Sunday 12 January 2020

ቀጣዩ ምርጫ፤ ስለትላንት ሙሾ በሚያወርዱ እና ዛሬ ላይ ሆነው ስለነገ ራዕይ ባላቸው መካከል ነው

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ

ሰበብህን ቆጥበው፤ ጊዜ የማግኘት ጉዳይ ሳይሆን፤ ጊዜ የመስጠት ጉዳይ ነው፤ ላንተ በጣም አስፈላጊ ከሆነ፤ ጊዜ ስጥ”።     ያልታወቀ ሰው ከተናገረው የተወሰደ፡፡



በሃገራችን የፖለቲካ ጉዳይ፤ በተለይም ኢሕአዲግ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ፤ ምርጫ አወዛጋቢ ያልሆነበት ጊዜ የለም፡፡ ኢሕአዲግ፤ በጉልበቱ የሽግግር መንግሥት አቋቁሞ፤ እራሱን ያፀደቀውን ቻርተር ጥሶ፤ ጊዜውን ካራዘመ በኋላ፤ ሃገራችን ውስጥ “ቋሚ የሆነ መንግሥት” ይመሰርት ዘንድ፤ በግንቦት 1987 ዓም ነበር የመጀመርያው “ሃገራዊ ምርጫ” የተካሄደው፡፡ ይህ ምርጫ ከመደረጉም በፊት ሆነ ከተደረገ በኋላ ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሳ ከመሆኑም በላይ፤ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፈው ሃይል፤ ሜዳውን ሙሉ ለሙሉ ለገዥው ፓርቲ ትቶ፤ ገዥው ፓርቲ፤ ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው መንግስት ተቋቋመ፡፡



ከሌሎች የምርጫ ጊዜዎች፤ የ1987ቱን ምርጫ የተለየ የሚያደርገው፤ ለዚህ ምርጫ ምዕራባውያን ትኩረት ሰጥተውት፤ ተቃዋሚው በምርጫ ሊሳተፍ የሚችልበትን መንገድ ለማመቻቸት ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት ነበር፡፡ የአሜሪካን መንግስት፤ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት፤ በየካቲት 1987 ዓም፤ የፕሬዝዳንቱ የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪ የነበሩት፤ አንቶኒ ሌክ የመሩት ቡድን፤ ከገዥው ፓርቲ እና ከተለያዩ የተቃዋሚ ሃይሎች ጋር በኋይት ሃውስ፤ ያደረጉት በርካታ ውይይቶች፤ የጥረቱ ምሳሌ ሆኖ ይጠቀሳል። ለዚህ የኢትዮጵያ ምርጫ፤ ምእራብውያኑ ትኩረት ሰጥተው በገዥው ፓርቲ ላይ ያደረጉት ግፊት፤ አንዳንድ ተቃዋሚ ጎራ ውስጥ የነበሩ “የፖለቲካ ልሂቃን” የተሳሳተ የፖለቲካ ስሌት በማድረግ፤ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ በመድረሳቸውም፤ ምዕራብውያኑ፤ ከሚገባው በላይ በገዥው ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ጫና አድርገው፤ ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ምህዳሩን ይበረግዳል ብለው ገመቱ። በዚህም የተነሳ፤ ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ ይመሩት ከነበረው የፖለቲካ ድርጅት በስተቀር፤ ሁሉም በሚባል መልኩ፤ ገዥው ፓርቲ የምርጫ ጊዜውን ካላራዘመ እና የምርጫ ቦርዱን ካልቀየረ በስተቀር በምርጫው አንገባም ሲሉ ደመደሙ። ዶ/ር በየነም፤ በተቃዋሚው ጎራ በተደረገባቸው ከፍተኛ ጫና፤ ወደ ምርጫው ለመግባት የወሰኑትን ውሳኔ፤ በመከለስ፤ የግንቦት 1987 ምርጫ ላይ እንደማይሳተፉ ገለፁ።

ይህ በተቃዋሚው ጎራ፤ የተወሰደው የተሳሳተ ውሳኔ፤ የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት ይልቅ በማጥበቡ፤ ሃገራችንን፤ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል። ይህ ፀሃፍ፤ በወቅቱ፤ በዋሽንግተን ዲሲ ይተላለፍ የነበረው የሕብረት ሬድዮ አዘጋጅ እና አቅራቢ ከነበሩት አንዱ ነበር። የዚህ ሬድዮ ዝግጅት የፈጠረለትን አጋጣሚም ተጠቅሞ፤ በተቃዋሚ ጎራ የነበረው የፖለቲካ ሃይል ወደ ምርጫው እንዲገባ ከፍተኛ ግፊት አድርጓል። ለኦነግ፤ ለኢድኃቅ፤ ለመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት፤ ለአማራጭ ሃይሎች፤ እንዲሁም በወቅቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር በአሜሪካ ለነበሩት ለአምባሳደር ብርሃኔ ገብረክርስቶስ፤ ቃለ መጠይቅ በማድረግ እና፤ መንግስትና ተቃዋሚው፤ ስምምነት ፈጥረው፤ ምርጫው ሁሉን አሳታፊ እንዲያደርግም፤ በቃለ መጠይቆቹ ሞግቷል። ሆኖም፤ በተቃዋሚው እምቢተኝነት፤ እና ያለምንም እስትራተጂ በተወሰደ እርምጃ፤ ተቃዋሚው፤ በአለም መድረክ ላይ የነበረውን ተደማጭነት አጣ። ምዕራብውያኑም፤ ተቃዋሚው ሰበብ ፈላጊ እንጂ፤ የተፈጠረለትን አጋጣሚ ተጠቅሞ፤ በትግሉ፤ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ተግቶ ለመታገል የቆረጠ አይደለም ሲሉ ደመደሙ።



ምንም እንኳን የተቃዋሚው ሃይል፤ ሕዝቡ በ1987ቱ ምርጫ ባለመሳተፍ ገዥው ፓርቲ፤ መንግሥት የመሆነ “ሕጋዊነት” (legitimacy) እንዳይኖረው በምርጫው ላይ ማዕቀብ እንዲደረግ ቢሞክርም፤ ሕዝቡ በምርጫው ተሳተፈ፡፡ ከዛም በላይ፤ በርካታ ግለሰቦች፤ “በግል ተወዳዳሪነት” ገዥውን ፓርቲ ተቃውመው በምርጫው በመሳተፍ፤ ገዥው ፓርቲ ብቻውን መንግሥትን እንዲቆጣጠር እና፤ መንግሥትም ምርጫው “ፍትሃዊ እና ነፃ” ነው እንዲል አደረጉት። የሚያሳዝነው፤ የተቃዋሚው ሃይል፤ በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀስ፤ ሁኔታዎችን ለመምራት፤ የረጅም እና የአጭር ጊዜ ዓላማና ግቡን ነድፎ የማይንቀሳቀስ፤ ለሚፈጠሩ ነገሮች ምላሽ በመስጠት (react) የተጠመደ በመሆኑ፤ ትግሉን በቅጡ ሊመራ አልቻለም። ይህ ፀሃፍ፤ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር፤ ኢሕአፓ በሳንዲያጎ አዘጋጅቶት ለነበረው ስብሰባ “lack of strategic planning, the deficiency in the Ethiopian opposition camp” የሚል ሰፊ ሃተታ ያለው ጽሁፍ በማቅረብ፤ ገና ከጅምሩ፤ ተቃዋሚው የአጭር እና የረጅም ጊዜ አላማና ግብ፤ እንዲሁም የሚጓዝበትን መንገድ እንዲነድፍ፤ የምክር ሃሳብ አቅርቦ ነበር። ሆኖም እስከ መጨረሻው ያይነው ነገር፤ ተቃዋሚው በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ነው። በዚህም ምክንያት ነው “አንጋፋ የነበሩት”፡ እንደ ኢድኃቅ አይነት እና መድህን የተባሉት ድርጅቶች፤ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ሊከስሙ የቻሉት።



