Monday, 3 December 2018

“እኛ ምን ላይ ነን?”

ከፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

የሀገራችን የሥልጣን ፖለቲካ በምን? እንዴት? ስለምን? በማን እንደተሞላ? አኗኗራችን ምስክር ነውና - ከሠለጠነው ዓለም አንጻር ምን ይመስላል? ምን ላይ ነን? ከመሰሎቻችን አንጻር ምን ላይ እንገኛለን? ልዩነቱስ ላይ የጋራ ግንዛቤ አለን? በልዩነቱስ የተነሣ ቁጭት መፍጠርና ማንባት ችለናል? የሚለውን በስፋት ለመመልከት ይቻል ዘንድ ከማዕቀፍ አንጻር ያሉ ዋና ዋና ነጠቦችን እንመልከት፡፡

  የሠለጠነው ዓለም ስንል ለዚህ ጽሑፍ ፖለቲካቸው ከሥልጣን ፖለቲካ ይልቅ ዕሳቤን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያለባቸውን፤ ከሴራ ይልቅ ግልጽነትን - ከመሰይጠን ይልቅ መሠልጠንን፤ በዘመኑ ከመዋጀት ይልቅ ዘመኑን የሚዋጅ እንቅስቃሴ ያለባቸውን፤ ከወረኛነትና ከተራ ጀብደኝነት ይልቅ በርዕዮትና በአርቆ ማሰብ ላይ የተመሠረተ - መሠረታዊ የሕግ የበላይነት፣ የፍትህና የነጻነት ጉዳይ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የማይገባባቸውን (ያልገባባቸውን) ሀገራት ማለታችን ነው፡፡

   በመኾኑም ንጽጽራችን ከእምነት (ከአስተሳሰብና አመለካከት)ና ከእውቀት (ስልትና ስትራቴጂ) በላይ በዋናነት ከተግባር እንቅስቃሴ (ከድርጊት) አንጻር ያለውን መሠረት ያደረገ ይኾናል፡፡

 ይኸውም፡-

አንደኛ፡- አጠቃላይ እውነታ፤
እኛ በዓለም እጅግ ድሃ የድሃ ድሃ ተብለው ከሚፈረጁ፤ ከእርዳታና ብድር ውጭ መኖር የማንችል፣ ከሩብ በላይ የሚኾነው ሕዝብ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚኖር፣ ከዛ የማይተናነስ የሥራ አጥ ቁጥር ያለባት፣ ዛሬ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን እንኳ ሳይቀር መሠረታዊ ፍላጎት የሚባሉት ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ አልባሳት - - - ጥያቄ የኾኑብን ኾነን ሳለ ፖለቲካችን፣ ሀሳባችንና እሰጣ ገባዎቻችን ግን እነዚህን ጥያቄዎች ከሚመልስ ይልቅ ከዚህ በእጅጉ በራቀ ኹኔታ ላይ ያለ ነው፡፡

  ወሬዎቻችን፣ ክርክሮቻችን፣ ትኩረታችን፣ አሰጣ ገባዎቻን፣ ምክሮቻችን፣ አድናቆታችንና ወቀሳችን፣ ቃለ መጠይቆቻችን፣ ፍላጎቶቻችን - - - በአብዛኛው ምን ላይ ያተኮሩ ናቸው? ብዙ ጊዜዎቻችንን የምናጠፋው በምን ላይ ነው? ዕውን ካለንበትና መኾን ካለበት አንጻር የሚስማሙና የሚጣጣሙ ናቸውን? ለምን እንደዛ ሊኾን ቻለ?   

 

ሁለተኛ፡- ቁመናችን አኗኗራችንን ይመስላል፤

   የኛ ኹለንተናዊ ነባራዊ ኹኔታዎች በላቀ ሀሳብና ዕሳቤ ላይ ተመስርቶ ሳይኾን ስሜትና አስተያየት የሞላበት እንደኾነ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በዚህም ኹለንተናዊ ነገሮችን ለመገመት፣ ለመተንተንና ሞያዊ ምክሮችን ለመስጠት አስቸጋሪ ከመኾኑም ባሻገር በውስጡ ማስመሰል፣ ወረኛነት (ወረተኛነትን)፣ ሃሰተኛነትና ሴራን በእጅጉ ባለቤት ማድረግን በሚጠይቀው የሥልጣን ፖለቲካችን ውስጥ ምክንያታዊ ትንታኔዎችን ማቅረብ እጅግ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ በምክንያት ኹለንተናዊ ሂደት ውስጥ የማያልፍን ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ በኹለንተናዊ አመክንዮ መፈተሽ ከባድ ነው፡፡

   ኹለንተናዊ አኗኗራችን የኹለንተናዊ አስተሳሰብና አመለካከት ደረጃችን ማሳያ ነው፤ ቁመናችን የዛ ሂደት እንቅስቃሴ ውጤት ነው፡፡ ሰው ያልያዘውን ኬት ያመጣል? ሕዝብስ ያላዳበረውን እንደምን ባለቤት ሊኾንና የዛ ፍሬ ተቋዳሽ መኾን ይችላል?

