ከገራገር
ዘበርጋ
መግቢያ፡
ባሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ
ላይ እየታየ ያለው እንቅስቃሴ
ወይም ለውጥ ላንዳንዶቻችን
ጉዳዩን በየዋህነት ከተመለከትነው
ባንዳንድ ወገኖች እንደሚነገረውና
ተቀባዮቻቸውም ለራሳቸው
ጠቀሜታ ብለው ጉዳዩን
እያሽሞነሞኑ እንደሚገልጹት
‹‹ከእባብ ፍጡራን መካከል
እርግቦች ተፈጥረው ነው!››
በሚል እሳቤ በኢሕአዴግ
ውስጥ የተፈጠሩት ‹‹ለውጥ
ፈላጊዎች!›› የእርግብ እንቁላሉን
ሰብረው እንደወጡና ለውጡን
እንዳመጡ አድርገን እንገምት
ወይም እንደናገር ይሆናል፡፡
ለውጡ እንዴት መጣ በሚል
እውነታውን እናውጣው ከተባለ
ግን ‹‹እባቦችም አልነበሩም!
ከእባቦች መካከልም እርግቦች
አልተፈጠሩም! የተሰራው
ነገር በኢሕአዴግ ምክር
ቤት ውስጥ የሊቀመንበር
ምርጫ ሲደረግ በ11ኛው ሰዓት
የፓርቲዎችና የአባላቶቹ
መከዳዳትና መቧደን በመከሰቱ
ምክንያትና ውጤቱም ዶ/ር
አብይ አህመድን ሊቀመንበር
አድርጎ በመውጣቱ ብቻ
ነው፡፡
1.
የአቶ ኃይለማርያም
ደሳለኝ ሁለንተናዊ ክህደት፡
የቀድሞው ጠቅላይ
ሚኒስትርና የኢሕአዴግ
ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም
ደሳለኝ ስልጣናቸውን ከመልቀቃቸው
በፊት የስንብት ጥያቄ
ለፓርቲያቸውና ለመንግስታቸው
አቅርበው ሲያበቁ በዛች
የአንድ ወር የስንብት
ጊዜ ውስጥ ስልጣኑን ለማን
ማስረከብ እንዳለባቸው
ሲያውጠነጥኑና ከድርጅታቸው
አባላት ጋር ሲመክሩ እንደከረሙ
እሙን ነው፡፡ በዚህን
ወቅት የነበራቸው አቋም
የደኢሕዴን አባል በመሆናቸውና
ምናልባትም ቀጣዩ ሊቀመንበር
ከደኢሕዴን መሆን ካለበት
አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እንዲመረጡ
ለማድረግ ከአባላቶቻቸው
ጋር ሲነጋገሩና ሲማከሩ
እንደነበረ ግልጽ ነው፡፡
ምንም እንኳን የአቶ ሽፈራው
ሽጉጤን ወደ ስልጣን መምጣት
ባይዋጥላቸውም አቶ ኃይለማርያም
ከደኢሕዴን ተፈጥረው በዛው
መሰላል አድርገው ወደ
ስልጣን ወጥተው ሲያበቁ
በወቅቱ ‹‹ሽፈራው አይመረጥም!››
ለማለት የሚያስችላቸው
ግልጽ አቋም መውሰድ አይችሉም
ነበር፡፡ ስለሆነም እስከመጨረሻው
11ኛ ሰዓት ድረስ ለሽፈራው
ሽጉጤ እንደቆሙ በመምሰል
አቋመቸውን ሲያራምዱ ከቆዩ
በኃላ ውስጥ ውስጡን ግን
እንደነአምባሳደር ተሾመ
ቶጋን፡ እንሙፈሪያት ካሚልን፡
መለስ ዓለምን የመሳሰሉ
የቅርብ አድማጮችን በመስበክ
‹‹ኦሮሞን ነው የምንመርጠው፡
ዓብይን ነው የምትመርጡት!››
እያሉ በመስበክና በማሳመን
ሽፈራው ሙሉ የደኢሕዴን
አባላት ድጋፍ እንዳይኖራቸው
አድርገው ሂደቱን ቀይረውታል፡፡
በዚህ ምስጢራዊ ተግባራቸውም
ከ45ቱ የደኢሕዴን ተወካዮች
ከ18 እስከ 21 የሚሆኑትን ከጎናቸው
ለማሰለፍ ችሏል፡፡ አቶ
ኃይለማርያም ይህንን ድርጊት
