላ የራሱ የኳራንታይን ማእከል በማድረጉ፣ ኤርትራ በርዋን እንድትዘጋና ዜጎችዋ በገዛ አገራቸው ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ ከፀጥታ አካላት የይለፍ ወረቀት ሳይዙ መንቀሳቀስ የማይቹሉበትና የድሮዋ የመንግስቱ ሃይለማርያምዋ ኢትዮጵያን የሚያስታውስ አገር በመፍጠሩ ነው ከኢሱ ወደ ኮቪድ-91 የተሸጋገረው። ኮቪድ-91 በአረቄ የተጠበሰው ፊቱን በሜክ አፕ እያደሰና እየሸፈነ፣ የታመመው ጉበቱን አንዴ ዶሃ፣ አንዴ አቡዳቢ፣ አንዴ ደሞ ጂዳ ሄዶ እየታከመ ይሄው ዕድሜውን አስረዝሟል። የሱ ዕድሜው ረዝሞ የብዙ ኤርትራዊያን ወጣቶች፣ አብሮ አደጎቹ፣ አብረው የታገሉቱና ለኤርትራ ነፃነት በተደረገው ትግል የትጥቅ ትግሉን የመሩ አስሮ በመግደል ዕድሜያቸውን አሳጥሯል።

ኮቪድ-91 ኤርትራ በሪፍረንደም በ1991 እ.አ.አ ነፃነትዋን እንዳወጀች ያለማንም ፍቃድ ወይም ምርጫ ስልጣን እንደያዘ አሁንም የስልጣን ጥሙ እንዳለ ነው፡፡ ስልጣን ወይም ሞት! እንግዲህ ይህ ነገር ሳይሆን አይቀርም ኮ/ል አብይን በቅናት ቅጥል እያደረጋቸው ያለው ጉዳይ። ኮኔሬሉ ኤርትራ፣ ኢሜሬትና ሳውዲ ዓረብያ በሄዱ ቁጥር ምርጫ ሳያደርጉ ስልጣን የያዙትን ፕሬዚዳንትና አሚሮች ሲያዩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ህገመንግስት፣ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ቅብጥርስ … እንዲጠሉና ጥምድ አድርገው እንዲይዙ ያደረጋቸው። ከምን የዋለ ምን ይማራል እንደሚባለው መሆኑ ነው። ኮቪድ-፣1ዱ ኢሳያስ ከአሜሪካው አምባሳደር በኢትየጵያ አምባሳደር ማይክል ቀጥለው የኮ/ል አብይ ኮች ናቸው። ስለ ምርጫ፣ ስለ ዲሞክራሲ፣ ስለብሄር ጥያቄና ስለ ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲ ስርዓት የኤርትራን ጥሩ ተሞክሮ ቀምረው ኮች/እየኮተኮቱ እያስተማሯቸው ነው። ስለ ማሰር እና መግደል እንኳን ኮ/ል አብይ ስልጣን ከመውጣታቸው በፊትም የተካኑት ጥብብ በመሆኑ የኢሳያስ ኮችነት ብዙም አያስፈልጋቸውም።