ሶስተኛ፡- ሕልውና ራሱ ጥያቄ ነው፤

   ዛሬ በሀገራችን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያልገባ ምን አለን? ተዘዋውሮ የመስራት መብት፣ ሰላም፣ ፍትሕ፣ የሕግ የበላይነት፣ ተስፋ፣ መቻቻል፣ አስተዳደር፣ ነጻነት፣ - - - ወዘተ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ነው፡፡ እንደምን እነዚህን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ከቶ በነሱ ቅድመ ኹኔታ ላይ የተመሰረቱ ተግባራት ማከናወን ይቻላል? እንደምንስ ሕልውና በራሱ ጥያቄ በኾነበት አግባብ ስለሌሎች ጉዳዮች ማንሣት ይቻላል?

አራተኛ፡- የጦርነት ወሬ ተበራክቷል፤

    በየቦታው የሰዎች መፈናቀል ተበራክቷል፡፡ የሕግ የበላይነት ጉዳይ በአደባባይ የሚታይ ነው፡፡ በየቦታው የምንሰማቸው የጦርነት ወሬዎች፣ መፈክሮች፣ ሽለላዎችና እሰጣ ገባዎች የሠለጠነው ዓለም ከብዙ ዓመታት በፊት ተሻግሮታልና ከነሱ ጋር ተወዳዳሪ መኾን የቀን ቅዠት ነው፡፡

   የሠለጠነው ዓለም በስፔስና ቴክኖሎጂ ውድድር ውስጥ ነው - እኛ ግን ገና ከመሬት ፖለቲካ አልተላቀቅንም፤ ዓለም ከአሽሙርና ከኮስሞቲክስ ፖለቲክስ ተሻግሯል - እኛ ገና ከአሽሙርና ከኮስሞቲክስ የፎቶና የጥቅስ የሥልጣን ፖለቲካ ገና አልተላቀቅንም፡፡ የሠለጠነው ዓለም ነገን ለመቆጣጠር ይተጋል - እኛ ገና ከታሪክ እሰጣ ገባ ነጻ አልወጣንም፡፡ የሠለጠነው ዓለም ለተግባራት ፍሬ ሌት ተቀን ይሮጣል - እኛ ጋር ገና ለወሬ፣ ለአሽሙር፣ ለፎቶና ሕዝብ ከሚያስፈልገው ይልቅ ሕዝብ የሚፈልገውን መርጦ ከመናገር የሃያኛው ክፍለ ዘመን ውዳቂ የሥልጣን ፖለቲካ ፕሮፕጋንዳ ቅኝ ግዛት ነጻ አልወጣንም፡፡ 

   የሠለጠነው ዓለም ከመግለጫ የሥልጣን ፖለቲካ ከተላቀቀ ዓመታት አልፈዋል፡፡ እኛ ጋር መግለጫው ራሱ ሥራ ኾኗል፡፡ ሌሎች ከገዥዎችና ከአስተዳዳሪዎች ወደ መሪዎች ተሻግረዋል - እኛ ገና ከገዥያዊና አስተዳደርያዊ አስተሳሰብና አመለካከት ከፍ አላልንም፡፡ 

  ወሬና ወረኛነት ላይ የተንጠለጠለ ድጋፍና ተቃውሞ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ሙላት ነው፤ የኮስሞቲክስ የፎቶ ውድድር አንድ ዋነኛ የፕሮፕጋንዳ መሳሪያ ነው፤ በአመክንዮ ላይ ያልተመሰረቱ ትርጉም አልባ የቃላት ክምር ደግመውና ተደጋግመው አትርሱኝ - አስታውሱኝ - ከጎኔ ኹኑ የመባያ ትልቅ መሣሪያ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ የ”ጀግንነት” መለኪያ እርሱ ኾኗል፡፡