በዚህ ፀሃፍ እምነት፤ የተቃዋሚው ጎራ ትልቁ ችግር፤ ከስህተቱ ለመማር ፈቃደኛ ያልሆነ መሆኑ ነው። ከ1987ቱ ምርጫ ምንም ዓይነት ትምህርት ያልወሰደው የተቃዋሚ ሃይል፤ ለግንቦት 1992ቱ ምርጫም የማይሳተፍ መሆኑን፤ በአደባባይ አወጀ፡፡ በምርጫ ለመሳተፍ ያንገራግሩ የነበሩ፤ ሃገር ውስጥ የነበሩ ድርጅቶችም ላይ የወከባ ዘመቻ ተጀመረ፡፡ ምርጫ ውስጥ መሳተፍ እንደ ክህደትም ተቆጠረ፡፡ አንዳንዶቻችን፤ የምርጫው ሜዳ፤ ለገዥው ፓርቲ መተው የለበትም ብለን በማመናችን፤ በተለይም በግል እንወዳደራለን ብለው ዝግጅት ያደርጉ የነበሩ ሰዎችን በአንድ አጀንዳ ስር በማስተባበር፤ በየምርጫ ጣባያው የሚኖረው ውድድር፤ አንድ የኢሕአዲግ ተወዳዳሪ፤ ከአንድ ተቃዋሚ ጋር ሊወዳደር የሚችልበትን፤ መድረክ ለማዘጋጀት፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አንጋፋ ሚና ካላቸው ሰዎችም ጋር ውይይት ተደረገ። ይህ ሁኔታ በውይይት እና በጥናት ደረጃ ላይ በነበረበት ጊዜም፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት በመጀመሩ፤ ለተጀመረው ንድፈ ሃሳብ እንቅፋት ሆነ። በዚህ ውስብስብ ጊዜም ነበር፤ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢዴፓ) የተባለ፤ በአቶ ልደቱ አያሌው የተመራ ድርጅት ገና ብቅ ከማለቱ፤ በግንቦት 1992ቱ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያበሰረው፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ጥሩ ዜና ነበር፡፡ ኢዴፓን ተከትሎ፤ ሌሎች በሃገር ውስጥ የነበሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች በምርጫው ተሳተፉ፤ በምርጫ 1992ም ተቃዋሚው ጎራ ገዥውን ፓርቲ ምጥ አስያዘው፡፡



በምርጫ 1992፤ ተቃዋሚው ባደረገው የምርጫ ተሳትፎ ምክንያት፤ የፌደራል ምክር ቤትም ውስጥ ሆነ በአንዳንድ የከተማ እና ክልል ምክር ቤቶች መቀመጫ ለማሸነፍ በመቻሉ፤ በየምክር ቤቶቹ ስብሰባዎች፤ ገዥውን ፓርቲ በመሞገት እና፤ የፖሊሲዎቹን ድክመት እና አደገኛነት በማጋለጥ፤ ለፖለቲካው ሂደት ያበረከቱት አስተዋጽኦ የሚናቅ አልነበረም። ተቃዋሚው ይህንን ያገኘውን ድል በማስፋት፤ የሕብረተሰቡን ልብ በማሸነፍ፤ ገዥውን ፓርቲ በራሱ የፖለቲካ ቁማር ከጨዋታ ውጪ ከማድረግ ይልቅ፤ እርስ በእርሱ በመጠላለፍ እና አንዱ ሌላውን በመተንኮስ ጊዜና ሃይል ማባከኑን ቀጠለ። “ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ” የሚለው የሕዝብ ግፊት በማየሉም ነው፤ በነሃሴ 1995 በአሜሪካ ሃገር ሜሪላንድ ግዛት ውስጥ፤ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ሕብረት (ሕብረት) የተባለው ድርጅት የተመሰረተው፡፡ ሕብረት ግን ወደ ታሰበለት ግብ ሳይደርስ፤ ገና ከጅምሩ፤ በውስጡ የነበሩት ድርጅቶች መንጠባጠብ ስለጀመሩ፤ ጉልበት አጣ፤ ያው ፖለቲካው ወደለመደው መጠላለፍ ቀጠለ፡፡ የዚሁ መጠላለፍ ምክንያት ነው በህዳር 1997 ቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ (ቅንጅት) የተባለውን ድርጅት የፈጠረው፡፡ ቅንጅት ከጅምሩ፤ ትግሉ ከኢሕአዲግ ጋር ሳይሆን፤ ትግሉ ከሕብረት ጋር ነበር፡፡ በሁለቱ መካከል የነበረው ሹክቻ ቀርቶ፤ ትግላቸውን በኢሕአዲግ ላይ እንዲያነጣጥሩ፤ ብዙ ግፊት በማድረጋችን፤ በሚያዚያ 1997፤ ምርጫው አንድ ወር ብቻ ሲቀረው፤ በቅንጅት እና በሕብረት መካከል ትብብር ተፈጠረ፡፡ ይህ የሚያሳየው፤ ተቃዋሚው፤ በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀስ እና ሃገራዊ ራዕዩ፤ የደከመ እንደነበር ነው፡፡ የግንቦት 2002 ምርጫም ሆነ፤ የግንቦት 2007 በኢትዮጵያ የተደረጉት ምርጫዎች የሚያሳዩት፤ በተቃዋሚው ጎራ መካከል፤ ኢሕአዲግን በጠላትነት ከመፈረጅ ባለፈ፤ ምንም ዓይነት፤ የአጭር እና የረጅም ጊዜ የጋራ አጀንዳ ነድፎ የማይንቀሳቀስ መሆኑን ነው።ምንም እንኳን መድረክ የተባለ ስብስብ ቢኖርም፤ በመድረክ ውስጥ ያሉ ብሔር ተኮር ድርጅቶች፤ የየብሔራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ከመቆም በቀር፤ ምንም ዓይነት ብሔራዊ የጋራ አጀንዳ ነድፈው የማይንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው፤ በህዳር 2007 የተነሳው አመጽ፤ ያለምንም ፖለቲካ ድርጅት መሪነት፤ በወጣቱ ግብታዊ ስሜት ሊቀሰቀስ የቻለው፡፡