በአሁኑ ወቅት ኮቪድ-19 በሚድያ ስሙ እንደገነነው ኢሳያስ እንደአሁኑ አያድርገውና ሚድያ በጣም ይወዳ ነበር። ጋዜጠኛ እስከሚመስሉ ድረስ በERTV ስክሪን ላይ ከጥዋት እስከ ማታ ይታዩ ነበር። ነገርግን እሳቸው በማይቆጣጠሩት ሚድያ መቅረብ በጭራሽ አይወዱም። በስህተት/በአጋጣሚ ከውጭ ሚድያ ጋር ቃለመጠይቅ ካደረጉ ደግሞ ተቆጥተው፣ አላቅም እና እንጃላቹህ ብለው አክሩፎውና አስኮርፈው ቃለመጠየቁ ያልቃል። በአገር ቤትም ሚድያ የሚቀርቡት ብዙውን ጊዜ ከአንድ ጋዜጠኛ ቢበዛ ደግሞ ከሁለት ጋዜጠኞች ነው። ጋዜጠኞቹ የራሳቸው ጥያቄ ማቅረብ አይችሉም። በጭራሽ አይፈቀድላቸውም። እነሱም አይደፍሩም። ኢሳያስ በአረብኛ እና በእንግሊዝኛ ጥሩ ችሎታ ቢኖራቸውም የውጭ ሚድያዎች የቀረቡት ግዚያት በጣት የሚቆጠሩ ግዝያት ናቸው። እንደ ኮ/ል አብይ የእንግሊዝኛ ችግር ባይኖራቸውም ለውጭ ሚድያ የማይቀርቡት ጥያቄዎቻቸውን በመፍራት ነው። ጥያቄውንም የሚፈሩት የኤርትራን ህዝብ ጥያቄ በውጭ ጋዜጠኛ ተጠይቀው ተገደው ሲመልሱ ሰምቶ ህዝቡ እንዳይታዘባቸው ነው። ኢሳያስ አፈወርቅ ሚድያ በመጠቀም ህዝቡ ምን ማሰብ እንዳለበት ወስነው ይንቀሳቀሳሉ። ከሳቸው ቁጥጥር ውጭ የሆነ ሚድያ እንዳይከታተል ይጥራሉ። ዲሽ የሚባል ቴክኖሎጂ እና ኢንተርኔት የሚባል ቴክኖሎጂ ጠላቶቻቸው ናቸው። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በኤርትራ ውስጥ አንዳይስፋፉ በተለያየ መንገድ ይዋጉታል። የራሳቸው የሆነ ዲጂታል ሰራዊት በመፍጠር በዓለም የሳቸውን ስም አንስቶ የሚተችና የሚቃወም ወያነና አጋሜ ብለው ታርጋ ያስለጥፋሉ በብዙ አቅጣጫ ተቃውሞ እንደሚመጣው አስመስለው ይገጥሙታል።

ኢሱ በስልጣን ዕድሜያቸው ቀልድ የለም። የግል/ ነፃ ጋዜጣ የሚባል የለም። ስለዚህ ያልተቆጣጠሩት ነገር በህዝቡ አንጎል እየተሸራሸረ ከሆነ 03 (ባዶ ሦስት) የሚባል የፈጠራ ወሬ የሚበትን አካል አላቸው በዛ የፈለጉትን አስተስሰብ ያሰራጫሉ። በባዶ ሦስት ተስፋ ይፈጥራሉ፣ ተስፋ ያስቆርጣሉ፣ የፈለጉትን አስተሳሰብ በህዝቡ በመበተን ውዥንብር ፈጥረው ሲያበቁ እሳቸው ከርመው ከራርመው በሚድያ ህዝቡ በጉጉት ከሳቸው መልስ እንዲጠብቅ አድርገው የፈለጉትን ሃሳብ ትክክል ነው ብለው ያልፈለጉትን የጠላት፣ የወያኔ ወይ የሲ.አይ.ኤ ወሬ ብለው ይሰብካሉ። በዚህም ዕድሚያቸውን ያስረዝማሉ

ኢሳያስ የሚያደርጉት ሁሉ የስልጣን ዕድሜያቸውን ለማረዘም ነው። የስለላ መዋቅራቸው ሌላ ስራ የለውም። በአገር ውስጥ ለመደራጀት የተከለከሉ ተቃዋሚዎችን በያሉበት አድፍጠው ይከታተላሉ። አውሮፓና አሜሪካ ያሉትን አንዳንዱን በመርዝ ይገድላሉ። በኢትዮጵያና በሱዳን ያሉትን ቅጥረኞችን በማሰማራት አግተው ይወስዳሉ። ማገት ሳይችሉ ሲቀሩ ደግሞ በማንአለብኝነት በሰው ሃገር ይገድላሉ። አዲስ አበባ፣ ደሴ እና ሁመራ የገደሏቸውን ማስታወስ ብቻ ይበቃል።

