Monday, 5 November 2018

የፖለቲካ ድብብቆሽ ጨዋታው አሁን ግልፅ እየሆነ ነው

ፍስሃ መረሳ

ገዢ ፓርቲው ኢህአዴግ መምራት አቅቶት በህዝብ ግፊትና ጫና ስልጣኑን ለሌላ ጥገኛ ሃይል ካስረከበ ማግስት ጀምሮ በስመ "አዲስ ለውጥ" እናመጣለን የሚል መፈክር አንግቦ ከህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ኢህአዴግ በቁማር ለማስበበላት ዋና አላማ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው ሃይል እነሆ ድርጅቱ በተለይ ከህወሓት ውጪ ያሉ የግንባሩ አባለት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የቆሙለትን አብዮታዊ ዴሞክራሲ በመተው ወደ ለየለት ጥገኛና ፀረ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ተቀይረዋል ፡፡

የነዚህ ሃይሎች ዋና አለማ ኢህአዴግ ለአመታት የገነባው ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም ስርአት በማፍረስ የራሳቸውን ፍላጎት የሚያሟላ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነፃነት የሌለው እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የውጭ ሃይሎች ፖሊሲ ተከራይቶ የሚኖር ስርዓት ገንብተው ለመቀጠል ያላቸው ፍላጎት ለመተግበር በውጭ ሃይሎች ያልተቆጠበ ድጋፍ ተጠቅመው እነሆ በዚህ አጭር ጊዜ ህገመንግስታዊ ስርአቱን በማፍረስ ጠቅላላ የስርዓት ለውጥ ለማምጣት መጀመሪያ የስርአቱ ባለቤት የሆነው ኢህአዴግ ኦፊሻል ባልሆነ መንገድ እንዲፈርስ በማድረግ ላይ   ናቸው ፡፡

አሁን የቀራቸው ነገር የኢህአዴግ ጠበል ቀምሷልና በቀጣይ እንቅፋት ሊፈጥሩ ይችላሉ የተባሉ በተለምዶ አጋር ድርጅቶች ተብለው የሚጠሩ አናሳ ክልሎች ተራቸው ደርሶ አብዛኛዎቹ ወደ ቤተ መንግሥት በመጥራት ወደዱም ጠሉም ለውጥ መቀበል እንዳለባቸው ካልተቀበሉ ግና ወደ ማጎሪያ ቤት እንደሚወርዱና ያላቸው አማራጭ ቦታቸው ለቀው መደመር ብቻ መሆኑ እስከ ማስፈራራት የሚሄድ ዛቻ እየደረሰባቸው ከስልጣን እንዲወገዱ ተደርጓል ፡፡ ይህ አካሄድ ሰላም ይፈጥራል አይፈጠርም ሌላ ጉዳይ ሆኖ የፌደራል ትእዛዝ በቀጥታ ተቀብለው ማስፈፀም የሚችሉ አሻንጉሊት መንግሥታት ስልጣኑን እንዲረከቡ በማድረግ ለጊዜውም ቢሆን ተሳክቶላቸዋል ሊባል ይችላል ፡፡

ከዚህ በኋላ አገሪቱን ወደ ሚፈልጉት ጥገኛ ስርአት ሙሉ ለሙሉ ለመቀየር በነሱ አስተሳሰብ ሁለት መሰረታዊ ስራዎች መስራት ይጠበቅባቸዋል ፡፡ የቅደም ተከተሉ ጉዳይ ትተን ሁለት የቀሩ ስራዎች ብለው እነሱን ለመፈፀም ካላቸው ዝግጅት አንፃር ሲታይ አንዱ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዋና አቀንቃኝና በቀጣይ ዋነኛ ስጋት ይሆናል ያሉት ድርጅት ህወሓት ቀስ በቀስ በማዳከምና ብቻውን እንዲቀር በተለያዩ ፀረ ሰላም ሃይሎች ጥቃት እንዲደርስበትና እሱን ከጨዋታ ውጭ በማድረግ ያሰቡትን የስርዓት ለውጥ ለማድረግ ምቹ ሆኔታ መፍጠር የሚል አላማቸው ለማሳካት አሁን ያለ የሌለ አቅማቸውን በማሰባሰብ በተለይ ነፍጠኛው ሃይል ቅድሚያ እንዲሰለፍ በማድረግ የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ላይ ይገኛሉ ፡፡

ሌላው የቀራቸው ዋነኛ ስራ ህገመንግስታዊ ስርአቱን የመጠበቅ ሃላፊነት የተሰጠው የአገር መከላከያ ሃይል ሙሉ ለሙሉ የነሱ መሳርያና ማስፈፀሚያ እንዲሆን ከተፈለገ አሁን ያለው አቋሙና በተለይ አመራሩ ለነሱ በሚመች መንገድ ለማስተካከል እንደገና አዲስ ስም እየሰጡ ፈርሶ እንዲደራጅ በማድረግ ሰራዊቱን በመቆጣጠር ስልጣናቸውን አደላድለው ለመያዝ ሰፊ ጥረት እንደሚያደርጉ ግምት ብቻ ሳይሆን እስካሁን ያለቸው እንቅስቃሴም ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ፡፡

ሰለዚህ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አገሪቱ ወደ ማትወጣው ቀውስ እየገባች ነው ፡፡ ክልሎች በራሳቸው ዓቅም መምራት ስለማይችሉ ድምር ውጤቱ እርስ በርሳቸው መናቆርና መጠላለፍ እንደሚሆን አሁን የአማራ ክልል መንግሥት በማንነት ጥያቄ ስም እየፈጠረ ያለው ሁከትና ግርግር በቂ ማሳያ ነው ፡፡ እና የነበረው የፖለቲካ ድብብቆሽ አሁን ግልፅ ስለሆነ ይህን የጥፋት ስልት ለማክሸፍ ዓቅማችን በማሰባሰብ መጨረሻው እንደ ትናንቱ በነሱ ሸንፈት እንዲጠናቀቅ በፅናት መታገል ይጠበቅብናል ፡፡