ይህ ግብታዊ አመጽ፤ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ለውስጥ ለለውጥ ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ ሃይሎች ጉልበት በመፍጠሩ፤ ገዥው ፓርቲ፤ ከውስጡ ተገዝግዞ ዛሬ ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ዛሬ ደግሞ ለውጡን የሚመራው ሃይል፤ በሃገራችን፤ የዲሞክራሲያዊ ስልተ ስርዓት እንዲገነባ፤ ሕዝቡ ወዶና ፈቅዶ የመረጠው የፖለቲካ ሃይል የመንግሥትን ሃይል እንዲቆጣጠር ተግቶ በሚሰራበት ወቅት፤ የዚህ ሂደት እንቅፋት በመሆን ላይ ያሉት፤ በተቃዋሚ ጎራ ውስጥ የተሰልፉ ሃይሎች መሆናቸው አስገራሚ ነው። ሌላው ቀርቶ፤ ለመጀመርያ ጊዜ በታሪካችን፤ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች በምርጫ ፖለቲካ ውስጥ እንዲሳተፉ፤ ፈረ ቀዳጅ ሆኖ ድፍረት የሰጠው ኢዴፓ እንኳን፤ “የምርጫው ጊዜ ይራዘም” ሲል መስማቱ፤ አስገራሚ ነው። ሌላው አስገራሚ ነገር፤ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፈው ሃይል፤ ሃይሉን ሰብሰብ አድርጎ፤ ለሃገር ይጠቅማል የሚለውን፤ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ኑሮ እቅድ ነድፎ፤ ለግንቦት 2012 ምርጫ እራሱን ለማዘጋጀት ከመትጋት ይልቅ፤ ምርጫው ውስጥ ላለመሳተፍ “ሰበብ” መደርደሩ ነው፡፡ በሃገራችን ውስጥ ከ130 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች መኖር እራሱ፤ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፈው ሃይል፤ መሪ ያጣ፤ የፖለቲካ ሃይል ለመሆኑ፤ ምስክር ነው፡፡ በመቶ የሚቆጠሩ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን፤ አስተባብሮ፤ ቁጥራቸውን መቀነስ ያልቻለ የፖለቲካ ሃይል፤ ስንት የተወሳሰብ ችግር ያለባትን ሃገር በመሪነት ተረክቦ ሊያስተዳድር ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል ወይ?



የምርጫ ቦርድ በተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀውን የምርጫ ሕግ ተከትሎ፤ ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የምንሰማው አቤቱታ ሰበብ እንጂ፤ ምርጫ ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚያግድ አይደለም። ጊዜ ሰጥቶ ተግቶ በመስራት፤ ፖሊሲ ነድፎ፤ 10 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ማሳመን የማይችል የፖለቲካ ድርጅት፤ እንዴት ነው በሚሊዮን የሚቆጠር መራጭ ሊያሳምን የሚችለው? ይህንን ተከትሎ የምንሰማቸው አቤቱታዎች፤ ትላንትና ላይ ቆመው የወደፊቱን ማየት በማይፈልጉ የፖለቲካ ሃይሎች ነው፡፡ በግንቦት 2012 ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ ምርጫ እንደሚካሄድ ለማንም ሚስጥር አይደለም፡፡ ይህ ከአምስት አመታት በፊት ጀምሮ ይታወቅ ነበር፡፡ በሃገር ውስጥም ያሉ ይሁኑ ከሃገር ውጪ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ በአሁኑ የለውጥ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ የወሰኑት፤ በ1987 የጸደቀውን ሕገ መንግስት ተቀብለው ነው፡፡ ሕገ መንግስቱም በየአምስት ዓመቱ ብሔራዊ ምርጫ እንደሚኖር ደንግጓል፡፡ ከዛም አልፎ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ምርጫው እንደሚካሄድ እና ተቃዋሚ/ተፎካክሪ ድርጅቶች፤ መርሃ ግብራቸውን በመንደፍ ለሥልጣን እንዲወዳደሩ፤ ሥልጣን መያዝ የሚቻለውም በሕዝብ ምርጫ ብቻ መሆኑን ደግመው ደጋግመው መክረዋል፡፡ የግንቦት 2012 ምርጫ መካሄድ፤ ለማንም አዲስ ዜና ሊሆን አይገባውም፡፡



አሳዛኙ ነገር፤ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ውስጥ የታዘብነው፤ ለምርጫ ውድድር ከመዘጋጀት ይልቅ፤ በሙሾ ፖለቲካ ጊዜ ማባከንን፤ የሕዝብን ተስፋ ማጨለም እና፤ የራስን ድክመት ለመሸፈን ስበብ በማብዛት የተገኙ እድሎችን ማበላሸት ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ዓይነት የፖለቲካ ሃይሎች አሉ፡፡ አንደኛው ሃይል፤ ትላንት ላይ ቆሞ የወደፊቱን ለማየት ያልፈቀደ እና፤ በሙሾ ፖለቲካ፤ የፖለቲካ ሕይወቱን ማርዘም የሚችል የሚመስለው፤ እንዲሁም በአቤቱታ ሊፈጠር በሚችል፤ ትርምስ ሥልጣን በአቋራጭ ይዛለሁ ብሎ በቅዠት ውስጥ ያለ ነው፡፡ ሌላው የፖለቲካ ሃይል ደግሞ፤ ካለፈው ተምሮ፤ ዛሬን ተጠቅሞ፤ ነገ ሕዝቡ የተሻለ ሕይወት እንዲኖረው፤ ሃገራችን ነገ የተሻለች ሃገር እንድትሆን ተግቶ የሚሰራ ነው፡፡ ብዙዎቹ የብሔር ድርጅቶች፤ መሪዎቻቸው፤ ትላንት ላይ ቆመው የሚያላዝኑ በመሆናቸው፤ በምርጫው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊኖራቸው ይችላል። ይህን አሉታዊ ተጽእኖ ግን አቅጣጫ ሊያስቀየር የሚችለው፤ በተለይ የድርጅቱ አባላት፤ በአጠቃላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በትላንት ላይ ቆመው በቀሩት እና፤ በወደፊት መፃኢ እድሉ ላይ ባተኮሩ ድርጅቶች መካከል ያለውን ልዩነት በመረዳት፤ የወደፊት እድሉን ብሩህ የሚያደርጉ የፖለቲካ ድርጅቶችን በመምረጥ እና፤ የፖለቲካ ነጋዴዎችን፤ አጨበርባሪነት እምቢ በማለት ነው።



ስለትላንትና  እያጋነኑ በማውራት፤ በሕዝቡ ውስጥ ጥላቻን በመዝራት ጊዜ እና ሃይል የሚያባክኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ለሕዝብ የሚጠቅም ምንም ዓይነት መርሃ ግብር የላቸውም፤ ሕዝቡ ይህንን በቅጡ ሊረዳ ይችላል። ዛሬ ላይ ሆነን፤ እንደ ኦፌኮ መሪዎች፤ የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ፤ ከጥቁር አሜሪካውያን ታሪክ ጋር በሚያነፃጽር የሃሰት ትርከት፤ ሕዝብ በመቀስቀስ እና ስለኢሕአዲግ ኢፍትሃዊነት በማውራት ምርጫ ላይ ተሳትፎ፤ ማሸነፍ የሚቻል አይመስለኝም። ጥያቄው እነዚህ እና መሰል ድርጅቶች፤ የኢኮኖሚ፤ የማህበራዊ መርሃ ግብራቸው፤ እንዲሁም የፖለቲካ ፍልስፍናቸው ምንድነው የሚል ነው። እንደ ጃዋር መሐመድ ያሉ ጽንፈኞች፤ የሚፈልጉት የፖለቲካ ሃይል በምርጫ ከተሸነፍ፤ ሁከት ለመፍጠር እየተዘጋጁ መሆናቸው፤ ምልክቶቹ እየታዩ ነው። ጃዋር፤ ለኒውዮርክ ታይምስ በሰጠው ቃለ ምልልስ፤ ምርጫው ፍትሃዊ እና ነፃ መሆኑን የሚመዝነው በእሱ መመረጠ እና አለመመረጥ መሆኑን መግለፁ፤ አስቂኝ ብቻ ሳይሆን፤ የፖለቲካ እንⶽጭ መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳየበት ነው። ይኸው ግለሰብ፤ በቅርቡ የምርጫ ቦርድን የሚያምነው 50% መሆኑን እንደገለፀ አቶ ያሬድ ጥበቡ በፌስቡክ ገፃቸው ለጥፈዋል። የምርጫ ቦርድን ተአማኒነትም ሆነ፤ ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ መሆኑን የሚመዘንበትን ሚዛን፤ መስፈርቱን የሚነግሩን እንደ ጃዋር ዓይነት ሰዎች ዓላማቸው አንድ ነው፤ ይህም እኛ ካላሸነፍን፤ ምርጫው ነፃ አልነበረም ለማለት ነው። እነዚህ ሃይሎች ግን ቀጣዩን ምርጫ ሊያሸንፉ የሚችሉበት መርጋ ግብራቸው እና ማራጭ ሃሳባቸው ምን እንደሆነ እንኳን አይነግሩነም።