ሁሉም ኤርትራዊ ከኢሳያስ የሚያመልጥ የለም ብሎ እንዲያስብ የሚያደርግ አላማ ይዘው ይፈፅሙታል። ይህን ጀብዳቸው በዜና አይነገርም ግን በዜሮ ሦስት የወሬ ማሽናቸው ሁሉም እንዲያቀው ይደረጋል። ኢህአዴግ ስል በምርጫ ፍርድቤት መስርቶ የደርግ ባለስልጣኖች በህግ እንዲጠየቁ ሲያደርግ ኮ/ል መንግስቱንም በሌለበት ሲከስ ኢሳያስ ግን ኮ/ል መንግስቱን ለመግደል ዙምባቤ ድረስ ገዳዮችን አሰማርቶ ነበር፡፡ አልቀናውም ከሽፎበታል። ቢሳካ ግን ምን ለማግኘት አስቦ ነው ለጥናት በዕቅዱ መሰረት ለመፈፀም በመቶ ሺ ዶላር ወጪ ያደረገው? ብንል ኢሳያስ አይተኛም ከማድረግ ወደ ኃላ አይልም የሚል የስነልቦና ጫና በኤርትራ ህዝብ በመፍጠር ለለውጥ እንዳይንቀሳቀስ ለማድረግ ነበር።

በአሁኑ ወቅት የኢሳያስ የስለላ መዋቅር “ኦፕረሽን ትንሳኤ ኤርትራ“ በሚል ኮ/ል አብይ በሰጣቸው ዕድል በኢትዮጵያ ሦስት ተልእኮ ይዞ ተሰማርቷል።


1) ትግራይን ማዕከል ያደረገ እና የትግራይ አስተዳዳሪ የሆኑት ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ላይ ያነጣጠረ ዝርዝር ጥናት በማድረግ ላይ ያነጣጠረ ስለላ እያደረገ ነው።


2) ከኤርትራ ጠፍተውና ኮብልለው የመጡትንና በተለይ ደግሞ በትግራይና በአዲስ አበባ የሚገኙ ስደተኞች እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ሰርጎቦችን አስገብቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።


3) ከአሜሪካ ኤምባሲ ቀጥሎ ብዙ ስታፍ ያለው ኤምባሲ በመሃል አዲስ አበባ አደራጅታል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ’ድብቅ’ ቤቶች በመከራየትና ምንጩ በማይታወቅ ገንዘብም መጠነ ሰፊ የቤት ግዥ በመፈጸም በአገራችን ህልውናና ሉዓላዊነት እንዳሻው እየፈነጨበት ነው። ከሁሉም በላይ አሳሳቢ የሚሆነው እነዚህ የኢሳያስ ሰላዮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮና የኢትዮጵያ ደህንነት ቢሮ በር ክፍት ተደርጎላቸው በጋራ ተቆራኝተው ከሚሰሩት በተጨማሪ ለብቻቸውም የሚሰሩት ምስጥራዊ ስራ ነው።

የኤርትራ ሰራዊት ከደርግ ጋር ለነፃነት በተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ተሞክሮ የነበረው ሰራዊት ነበር። ይህ ሰራዊት በኢሳያስ አያያዝ ምክንያት ከአገር ሰራዊትነት ወደ ኢሳያስ ሰራዊትነት ተቀይሯል። ኢሳያስ በእብሪተኝነት ከኢትይጵያ ጋር ጦርነት በመክፈቱ ሰራዊቱ ኩፍኛ እንዲመታና እንዲዳከም ምክንያት ሆኗል። ብዙ ተሞክሮ ያላቸው የሰራዊቱ አመራርና አባላት ህይወታቸው እንዲያልፍና አካላቸው እንዲጎድል ሁኗል። ኤርትራ በእያንዳንዱ ቤት የሚያንካካ ሃዘን በኢሳያስ ጠብ አጫሪነት በተከፈተው ጦርነት ተከስቷል። አሁን ያ አርበኛ ኤርትራዊ ሰራዊት የኢሳያስ ዕድሜ ማራዘሚያ በመሆን ደረጃው ዝቅ ብሎ በየቀኑ በመቶዎች ወደ ሱዳንና ኢትዮጵያ መኮብለሉ ተያይዞታል፡፡