ሲፈጽሙ ላንዳንዶቹ አባላት
በቀጣይ ጊዜ ስልጣን እንደሚሰጣቸው
ተስፋ በመስጠት፡ ላንዳንዶቹ
ደግሞ ‹‹ኦሮሞ ስላመጸ ሰላም
ሊመጣ የሚችለው ኦሮሞን
የመረጥን እንደሆነ ነው!››
የሚል ማስፈራሪያና ከድርጅቱ
መርሕ ውጭ የሆነ የሊቀመንበር
አመራረጥ ስልትን በመከተል
እንደነበር ይነገራል፡፡
አቶ ኃይለማርያም
ደሳለኝ በ11ኛው ሰዓት ቀደም
ብለው ከጓሮው ሆነው በተስማሙት
መሰረት አቶ ደመቀ መኮንን
የሊቀመንበርነቱን ስልጣን
እንደማይፈልጉ እንዲያስታወቁ
ከተደረገ በኃላ ግማሹ
የምክር ቤት አባል ዶ/ር
ዓብይ አሕመድን እንደሚመርጥ
እርግጥ ነበርና (ብአዴንና
ኦሕዴድን ተደምረው ማለት
ነው) በዚህን ወቅት ምስጢራዊ
ድምጽ ሲሰጥ በምስጢር
ያደራጇቸውን የደኢሕዴን
አባል የምክር ቤቱ ተወካዮች
ድምጻቸውን ለዶ/ር ዓብይ
በመስጠት በ108 ድጋፍ ሊቀመንበር
ሆነው እንዲመረጡ ሲያደርጉ፡
የራሳቸው ፓርቲ ተወካይ
የሆኑትና ለሊቀመንበርነት
የተወዳደሩት አቶ ሽፈራው
ሽጉጤ ያገኙት የድጋፍ
ድምጽ ግን በ59 ብቻ ተወስኖ
ውጥናቸው ውድቅ ሆኖ ሊቀር
ችሏል፡፡ የአቶ ኃይለማርያም
ክህደት እንግዲህ ከዚህ
ተግባራቸው ይጀምራል፡፡
የደኢሕዴን ሊቀመንበር
የሆኑትንና የራሳቸው እናት
ፓርቲ ሊቀመንበርን ብቻ
ሳይሆን ክህደቱ ከዚያም
በላይ አንድምታ ያለው
የፓርቲ፡ የፖለቲካ፡ የመስተዳድርና
የማህበራዊ ክህደትም ሆኖ
ስለተመዘገበ የኃላ ኃላ
በደቡብ ብሄር፡ ብሄረሰቦችና
ሕዝቦች ክልል ውስጥ ረጭቶት
ያለፈው አቧራ ግን እስካሁን
ድረስ በየፈርጁ እየቦነነ
ሕዝቦችን እያነሳሳና ብሎም
ለግጭት እየዳረገ ይገኛል፡፡
2.
የደኢሕዴን መፈረካከስና
የኢሕአዴግ መዳከም፡
የአቶ ኃይለማርያም
ክህደት ቁጥሩ 56 የሆነውን
የደቡብ ብሄር፡ ብሄረሰቦችና
ሕዝቦችን ይወክል የነበረውን
ፓርቲ ማለትም ደኢሕዴንን
ፍርክስክሱ እንዲወጣ አድርጎት
ይገኛል፡፡ ደኢሕዴን ለስሙ
አለ ይባላል እንጂ በተግባር
ፈርሷል፡፡ ባሁኑ ወቅት
በክልሉ ሰባት ዞኖች የክልል
ደረጃ ስልጣን እንዲኖራቸው
በምክር ቤቶቻቸው በኩል
አድርገው ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡
በመሰረቱ እነዚህ የዞን
ምክር ቤቶች የያዙዋቸው
አባላት በሙሉ የደኢሕዴን
አባላት ናቸው፡፡ ሆኖም
ሐዋሳ ለተቀመጠው የክልሉ
ምክር ቤት ባለማዳመጥና
ትኩረትንም ባለመስጠት
ራሳቸው ዞኖቹ የራሳቸው
ስብሰባዎችን እየጠሩ ውሳኔዎቻቸውን
አስተላልፏል፡፡ ውሳኔያቸው
ደግሞ በሕገ መንግስቱ
አንቀጽ 47 መሰረት የተደገፈ
ስለሆነ የክልሉ ምክር
ቤት በተሰጠው የአንድ
ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ
በየዞኖቹ ሕዝበ ውሳኔ
የማካሄድና ሂደቱን የመምራት
ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ ባሁኑ
ወቅት የሲዳማ፡ የወላይታ፡