በዚህ ፀሃፍ እምነት፤ እነዚህ የፖለቲካ ሃይሎች፤ ሙሾ ከማውረድ ባለፈ አቅም የላቸውም። ኦፌኮም ሆነ በመድረክ ስር የተሰባሰቡት የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ንፈ ሃሳብ አቅርበው የሚያውቁት መቼ ነው? እስከዛሬ የነበረው “ፖለቲካ” “ኢሕአዴግን በመኮነን” ላይ ብቻ ያተኮረ ፖለቲካ ነው፡፡ ዛሬ ትላንት አይደለም፤ ኢሕአዴግን በመኮነን ብቻ መጽደቅ አይቻልም፤ “የራስን የጽድቅ” ሥራ ሰርቶ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ በሚቀጥለው ምርጫ ኢሕአዴግ የሚባል የፖለቲካ ድርጅት እንኳን አይኖርም፡፡ ስለዚህ፤ ኢሕአዲግ አሳሪ ነው፤ ገራፊ ነው፤ ገዳይ ነው የሚል አጀንዳ ቦታ አይኖረወም፡፡ በዚህ ጸሃፍ ግምት፤ ዛሬ ላይ ሆነው፤ የነገን ተስፋ በመሰነቅ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ፤ እጅግ የሚደነቅ ተግባር እያከናወነ ያለው፤ ኢዜማ የተባለው የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ በኢዜማ ውስጥ የተሰባሰቡ የፖለቲካ ሃይሎች፤ ብቃታቸውን እና፤ የድርጅት ስርዓታቸውን (ዲስፕሊን) በተግባር አሳይተዋል፡፡ ምርጫው አይቀሬ መሆኑን በመረዳት፤ ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች አሰባስቦ አንድ ድርጅት ያዋቀረው ይህ ድርጅት፤ ስለትላንትና ስሞታ በማቅረብ ጊዜውን ሲያባክንም ሆነ፤ በትላንትና ታሪክ ላይ “የፖለቲካ ልፍያ” ውስጥ ሲንቦጫረቅ አናየውም፡፡ ይህ ፀሃፍ፤ ኢዜማ ውስጥ ካሉ ከማናቸውም ጋር ግላዊ ግንኙነት የለውም። በአንድ ወቅት ብቻ ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ዶ/ር ሳᎀኤል ዮሃንስ ጋር፤ በአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ላይ ለውይይት ከመቅረብ እና የተወሰነ ውይይት በግል ከማድረግ ውጭ፤ ምንም ዓይነት የጠበቀ ግንኙነት የለውም። ይህ ጽሁፍም አላማው ኢዜማንም ሆነ ሌላውን የፖለቲካ ድርጅት ምረጡ ወይም አትምረጡ ለማለት የተዘጋጀ አይደለም። የጽሁፉ ዓላማ፤ ሃገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የሚፈጥሩትን ሰበብ አቁመው፤ ጊዜያቸውን ተጠቅመው፤ ለሕዝብ አማራጭ እንዲያቀርቡ ለማሳሰብ ነው።

ከኢዜማ አካሄድ ብዙ መማር ይቻላል፤ ኢዜማ በበርካታ የምርጫ ጣብያዎች እጩዎቹን አዘጋጅቷል፤ ለአይቀሬው ምርጫ መርሃ ግብሩን ነድፎ፤ አባላቶቹ እንዲወያዩበት አድርጓል፤ “የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” ዓይነት ሰበብ ከኢዜማ አይሰማም። ኢዜማ ዛሬ ላይ ሆኖ፤ ለነገ፤ ለሃገር ያለውን ራዕይ፤ በወረቀት አስፍሮ የምርጫ ዘመቻ በማድረግ ላይ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ሃገራችን ዛሬ የምትፈልገው እንዲህ ዓይነት ይፖለቲካ ሃይል ነው። ለኢዜማ ተመጣጣኝ፤ ተፎካካሪ የሚሆነው፤ በቅርቡ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ መሪነት የተመሰረተው፤ የብልጽግና ፓርቲ ነው። የብልጽግና ፓርቲ ከኢሕአዴግ የወረሳቸው፤ ድርጅታዊ መዋቅሮች እና ሃብት ስላለው፤ በሃገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በክልሎች ደረጃ የመወዳደር ብቃት አለው። በዚህ ፀሃፍ ግምት፤ ብልጽግና ፓርቲ፤ እንደ ኢዜማ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ጉዳይ በእውቀት የተካኑ ሰዎች የሉትም። ብዙዎች፤ ብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ያሉ የአመራር አካላት፤ አቅማቸው ውሱን ነው። ሆኖም፤ እንደ ዶ/ር አብይ ያሉ፤ ብቃት ያላቸው መሪዎች፤ ሌሎች ብቃት ያላቸውን ልሂቃን ወደ ብልጽግና ፓርቲ ሊጎትቱ ይችላሉ። ትልቁ ነገር፤ ብልጽግና ፓርቲ በትላንትና ላይ ቆሞ ሙሾ እያወረደ አይደለም፤ ለሕዝብ የነገ ራዕዩን እያቀረበ ያለ እና፤ ለሕዝብ ተስፋ የሰጠ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ቀጣዩ ምርጫ፤ ስለፍትህ፤ ዲሞክራሲ፤ የፕረስ ነፃነት፤ ወዘተ ዓይነት አጀንዳዎች ብዙውን የክርክር ቦታ የሚወስዱ ሳይሆኑ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚደረግው የሥራ ፈጠራ፤ የቤት እጦት ቅነሳ፤ የሕክምና ተቋማት መስፋፍያ፤ የትምህርት ፍኖተ ካርታውን እና ትምህርት ቤቶችን ማሻሻያ፤ በሃገሪቱ ውስጥ የብሔራዊ ከበርቴውን ሊያሳድግ የሚችል የቀረጥ ሕግ፤ ሕፃናት እና አዛውንት ተኮር መርሃ ግብር፤ የፍትሕ ስርዓቱን ማሻሻያ፤ እንዲሁም በሃገሪቱ ውስጥ ያሉትን መሰረታዊ ልማቶችን ማሻሻያ፤ ተገቢ የሆነ የሞንተሪ እና የፊሲካል ፖሊሲውን ቀርፆ፤ የምርት አቅርቦት አሻሽሎ፤ የኑሩ ውድነትን መቀነስ እና፤ በተለይም ደግሞ፤ የሕዝብ ቁጥርን ጭማሬ ፍጥነት የሚገድብ እቅድን የተመለከቱ ክርክሮች ትኩረት የሚያገኙበት ይሆናሉ የሚል ግምትም አለ። ከምንም በላይ ቀጣዩ ምርጫ፤ ትላንት ላይ ቆመው ሙሾ በሚያወርዱና፤ ዛሬ ላይ ሆነው ስለወደፊቱ የሃጋራችን እድገት ራዕይ ባላቸው ሃይሎች እንደሚሆን፤ በርካታ ምልክቶች እየታዩ ነው። ስለዚህ፤ ሁሉም የፖለቲካ ሃይል፤ ጎራዴውን ሳይሆን አዕምሮውን በመሳል፤ ለውድድር ይዘጋጅ እላለሁ።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ።              