ኢሳያስ አፈወርቅ ያዳከመው ሰራዊት ስንት እግረኛ ክፍለ ጦሮች አሉት? ስንት ሜካናይዝድ ክፍለ ጦሮች አሉት? ስንት ሚሊሻ ክፍለ ጦሮች አሉት? የነዚህ ኃይሎች የሰው ኃይል ብቃትና ሞራል ምን ይመስላል? የትጥቅ ሁኔታውና ብቃት ምን ይመስላል? በዚህ አቅም ምን የማድረግ ችሎታ አለው? የሚሉትን በማየት ኮቪድ-91 የኤርትራ ሰራዊት ከየት-ወዴት እንዳደረሰው በአጭሩ እንቃኛለን።

ኤርትራ 23 መደበኛ እግረኛ ክ/ጦሮች ሲኖራት 2 ኮማንዶ ክ/ጦሮች አሏት። 4 ታንክ መድፍና አየር መቃወሚያ የታጠቁ ሜካናይዝድ ክ/ጦሮች አሏት። 9 የሚሊሻ ክ/ጦሮች በየአካባቢያቸው የሚንቀሳቀሱና ሲያስፈልግ በየአካባቢው በሚገኙ የግምባር ምሽግች የሚሰለፉ ናቸው። ሚሊሻ ክ/ጦሮቹ ልምድ ባላቸው የመደበኛው ሰራዊት አዛዦች ይመራሉ። የሚሊሻ ኃይሉ ብዙ የሚኮበልል ስላልሆነ የሰው ብዛቱ ከተቀመጠለት ስታንዳርድ ሲንፃፀር ደህና በሚባል ደረጃ ይገኛል። የዚህ ኃይል ዋናው ችግር ሦስት አረተኛው ዕድሜው ለውትድርና ብቁ አለመሆኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ምንም የመዋጋት ፍላጎት የሌለውና ያለፍላጎቱ የተደራጀ ነው። በአካባቢው ከቤተሰቡ ሳይርቅ የተደራጀ መሆኑ ብቻ እንደ ተሻለ አማራጭ አይቶ ጊዜ ያልፋል ብሎ አድብቶ የሚጠብቅ ነው።

መደበኛና እግረኛ ክ/ጦሮቹ ተራ ተዋጊ የሌላቸው ቆፎዎች ናቸው። ተዋጊ የሰው ኃይል ብቻ ሳይሆን ታችኛው መዋቅር ጋድ/መስርዕ/ እና የመቶ /ጋንታ/ የሌላቸው በሻምበል /ሐይሊ/ ደረጃ አራት አምስት ሰው ያላቸው ናቸው። በየዙሩ ሳዋ የሰለጠኑ (በደርግ ጊዜ ብሄራዊ ውትድርና እንደሚባለው በአስገዳጅ የተሰለፉ ናቸው/ በመሆናቸው በነዚህ ክ/ጦሮች ቢመደቡም ብዙ ሳይቆዩ ወደ ጎረቤት አገር የሚኮበልሉና ወደየቤታቸው ጠፍተውም ተደንቆው የሚቆዩ እና የኢሳያስ መንግስት በየጊዜው ፍተሻ በማድረግ የሚያሳድዳቸውና በየክ/ጦሮቹ እስርቤት ታስረው ለአስገዳጅ ስራ የሚሰማሩ ናቸው። ሁለቱ ኮማንዶ ክ/ጦሮች የተሻለ የሰው ኃይል ያላቸው ቢሆንም በጋድ ሁለት ተራ ተዋጊዎች ያላቸውና በየመቶውም ስድስት ተራ ተዋጊ ያላቸው ናቸው። የተሻለ ስልጠናና ደሞዝ አላቸው። ከነዚህም የሚኮበልል በተመሳሳይ ብዙ ነው። እነዚህ በጋድና በመቶ ተራ ተዋጊ የሚኖራቸው የሳዋ ዙር ምደባ ላይ በብዛት ቅድሚያ ሰለሚሰጣቸው ነው። ከስታዳርድ አንፃር የመቶ ሳላሳ ሰው ይኖረዋል ከሚለው አንፃር ሲታይ የተሟላ አይደሉም።