አምስተኛ፡- ያለሽ መስሎሻል ግን ተበልተሸ አልቀሻል፤

  ሀገራችን ያለች ቢመስለንም በብዙ መልኩ ተበልታለች፡፡ ሀገራዊ ዕሴቶች በተለይም እንግዳ ተቀባይነት፣ ፍትህ፣ ፈሪሃ ፈጣሪ፣ ሞራል፣ ቃልን ማክበር፣ ታማኝነት፣ መረዳዳትና መደጋገፍ የተሰኙ መገለጫዎቻችን እጅግ በከፋ አደጋ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በብዙ ቦታዎች አብሮ መኖር በራሱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቷል፡፡

 ብዙ ነገሮች ተከስተዋል ነገር ግን ተጠያቂነት ከመግለጫ ጋጋታነት የዘለለ አይደለም፡፡ ብዙ ነገሮች ተፈጽመዋል ነገር ግን ፈጻሚዎች ዛሬም ማንነታቸው በግልጽ አይታወቅም፡፡ ብዙ ነገሮች ሲኾኑ ስለመኾናቸው እንጂ የኾኑበት ምክንያት፣ መንስኤና ውጤት ትርጉም ባለው መንገድ ተተንትነው አይቀርቡም፡፡

ስድስተኛ፡- አርቆ ማሰብ ከራቀን ዋል አደር ብሏል፤

   አርቆ ማሰባችን እጅጉን ኃላ ቀር ከመኾኑ የተነሣ ተሹሞ ወር ያልሞላው ሌላ ሹመት ይሰጠዋል፡፡ ገና ከመንግሥት ሚንስተር መሥሪያ ቤት ማፍረስና መገንባት ነጻ አልወጣንም፡፡ ዜናዎቻችን በአብዛኛው ትርኪ ምርኪና ትርጉም አልባ ጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡

  አርቆ ማሰብ የዓመታት ዕቅድ ማውጣትን እርሱንም በግብ (በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም)፣ ራዕይ (ነጠላና አጠቃላይ) እንዲሁም ከዓላማና ተልዕኮ ጋር አስተሳስሮ ማቅረብ የሚገባ ቢኾንም ምን ላይ እንዳለን መዘርዘር ለቀባሪ ማርዳት ነው፡፡

ሰባተኛ፡- የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት፤

  ምንም እንኳ የታዳጊ ሀገራት የሥልጣን ፖለቲካ ፍጹም ከቀጥተኛና ተዘዋዋሪ የውጭ ጣልቃ ገብነት ነጻ ይኾናል ብሎ ማሰብ ፍጹም በዓለም ተወዳዳሪ የሌለው ጅልነት ቢኾንም በአንጻራዊ መልኩ መታገልና ቢያንስ ቢያንስ በብሔራዊ ጥቅሞች ላይ አቋም መያዝ የሚገባ ቢኾንም ተቀናቃኝና ተወዳዳሪ የሚባሉ ሀገራት እንኳ ሳይቀሩ በኛ ሀገር ነባራዊ ኹኔታ ከኛ በላይ እጅጉን ደስተኛ ሲኾኑ ስንመለከት ከማዘን ውጭ ምን ይደረጋል?

  እንደሀገር ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ተቀናቃኝህ ባንተ ኹለንተናዊ ነባራዊ ኹኔታ ደስተኛ ከኾነ በትንሹ ጥቅሙ እንደተከበረለትና እንደሚከበርለት ማመኑን ለመረዳት ሰው መኾን ብቻ በቂ ነው፡፡

   ጠቢቡ ሰለሞን “ልጄ ሆይ! እጅግም ጠቢብ አትሁን - እንዳይገሉህም!!!” የሚለው ህያው ጠቢባዊ ምክር ታሳቢ በማድረግ ምን ላይ እንደሆንን በማስተዋል በማዕቀፍ ደረጃ እነዚህን ሰባት ነጥቦች ተመልክተናል፡፡

   የሀገራችን የሥልጣን ፖለቲካ ከይሁዳዊ ባሕሪያትና ጠባያት ወደ ትክክለኛ ሕዝባዊ (አብርሃማዊ) ባሕሪያትና ጠባያት ካልተሻገረ በቀር ኹለንተናዊ መሠረታዊ ለውጥ የማምጣትም ኾነ የመሠልጠን ሕብረተሰባዊ ጉዞ ወደ ኃላ እንጂ ወደ ፊት እንደማይጓዝ መረዳት አስፈላጊ ይኾናል፡፡ ስለኾነም ኢትዮጵያውያን ያለንበትን ነባራዊ ኹለንተናዊ ነባራዊ ኹኔታ ትርጉም ባለው መንገድ ተረድተናልን? ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!