ኦህዴድ ከየት ወዴት? (ክፍል ሁለት)

ኡስማን ሙሉዓለም

በክፍል አንድ ፅሁፌ
ኦህዴድ እንዴት ከማጡ ወደ ድጡ እንደተንደረደረ ለማየት ሞክሬ ነበር፡፡ በክፍል ሁለት ላይ ኦህዴድ ግብዓተ መሬቱ እንዴት እንደተፋጠነ እናያለን፡፡

በኢትዮጵያ ህገመንግስት ይሁን በኢህአዴግ አሰራር ከኢህአዴግ ግንባር ድርጅቶች ማንም ሰው መመዘኛው ካሟላ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ለመሆንና ብሎም ጠቅላይ ሚኒስተር ለመሆን የሚያግደው ነገር አልነበረም። ኦህዴድ አዲሱ ሊቀመንበሩን የኢህአዴግ ሊቀመንበር አድርጎ ካስመረጠ በኃላና ጠቅላይ ሚኒስትርነቱም ከተቆጣጠረ በኃላ በሁሉም የኦሮሞ ሊሂቃን ሊባል በሚችል ደረጃ አዲስ ክስተት እንደተፈጠረ ተደርጎ ነበር የተቆጠረው ወይም የተሰበከው።  ይህንን ሁኔታ ይቻል እንዳልነበረ ሆን ተብሎ ተሸፋፍኖ ለመጀመርያ ጊዜ ኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆነ ተብሎ ተጋኖ ቀረበ። ትግራዋይም ወላይታም ለመጀመርያ ጊዜ ነበርኮ ጠቅላይ ሚኒስተር የሆኑት! ምን አሁን የተለየ ነገር ተፈጠረ የሚያስብልና የሚያስተዛዝብ ሆነ።

ይህ አሁን በአገሪትዋ ላይ የተፈጠረው ለውጥ/ነውጥ የቀየሱት ሰዎች ይህ የኢህአዴግ እምነትና አሰራር አጥንተውና አስጠንተው ባህርማዶ ላይ ሆነው አቅደውና ዝግጅት አድርገው ስለመሩት ነበር የተሳካ የቀለም አብዮት ያደረጉት፡፡ ይህ ቀለም የሌለው የቀለም አብዮት የተሳካው የኢህአዴግ አሰራር ዕድል ስለሰጣቸው ነበር። ይህም አድርገው ይኸው አሁን ወዳለንበት ትርምስምስ ያለ ሁኔታ ከተቱን። በኢትዮጵያ የነበረውን ፈጣን ዕድገት፣ ልማትና ዲሞክራሲ እንዳልነበረ ሰበኩ፡፡ የነበሩት ጉድለቶቹን ነቅሰውና አጉልተው በማውጣት የችግሩ ምንጭ አምታትተው ምክንያት ያልሆነውን ምክንያት አስደርገው ፈጣን ዕድገት ያስመጡልንን አብዮታዊ ዲሞክራሲያችን፣ ህገ መንግስታችንና ፌደራላዊ ስርዓታችንን ወነጀሉ፡፡ የህዝቡን ጥያቄዎች የማይመልስ መፍትሔ ብለው የስርዓት ለውጥ ብለው ወደ ባሰ ችግርና ትርምስ እንድንገባ ሆነ።

በስመ ኦሮሞ ስልጣን የያዙት ጠቅላይ ሚኒስተር መጀመርያ ላይ ኦህዴድና ምክትላቸው የነበሩትን ለማ መገርሳ፣ እነ አባዱላና ግርማ ብሩ ሳይቀሩ በሁሉም ጉዳይ ያማኩርዋቸው ነበር። ይህ ሲያደርጉ አብዮታዊ ዲሞክራሲን አጥብቀው የሚያምኑትንና ‘የህወሓት ተላላኪ’ አደረጉን የሚሉዋቸውን የድርጅቱ አበላት ስም ዝርዝር ይዘው በተለያየ ምክንያቶች ከአገር ውጭ ርቀው እንዲሄዱ አደረጉ፡፡ አበላቱ በየስብሰባው የለመዱትን በእኩልነት አስተያየት መስጠትና ሁሉም ውሳኔዎች በድምፅ እንዲወሰኑ የማድርግ ልምድ አዲሱ ሊቀመንበር አይፈልጉምና ለትምህርት፣ ለአምባሳደርነት እና ለተለያዩ ስራዎች እያሉ ከድርጅቱ ከኦህዴድ እንዲሩቁ አደረጉ። በመጨረሻም ለሳቸው የሚመቹትን ብቻ አሰባስበው የገደል ማሚቶ ስራ አስፈፃሚ ፈጠሩ።