ሜካናይዝድ ክ/ጦሮች በብዱን የምትታጠቀው መሳርያ በመሆኑ የታጠቁት ለምሳሌ አንድ ታንክ ከአምስት እስከ ሰባት ሰው የሚስፈልገው ሲሆን ብዙ ታንኮች ይህን ያህል የሰው ምድብተኛ ስሌላቸው የተሟላ ክሪው የለንም በሚል ታሽገው የተቀመጡ ታንኮች፣ መድፎችና የአየር መቃወሚያዎች ብዙ ናቸው።


በአጠቃላይ ሰራዊቱ ስልጠና ጥሩ የሚሰለጥኑ ቢሆንም ሰልጥነው ስለሚኮበሉሉ አሁን አሁን ልምድ ያለው የሰራዊት አባላት በተራ ተዋጊ ብቻ ሳይሆን በታችኛው አመራርም የለም። ከሁሉም በላይ ዋናው ችግር የሰራዊቱ አገባላት በኢሳያስ ስርዓት ምንም እምነት የላቸውም። ሰላም የናፈቀው ሰራዊት ነው። ያለፍላጎቱ መጨረሻ ለሌለው ጊዜ በምሽግና ፍትሓዊ ባልሆነ ጦርነት መሰለፍ ሰልችቶታል። ሰራዊቱ በተለይም በኢትዮጵያና በኤርትራ ሰላም መጣ ብሎ ተስፋ አድርጎ የነበረው ያህል ኢሳያስ ምክንያቱ በማይታወቅ ውሳኔ ድንበሩ በመዝጋቱ በዛው ልክ ተስፋው ጨልሞበታል። ኢሳያስ እያለ በኤርትራ ሰላም የለም ብሎ እንዲደመድም አድርጎታል።

ኢሳያስ በዚህ በቃኘነው ኃይልና በደርግ ጊዜ በነበረ ትጥቅ በታጠቀ ኃይል ምን ሊያደርግ ይችላል? ሊያስፈራራ ይችላል። ውስጣዊ አቅሙን ለማያውቅም ሊያስደነግጥ ይችላል። ይህም ሆኖ ግን ምንም አያደርግም ማለት አይደለም። አደራጃጀቱን በመጠኑ አስተካክሎና ኃይል አግኝቶ የተወሰኑ ክ/ጦሮቹን በድንገት አዘጋጅቶና ድንገተኝነትን ተጠቅሞ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገሮች ጥቃትና ችግር ሊፈጥር ይችላል። ይህ ሲባል ግን ለረዥም ጊዜ ጦርነት የማድረግ አቅም አለው ማለት አይደለም። ሰለዚህ ኢሳያስ አደጋ /risk/ ያለው እርምጃ መሆኑ አውቆ ከሌሎች መሪዎች ትብብር ይፈልጋል። አገር ለመሸጥ ወደኃላ ከማይሉት እንደነ ኮ/ል አብይ አህመድ እና ደመቀ መኮነን የመሳሳሉት ወያኔን ለማዳከም ይረዳናል ብለው አስበው ሊተባበሩት ይችላሉ። ለነሱም አደጋ ቢኖረውም የነገ አደጋ ማየት ተስናቸው እንደበሬው ሳሩን ብቻ ሊያዩ ይች

ኢሳያስ ይህን ሁሉ እላይ የቃኘነው ኃይል የገነባው ተጨባጭ ስጋት ስላለው አይደለም። ኢሳያስ የስልጣን እድሜውን ለማስረዘም ወጣቱ የሚያስርበት ዘዴ ነው። የአስመራ ዩኒቨርስቲን ዘግቶ ከአስራ አንደኛ ክፍል በኃላ ትምህርት በጦር ሰራዊት ስር እንዲሆን አድርጎ የተማረ የማይከበርባትና ብሎም የሌለባት ኤርትራ ፈጥሯል። ኢሳያስ ከሱ የተለየ አቋም ያለው ብቻ አይደለም የሚጠላው ኢሳያስ የማያቀው ዕውቀት ያለውን ሁሉም ሙሁር አይወድም። ይህ ደግሞ በትግል ሜዳ እያለም በሙሁራን ላይ የነበረው የፀና አቋሙ ነው። ለአብነት ያህል ኤርትራ ነፃነትዋን እንደተቀዳጀች አንዱ የጦር መሪ አዲስ አበባ ደርሶ ሲመለስ ኢሳያስን እንዲህ ብሎ ይጠይቀዋል። ወያኔ ታጋዮችዋን ነባሮቹን የጦር አዛዦች ት/ቤት ከፍታ እያስተማረች ነው። እኛንም እንድንማር ለምን አታደርግም? ብሎ ሲጠይቀው ኢሳያስም እናንተን ማን ነው የሚያስተምራቹሁ? እናንተ የማታቁት ምን አለና? ብሎ በጥያቄ ሲመልስለት ዝም አለ አሉ ጠያቂው። ተጠያቂውም ባይሆን እንግሊዝኛ ውጭ ሄዳቹሁ ትማራላቹሁ ብሎ ጥያቄውን መለሰለት። በኢሳያስ አመለካከት ማንም ውርጋጥ ማስተርስ አለኝ ብሎ የሱን ጀነራሎች ማስተማር ማለት ውርደት ነው። እሱም ከማንም ምክርም ትምህርትም ያስፈልገኛል ብሎ አያምንም። በቃለመጠይቅ ወቅት ስለሁሉም ነገርና ስለ ዓለምአቀፍ ጉዳዮች የሚዘባርቀው ከዚህ በሽተኛ አስተሳሰቡ በመነሳት ነው።

ከትግሉ ወቅት ጀሚሮ የነበረና የተለመደ ቢሆንም ከቅርብ ግዝያት ጀምሮ እንደአዲስ ኢሳያስ ራሱን በመደበቅ ታሟል። ሞቷል። ታስራል። ሲባል ደስ ይለዋል። እሱ ባለመኖሩ ህዝቡ እንደማይጨነቅ ቢያቅም ምንም ማድረግ የሚችል ሰው የለም ብሎ ለማስፈራራት ይጠቀምበታል። ብሞትም ገና እገዛችሀለሁ ዓይነት ሙድ ነው። ሰሞኑ ይህ ከድሮ ጀምሮ የተጠናወቶው ተግባር ተፈፅሟል። ታሟል፣ ታስራል፣ ሞቷል፣ ተባለለት፡፡ ነግር ግን ይህ ወሬ በሰፊው በሚወራበት ወቅት የተወራና የተፈፀመ ነገር ነበር። ኮ/ል አብይ በቻርተር አውሮፕላን ምፅዋ ድርስ ሄደው ነበር። የሄዱበት ምክንያት ብዙ ተቀባይነት ሳያገኝላቸው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ። በዛው ሌሊት የኤርትራ ጦር በሁሉም ግንባር ምሽግ እንዲገባ ተደረገ። በኢትዮጵያ በኩልም ጨቅላው የጦር አዛዥ ነኝ ባዩም የኢትዮጵያ ሰራዊትም ምሽግ እንዲገባ አዘዙትና ገባ። የሁለቱም አገር ሰራዊቶች ምሽግ መግባታቸው የተረጋገጠ ሐቅ ነው። አብይ መሄዳቸው ምንም የተገለፀ ነገር የለም። ከሶሻል ሚድያ ውጭ። ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ አሉ የሉም ሲጫወቱ የቆዩት የሰሜኑ ኮርያ ኪም ኡን የሜይደይ በዓልን ለማክብር ታዩ ሲባል ኢሳያስም ከስትሮክ ነቅተው አስመራ ሳይታዩ ኢትዮጵያ ሄዱ ተባሉ። ኢትዮጵያም በሶሻል ሚድያ መጡ አለመጡም እየተባለ ጨቅላው በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎችና በማህበራዊ ሚዲያ አጋፋሪዎቹ የልጆች ጫወታ የሚመስል ተውኔት ተተወነ።