ለማ መገርሳ ግን የለማ ቲም ያመጣው ለውጥ በሚባልበት ሁኔታ በቀላሉ የገደል ማሚቶ መሆን አልቻሉም። ጠቅላዩ መጀመርያ ስልጣን የያዙ ሰሞን ለማን አንተማ አለቃዬ ነህ! ብለው ቤተመንግስት ውስጥ አብረህኝ መኖር አለብህ ተቀራርበን እየተማከርን መስራት አለብን ብለው መኝታ ክፍል ተዘጋጅቶላቸው (ማን ያውቃል ሌላም ነገር ተዘጋጅቶላቸው ይሆናል) አብረው ተዳብለው መኖር ጀምረው ነበር። እንደዛ አብረህ እየኖርክ በየአደባባዩ በግልፅ የሚያሞግስህን ሰው ጠንከር ያለ ሃሳብ ማቅረብ ወይም ተቃውሞ ማቅረብ በጣም የመርሆ ሰው ካልሆንክ ይከብዳል። ለማ መገርሳም የከበዳቸውም ይመስለኛል። ለማ መገርሳ ግን አብይ ስመከረው እሺ ይልና ሌላ ነገር ይስራል፤ ከተነሳንበትና መነሻ ካደረግነው ዓላማ አፈንግጦ እየሄደ ነው ብለው ማማት የጀመሩት ብዙም ሳይቆዩ ነበር። ይህ በብዙ የኦሮሞ ሊሂቃን የሚታወቅ ጉዳይ ነበር። ለማ መገርሳ የስራ ምክንያት እያደረጉ ከቤተመንግስቱ መራቅና ከዛም ከሰውየው ጭራሽ የማይገናኙበት ሁኔታ እየተፈጠረ ሄደ። ተጣሉ የሚል ወሬ ሲበዛ አብይ የሆነ መድረክ ፈጥረው ወይም ለማ ያዘጋጀው መድረክ ካለ በድንገት ተገኝተው አንድ ላይ ነን ሞት ብቻ ነው የሚለየን ብለው ይመፃደቁና ህዝቡ፣ ሊሂቁ፣ ወዳጅም ጠላትም ያሳስታሉ። ድሮስ ሊያስመስሉ ብለው ነው እንጂ በመሃላቸው ንፋስም አይገባ ወይም ፀረ-ለውጥ ኃይሎች ሆን ብለው ያስወሩት ነበር አሰኝተው ጊዜ ይገዛሉ። ሰውዬው ኦህዴድን በዚህ ሁኔታ አስታግሰው ብአዴንና ግንቦት ሰባትን የሚያስደስት ነገር በፓርላማ ወይም በሆነ መድረክ ጣል ያደርጋሉ፡፡ እሳቸው ኦሮሞ ሳይሆኑ ንፁህ ኢትዮጵያዊ ናቸው ተብለው ግልብ ሁሉን ወደ ፈለጉበት አቅጣጫ ያስጋልብዋቸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከሰሜን ህወሓት ከደቡብ ኦነግ ሲቃወሙ የተለያዩ አልባልታዊ ምክንቶች ይደረድራሉ፡፡ ለሰሜኑ ተቃውሞ መያዣ የያዙዋቸውን ትግርኛ ተናጋሪዎችና የፖለቲካ እስረኞችን ልፈታ እያሰብኩ ነው እናንተ ተቃውሞቹሁን ለምን ለዘብ አታደርጉትም። ብአዴኖች እነ ደመቀና ገዱ ስለናንተ ብዙ ነገር እያነሱ እርምጃ ውሰድ እያሉኝ እኔ ሁኔታውን ለማብረድ እየጣርኩ ነኝ። እናንተም እያገዛችሁኝ አይደለም ብለው ለማለሳለስ ይሞክራል። የውጭ አማካሪዎች መቼ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በቅድመ ተከተል አዘጋጅተው ይሰጥዋቸዋል። ነገር ግን አንዳንዴ ሰውዬው ጭብጨባ ሲበዛ ከተመከሩት ወጣ እያሉ እየዘላበዱ ያስቸግሯቸዋል። ነገር ግን ነገርየው ጊዜ ለመግዛት እንደሆነ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ኦነግን ደግሞ ከአስመራና ከካይሮ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አምጥቻቹሁ ለምን ፋታ አትስጡኝም? ብለው መልእክት ይልኩባቸዋል። ሌላ ጊዜ አባገዳዎች ጠርተው ስልጣን ለመጀመርያ ጊዜ እኔ ኦሮሞ ልጃቹሁ ይዠ እንደማገዝ ኦነግ እየረበሹኝ ነው። ኦሮሞ መምራት እንደማይችል መልእክት እየተላለፈ ነው። አንዴ ይህ እጃችን የገባው ስልጣን ካጣነው መቼም መልሰን አናገኘውም። አሁን ኦሮሞዎች መተባበር ነው ያለብን በመካከላችን ሽኩቻ አያስፈልግም። ግድ የላቹሁም ጊዜ ለመግዛት አበሾችን አንደየሁኔታው አያያዝ ማድረግ አለብኝ። እነሱ ኦነግን ለምን ልኩ አታስገባውም? የህግ የበላይነት እያስከበርክ አይደለህም። ወደ ኦሮሞነትህ እያደላህ ነው እያሉኝ ነው። ሰለዚህ ኦነግን መክራችሁ ጭጭ አሰኙልኝ ብለው አባገዳዎችን ይልኩዋቸዋል። የእስስት ተለዋዋጭ ታክቲክ እና ስትራተጂ ተከትለው የስልጣን ዕድሜቸውን ለማራዘም ይጥራሉ።


አብይ አህመድ በተፈጥራቸው እሳቸው ተናግረው በጭብጨባ እንዲቀበልዋቸው ወይም ተሰብሳቢዎቹ እንዲሰሙ ብቻ እንጂ ጥያቄ አይወዱም። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ውጭ ስብሰባ አይፈልጉም። እንኳን የኢህአዴግ ምክርቤት 180 ሰዎች ሰብስበው ስንቱ ጥያቄ አለኝ፣ ተቃውሞ አለኝና የተለየ ሃሳብ አለኝ ብሎ የሚነዘንዝ ካድሬ ያለበት ይቅርና የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴንም ሰብስበው አያቁም። የኢህአዴግ ምክር ቤት የሚፈሩት ጥያቄውንም ክርክሩንም ነበር። በመቶ ሰማንያ ሰው ፊት ተቃውሞ ቀረበ ማለት ለሳቸው ውርደት ነው። በተለይ ህወሓትና ከድርጅታቸው ነበር ኦህዴድ ለማ መገርሳ እየተቀባበሉ የአብይ አስተዳደር ግድፈትና ውድቀት እንዲነገር ጭራሽ አይፈልጉም። የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴን ስብሰባ የማይፈልጉት ግን ሌላ ምክንያት ነበራቸው። ነበር ሆኖ ቀረ አይደል።

አምባገነን አብይ ምን ይሳነዋል! ኦህዴድን ቀድሞ በግሉ አፈረሳት። ምክትላቸው የነበረው ለማ የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሜቴ ስብሰባ እናድርግ ሲል ደንገጥ ብለው ለምን? ይላሉ። ህፃን ልጆች ሁነን አያ ጅቦ መጣ ስንባል እንደምንደነግጠው የማ/ኮሜቴ ስብሰባ ለአብይ የሚያስበረግግ ነበር። ለማ መገርሳና አብይ ይህን ማ/ኮሚቴ ይዘው ነበር በድንገተኝነት ምንም ግምገማ ሳይደረግ ሙክታርና አስቴርን አውርደው ለማና ወርቅነህ ገበየሁ (አሁን መጣያ አጥተው ካንዱ ወደ አንዱ እያንገላቱት ያለውን ሲፈጠር የጀርባ አጥንት ያልታደለውን) ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ያደረጉት። ታድያ ይህን የኦህዴድ ማ/ኮሚቴ መድረክ ፈርተው እንዳይደረግ ማድረጋቸው ስልጣንን ከሁሉም ነገር አብልጠው ለሚወዱ አብይ አህመድ እንደ ዋነኛ አደጋ ማየታቸው ምኑ ላይ ስህተት ሁኖ ሊታያቸው ይችላል።

አብዛኛው ፓለቲካ ላይ ያለ ሰው አብይ አህመድ ቀድሞ ማጥፋት የሚፈልጉት ኢህአዴግን ይመስለዋል። በኔ ግምት ግን አብይ አህመድ ቀድሞ ማጥፋት የሚፈልጉት ብቻ ሳይሆን ቀድመው ያጠፉት ኦህዴድን ነው። ምርጥ የኦህዴድ አመራሮችና ካድሬዎችን በማጥፋት ከስልጣን በማውረድ ምርጥ የመሬት ቸብቻቢዎች ሌቦችን በአደባባይ የሚታወቁ ጉበኞች እንደ ብርሃኑ ፀጋዬ፣ ደምመላሽ ገብረሚካኤል፣ ሽመልስ፣ አዳነችና ሌሎችም ወደፊት አምጥተው ሾሙ። ምርጥ ካድሬዎችና ለኦሮሞ ህዝብ የሚታገሉትን ገድለውና አስገድለው የቀሩትንም ለውጥ ያስፈልጋል በሚል በምትካቸው ሌቦችንና ጉበኞች ህዝቡ የተማረረባቸው ቦታ እየቀያየሩ ሾሟቸው። የለውጥ መዝሙር በባዶ ቦታ ዘመሩ። የኦሮሞ ህዝብ በተለይም የወጣቶች (የቄሮዎች) ጥያቄዎች እንኳን ሊመልሱ የባሰ በለውጥ ሂደት ነው ያለነው ችግሩ በሽግግር ወቅት የሚፈጠር ነው። ቻሉት! ብለው ይመልሳሉ። ጥያቄው አፍጥቶ ሲመጣባቸው ደግሞ ሦስተኛ ወገን፣ ፀረ ለውጥ ኃይሎችና ኦሮሞ አገር ማስተዳደር እንደማይችል ለማሳየት የሚፈልጉ ወገኖች ችግር እየፈጠሩ ስለሆነ የናንተን ችግር ተረጋግተን አጥንተን መፍታት አሁን አንችልም ታገሱን ይላሉ።

አሁን በአገራችን ኦህዴድ የሚመራው ለውጥ አንዳንዴም ኦሮሞ የሚመራው መንግስት ቢባልም በተጨባጭ የአገሪቱ መሪዎቹ ግን ቅጥረኛው አብይና ቅጥረኞቹ አክራሪ ኒዮ ሊበራል ኃይሎች ናቸው። ከቄሮ ትግል ጀምሮ የነበረው ዋና ድብቅ ዓላማ ቅጥረኛውንና ጥገኛ ሃይል ስልጣን ላይ አውጥቶ ኢትዮጵያን ራሷን እንዳትችል በማድረግ በነሱ ትዕዛዝ የምትመራ ማድረግ ነው። የቄሮ የስራ ማጣት፣ የህዝቡ መልካም አስተዳደር እጦት ጥያቄ ጉዳያቸው አልነበረም። በጭቁኖች መካከል ህብረት እንዳይኖር አድርገው የቄሮ ትግል ውጤታማ እንዳይሆንና ወደ ፀረ-ህወሓት፣ ፀረ-የትግራይ ህዝብና ፀረ-ትግርኛ ተናጋሪ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ያደረገው በኦህዴድ የበቀለው አረም አመራር የፈጠረው ለውጥ አይደለም። ይህ እንደሚመጣ ህወሓቶች በምርጫው ምሽት አጥብቀው ተቃወሙ። እነ በረከት ስምኦን ከብአዴን እነ ስራጅ ፈርጌሳ ከደህዴን ተቃወሙ። በረከት ስምኦን ለእስር የዳረገውን ትንቢት የሚመስል የተቃውሞ ንግግር ያደረገውም ያኔ ነበር። በረከት አብይ ከተመረጠ አገራችንን አሳልፈን ለውጭ ሃይሎች የምንሰጥበት ሁኔታ እንደሚፈጠር በማስረጃ አቀረበ። እነ አዳነችና ለማ መገርሳም አብይ እደዛ እንዳልሆነ በማስረጃ ሳይሆን ባዶ ቃላቶችን ተጠቅመው ሰበካ የሚመስል ንግግር አድርገው በውጭ አብዛኛውን የምክርቤት አባል መልምለውና ገዝተው ያስገቡትን እንዳይፈርሱባቸው ተከራከሩ። ቤቱ ትክክለኛውን አደጋ እንዳያይ አደረጉት፡፡ አብይ ተመረጠ። አለቀ። ለኔ በአጠቃላይ የለውጡ ትግሉ የተቀለበሰው እነ አብይ ስልጣን ሲይዙ ያኔ ነበር።
ኦህዴድ ታድሶ እነ ለማንና አብይን ወርቅነህን ጠራርጎ ቢታደስ ኖሮ ለውጡ አይቀለበስም ነበር። ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ የከዳው ፎርማሊ በዚች ቀን ነበር። ፎርማሊ ያልኩት ኦህዴድ ዝቅጠቱ የቆየ ቢሆንም በጥልቀት ተሃድሶ ይታደስ ይሆናል የሚል ግምት ስለነበር ነው። ኦህዴድ መቼም የማያስቆጭ ፕሮግራም ሽጦ ኦሮማራ ብሎ እንደሱ ከዘቀጡት የብአዴን አባላት ጋር አበረ፡፡ ከጎሹ ወልዴና ካሳ ከበደ የሚሞዳመድ ሆነ፡፡ አዲሶቹ ደርጎች በወጣትነት ዕድሜያቸው አሮጌ ብትቶ አስተሳሰብ አንጎላቸው ከሞላው ጋር ግንባር ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ ነበር የኔ ለውጡ የተቀለበሰው። ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው፣ ስንኖር ኢትዮጵያውያን ስንሞት ኢትዮጵያውያን ሲባል ያኔ ነበር ለውጡ የተቀለበሰው። የቄሮ ትግል የከሸፈው! ለዘለቄታው የማይጠፋ ቢሆንም ትግሉ ውጤታማ ሳይሆን የቀረው። በተመሳሳይም የአማራ ህዝብም ትግል የለውጥ ፍላጎት የከሸፈው በዚሁ ደቂቃና ሰዓት ነበር።

ያልታደሰ ኢህአዴግ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። ለዚህ ነው አብይን የወለደ የዘቀጠ ኢህአዴግ ወርቅ የሆነ ፕሮራም ይዞ የሞተው። አርማጌዶን እንዲሁ ቅርብ የሚገኝ ሳይመስለን ራሳችንን አርማጌዶን ውስጥ አገኘንው። ኢህአዴግ ተልእኮውን ሳይፈፅም በውስጡ በበሰበሱ ትሎች ተበልቶ የተጋደመው። የፈጠሩት ድርጅቶችም ከዚህ ውጭ አልሆኑም፡፡ ደህዴን ከላይ የነበረ ቢመስልም የኦህዴድ ተላላኪ መሆን ፀጋ ነበር እያለ የአብይ አህመድ ተላላኪ ሆነ፡፡ በጣት የሚቆጦሩ መሪዎች ደህዴን የሚለውን ስም ይዞ ተበታተነ። ሃይለማርያም በታሪክ የሚወሳበት ታሪክ ካላ የብተና ታሪክ ነው። ኦህዴድ የተጠጋው ብአዴንም በውስጥ ሽኩቻ ለራሱም ለደባሉ ኦህዴድም ሳይሆን ቀርቶ ከአብን ልወዳደር ብሎ ምኑም ሳይችለው ውስጡ ታመሰ። የተረከባትን ክልል አንድና ሰላም ያላት አድርጎ መምራት ተሳነው። እርስበርስ እየተፎካከሩ የቲም ለማ የቁርጥ ቀን አባል ተብለው የሚታወቁት ገዱ ክልሉ ውስጥ በሰላም መኖር ሳይችሉ ቀርተው ለህይወታቸው ሰግተው አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው የጀግናው ቀነኒሳ ሆቴል ውስጥ ከሁለት ሳምንት በላይ መሽገው ቆዩ (በነገራችን ላይ በኮፒራይት ህግ ሳይጠየቁ አይቀሩም መቐለ አክሱም ሆቴል ላይ እንደ መሸጉት በመመሸጋቸው)። ገዱም የሃይለማርያም ደሳለኝ ዓይነት ሁኔታ ገጠማቸው፡፡ በሽምግልና በፈቃዳቸው ስልጣን እለቃለሁ አሉ ተብለው ነብሳቸው ይማርና ለአምባቸው ስልጣኑንም አደጋውንም ጭምር አስረክበው ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ተባሉ። እንደተፈራውም አምባቸው በገዛ ቢሮቸው በጭካኔ በጥይት ተደብድበው ተገደሉ። ኦህዴድ በማይመራው መንግስት ኦሮሞ በማያስተዳድረው ስርዓት እንዴት ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል? ኦህዴድ የአብይ አህመድ የፈረስ ስማቸው እንደሆነ እንጂ የትኛው ክልል ነው ያስተዳደረው፡፡ ኢትዮጵያን ይቅርና ኦሮሚያንም ማስተዳደር አቅቶት አይደለም እንዴ ለጄነራል ብርሀኑ ጁላ በወታደራዊ ኮማንድ ፖስት እንዲያስተዳደሩለት ያስረከበው፡፡ ክልሉ በአጭሩ የጦርነት ቀጠና ሁኗል፡፡ አብይ አህመድ ከሚንሰፈሰፍላቸው ያለፉት ጨቃኝ ሰርዓቶች ፊፃሜ አልተማረም፡፡ ጨካኙ አፄ ኃይለሥላሴ የእንግሊዝ አውሮፕላን ተበድረው በመቐለ እና ጨካኙ ደርግ በሐውዜን ህዝብ በተሰበሰበበት የገበያ ቀን የሚያስተዳድሩት ህዝብ እንደጨፈጨፉት የሚታወስ ነው፡፡ አብይ አህመድ በአጭሩ የስልጣን ዕድሜ ዘመኑ የወለጋ ህዝብ ተቃውሞን ለመጨፍለቅ በቀርቡ ጊዜ ሁለቴ በሄሊኮፕተር ከሰማይ እሳት የጎረሰ የፋክራስ ቦንብ አርከፈክፎባቸዋል። አብይ መስሎት እንጂ በአውሮፕላን ድብደባ የተገታ ትግል የትም አገር አልታየም።