ይህ ሁሉ ምንድነው? ለምንድነው? ኢሳያስ ሊቆጣጠሩት ያልቻሉት ስትሮክ የደህንነታቸውንና የሰራዊታቸውን ምሽግ አልፎ አጠቃቸው። እሳቸውም የሞትን ዳርቻ አይተው በመቐለ ጎደና ሳልንሸራሸርማ ጠቅልዬ ለመሄድ አልተዘጋጀሁም ብለው ለወሰዳቸው ቅድስ አምላክ ይሁን ዲያብሎስ ተማፅነው ለአጭር ጊዜ ተመልሰዋል። የኮ/ል አብይ የሰሙኑ የጦር አዋጅ አጣዳፊነትም ከዚህ የሚመነጭ ይሆናል። የ’ቀን ጅቦች’ን መልክ አስይዞ የብልፅና አሰተዳዳሪው ኮ/ል ነብዩ ስሑል ሚኬኤል በራስ አሉላ አባነጋ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፍያ አቀባበል ለአቶ ኢሳያስ አድርጎ ኢሳያስም የመቐለ ጎደናዎችን እንደተመኙት ተንሸራሽረው ዳርቻውን አይተው ሕ.ወ.ሓ.ት. የሰራችው የሚመረቅ የልማት ስራ ካለም መርቀው ተማፅነው ከወደ ተመለሱበት ለመሄድ እየተጣደፉ ይሆናል።

ኢሳያስ ለብዙ ዓመታት የኤርትራ ጠላት ወያኔ፣ አሜሪካ፣ እና ሌሎች ጎረቤት አገሮች እንደሆነ ሲሰብክ ቢቆይም ህዝቡ ራሱ ኢሳያስ መሆኑ ከተረዳ ቆይታል። የኤርትራ ህዝብ ኢሳያስ ይሙትም ይኑርም የኢሳያስን ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስወገድ የጀመረው ትግል አቀጣጥሎታል።

ዳግም ትንሳኤ ለኤርትራ ነፃነት በሚል መፈክር ለሳላሳ ዓመታት የታገለ ህዝብ ከኢሳያስ ጭቆና ተላቆ ለውጥ የሚያረጋግጥበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ብሎ በውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኤርትራዊያን ‘ይኣክል’ (ይበቃል) ብለው እየታገሉ ነው። የኤርትራ ህዝብ በለውጥ ስም ነፃነቱ ወደ የውጭ ጣልቃ ገብነት ወይ ቀጥተኛ ወደአልሆነ አዲስ ቅኝ ግዛትም እንዲገባ ፍቃደኛ አይደለም። የተበተነች ኤርትራ እንድትሆንም ፍፁም ፍቃደኛ እንዳልሆነ በተለያዩ ሚድያዎች እየገለፀ ነው። ህዝብ ያልተሳተፈበት ለውጥ ከኢሳያስ ስርዓት በኃላም አይፈልግም። በህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ መንግስት ለማቋቋም የኤርትራ ህዝብ ብቃትም ንቃትም ያለው ህዝብ ነው። የማንም ሞግዚትም አይፈልግም። የኢሳያስን ሌጋሲ ለመጠበቅ የሚሞክር ኃይል የሚሸከም ዓቅምም ትዕግስትም የለውም። ከኢሳያስ አፈወርቅ ስርዓት ነፃ የሚሆንበት ጊዜ ናፍቃል፡፡ ጊዜውም ተቃርቧል።

የኢሳያስ አፋወርቂዋ ኤርትራ በኮቪዲ-91 የመጨረሻ ምዕራፍ በኔ ኢንፎርመሽንና ትንታኔ ይህን ትመስላላች።

ሁለቱም ክፍሎች በትዕግስት ስለአነበባችሁት አመሰግናለሁ። አስተያየታቹሁ፣ ደግፋችሁም ተቃውማቹሁም በዓይጋ ፎርም በኩል ብትፅፉ ይጠቅማል። እንወያይበትለን፡፡

ራሳችሁን ከኮቪዲ-19 እና ከኮቪዲ-91 ጠብቁ!

(ምንጭ : www.aigaforum.com )