ኦህዴድ ወደ ጭንቅላቱ ጫፍ ላይ በስብሶ ገምቶ ቢሆንም የፓርቲ ውስጥ ትግል/ አብዮት ቢደረግ የመዳን ዕድል አልነበረውም ማለት አይቻልም። ከላይኛው ካድሬ ጥቂቶች ከመካከለኛው ደግሞ ቀላል ያልሆኑትና ከታችኛው ደግሞ አብዛኛው ጨርሶ ህዝባዊነቱን ያላጠፋና መስመሩን ያልከዳ ቢያንስ ደግሞ ኦሮሞ ብሄርተኝነቱን ያልሸጠ ስለነበረ እስከቅርብ ግዜ ድረስ ተስፋ ሲደርግበት ነበር። የዚህ ማስረጃ በእንደመር ውይይት ወቅት ያነሳቸው የነበሩት ጥያቄዎች ማስረጃ ናቸው። የለማ መገርሳ የረፈደበት የቁጭት አቋም ይዞ ጠይቋል። ተከራክሯል። ፀረ ዲሞክራሲ የሆነው አብይ አህመድና ቡዱኑ የካድሬዎቹ ተቃውሞ ረጋግጠው እና አስፈራርተው አለፉት እንጂ። ምክትል ሊቀመንበሩ ያልተገኘበት፣ ሳይታወጅና በምን አሰራር እንደተጠራ የማይታወቀው የኦህዴድ ጉባኤ ተብዬ መድረክም ቢሆንም አልጋባልጋ ሆኖ መደመሩንና መበልጠጉን አልተቀበለም። በድምፅ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ተቀበሉት ብለው ራሳቸው ሊቀመንበሩ ከጉባኤው በላይ ሆነው በስሙ አወጁ።

ኦህዴድ የግል ካምፓኒያቸው ይመስል ከስሟል ብለው አከሰሙት። የኦህዴድን ቢሮዎች ለብልጥግናቸው አስተላለፉዋቸው። ለማ መገርሳ ኦህዴድን ይዘው ከሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች የፈጠሩት ጥላ ውስጥ የነበረው ኦህዴድ ከጥላው ስር ወጥቶ ጠፋባቸው። ምን ቀራቸው? ምንም! በነገራችን ላይ ኦነግ በጣም ብዙ የትግል አካሄዱ ውስጥ የተንፀባረቁ ትላልቅና መሰረታዊ ስህተቶች ቢኖሩትም (እዚህ መዘርዘሩ ከአጀንዳዬ ያስወጣኛል) መቼም ቢሆን ለደቂቃም የኦሮሞ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር እድልን ከድቶም ሽጦም አያውቅም። ኦህዴድ ይዞት የነበረውን ይህን ክቡር ህዝባዊ ዓላማ ክዶ አማሟቱ ሳይታወቅ እንደ ፀጉራም ውሻ አለሁ እያለ ላይመለስ አሸለበ። የከፈለው ከባድ መስዋዕትነት ተረሳ። ድርጅቱን ለስልጣን ብለው አገር ለሚሸጡ የፖለቲካ ነጋዴዎች አሳልፎ ሰጠ።

የኦህዴድ ዲቃላ ልጅ አፋን ኦሮሞ በመቻሉ ብቻ ለኦሮሞ ይቆማል ብሎ መገመት ስህተት ነው። ይህ ብዙ ጊዜ በሁሉም ትግሎች ታሪክ የተከሰተና የታየ ስህተት ነው። ባንዳዎች በሁሉም የትግል እንቅስቃሴዎች ለስልጣን፣ ለገንዘብ እና ለሌላ ጥቅሞች ለማግኘት ብለው አገራቸውን ህዝባቸውን ቤተሰባቸውንም ጭምር ይሸጣሉ። ከኦህዴድ ወደ ባንዳው ብልጥግና የተካሄዶው ሽግግር የቀለም አብዮት ውጤት ነው። የቀለም አብዮቶኞች የሚያማምሩ ቃላቶችን በመደርደር ቀለም በማንፀባረቅ የህዝብን ቀልብ በመስረቅ፣ በማፍዘዝና በማደንዘዝ እርካብና መንበርን ይዞ ዕድሜ ለማስረዘም ይሞክራሉ። አብይ አህመድ ከኦህዴድ ውጭ በግልፅ ኦሮማራ አደራጁ። በድብቅ ከሃይማኖታቸው የተሳሰረ ማይንድ ሴት የሚባል ፎረም በምህረት ደበበ በተባለ የስነልቦና ሃኪማቸው የሚመራ ድርጅት አላቸው። ሁለቴ ብቻ በግልፅ ሲሰበሰቡ አይተናል። ስልጣን ከመያዛቸው በፊትና ከያዙ በኃላም የምስጋና መድረክ ተዘጋጅቶ ተገኝተዋል። ከዚህ ውጭ አሜሪካ አገር እየሄዱ ከጁሓርና ከግንቦት ሰባት የፈጠሩት ጥምረትም ሌሎች ለስልጣን ሲሉ የተጠቀሙባቸው ድርጅቶቻቸው ናቸው። ከውጭ መንግስታት የተፈራረሙትን የቅጥር ስራቸውም ሌላው ለስልጣን ያበቃቸውና አሁንም በስልጣን እንዲቆዩ እያደረጋቸው ያለ አቅም ነው። ለዚህም ማሳያ ምንም ለውጥ ያላመጣና የአገር ሉዓላዊነትን አሳልፎ የሰጠ ሰው የኖቤል ተሸላሚ ማድረግ በላይ ማረጋገጫ የለም። ይህም አለም ያወቀወ ፀሀይ የሞቆው እውነታ ነው፡፡  


አብይ አህመድ ኦህዴድና አገራችን ለበለፀጉ አገሮች ሽጦ ስለበለፀገ ብልጥግና ፓርቲ ስትሞላቀቅ ደግሞ ፒፒ የምትባል ፓርቲ ፈጠረ። ለውሻ ደስ የሚል ስም ነው ብዬ ውሻዬን ፒፒ ብዬ ስም አወጣሁላት። የሚከለክል ህግ ያለ አይመስለኝም። ህግ በፈረሰበት አገር ደግሞ ስለ ህግ ምን አስጨነቀኝ።

ቸር እንሰንብት እንላቹሀለን እኔና ፒፒ ውሻዬ በጋራ!

(ምንጭ : አይጋ ፎረም )