የጉራጌ፡ የሐዲያ፡ የከምባታ፡
የከፋና የቤንች ማጂ ዞኖች
ውሳኔዎቻቸውን አስተላልፈው
ጥያቄያቸውን ለክልሉ ምክር
ቤት በማስተላለፍ ላይ
ይገኛሉ፡፡ የክልሉ መንግስት
‹‹አረ ረጋ በሉ፡ አካሄዱ
እንዲህ መሆን የለበትም!...››
ቢልም ሰሚ አላገኘም፡፡
ለነገሩ የክልል ጥያቄው
በዚህ ብቻ ያበቃል ተብሎም
አይገመትም፡፡ አሁንም
የክልል ጥያቄን ለማቅረብ
በመዘጋጀት ላይ የሚገኙ
ዞኖች እንዳሉም ይነገራል፡፡
ከዚህ ሂደት በኃላ
ደኢሕዴን አንድ ፓርቲ
ሆኖ ለመቀጠል አይችልም፡፡
ድሮ ሲመሰረትም 17 የሚሆኑ
የብሄር፡ ብሄረሰብ ፓርቲዎች
ባንድ ላይ ተዋህደው ነበር
የመሰረቱት፡፡ አሁን ያለው
ሂደትም ድርጅቱ ተፈረካክሶ
ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው
ድርጅቶች ሊመሰረቱ ይችላሉ፡፡
እንዲዚያ የሚሆን ከሆነ
ደግሞ በኢሕአዴግ የሚኖራቸው
ውክልና ምን ሊሆን እንደሚችል
መገመቱ ያስቸግራል፡፡
ኢሕአዴግ ራሱስ ቢሆን
አሁን ባለበት ቁመና አንድ
ፓርቲ ሆኖ ይቀጥላል ወይ?
የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ
ሆኖ፡፡
እንግዲህ አቶ ኃይለማርያም
ደሳለኝ በኢሕአዴግ ውስጥ
በፈጸሙት ክህደት ደአሕዴንን
ብቻ ሳይሆን ያፈረሱት
የክልል መስተዳድሩንም
ጭምር ነው እንዲፈርስ
ሁኔታውን አመቻችተው ከስልጣን
የወረዱት፡፡ እነዚህ አሁን
የክልል ጥያቄ በማቅረብ
የደቡብ ክልልን ለማፍረስ
እያቆበቆቡ የሚገኙት የዞኖች
የክልል ጥያቄዎችና እንቅስቃሴዎች
መነሻቸው አቶ ኃይለማርያም
እነአቶ ሽፈራውን ከድተው
የራሳቸውን ክብርና ዝና
ለማመቻቸት ከተንቀሳቀሱበትና
ሴራ ከጎነጎኑበት ሰዓት
የሚጀምሩ ናቸው፡፡ አቶ
ኃይለማርያም ለፈጸሙት
ክህደት ክብርና ሽልማት
አግኝተውበት ሊሆን ይችላል፡፡
ሆኖም ያ ክብርና ሽልማት
በደቡብ ሕዝቦች ክልል
ኪሳራ የተገኘ መሆኑን
ሊጤን ይገባል፡፡
3.
ክህደቱ ያስከተለው
ማሕበራዊ ቀውስ፡
አቶ ኃይለማርያም
ስልጣን ካስረከቡና የኢሕአዴግ
አዲስ አመራር ከመጣ በኃላ
በደቡብ ክልል ውስጥ ባሉት
ዞኖችና ወረዳዎች ብሎም
ቀበሌዎች ተደጋጋሚ ግጭቶችና
የሰላም መደፍረስ ሁኔታዎች
በመከሰት ላይ ስለሚገኙ
በርካታ ሕዝብ ለሞትና
ለመፈናቀል እየተዳረገ
ይገኛል፡፡ በሐዋሳ ከተማ
አጋጥሞ የነበረው የሕዝቦች
ግጭት አንዱ ማሳያና ምናልባትም
ከፍተኛው ግጭት ሊባል
የሚችል ነው፡፡ ከዚያ
በመቀጠልም በጉራጌ፡ በወላይታ፡
በጌዴዎ፡ በጋሞጎፋ፡ በማጂ፡
ወዘተ… አካባቢዎች የተለያዩ
ግጭቶች በማጋጠማቸው ምክንያት
በርካታ ሰዎች ለሞትና
ለመፈናቀል ተዳርጓል፡፡
እንዚህ ግጭቶች በገዢ
ፓርቲው በተፈጠረው ክፍፍልና
ከዚያም በመቀጠል በዞኖችና
ወረዳዎች አካባቢ ከተከሰተው
የአስተዳደር መዳከምና
ሕገመንግስቱን በተለያየ
ፈርጅ የመዳፈር እንቅስቃሴዎች
የመጣ እንደሆነ ይገመታል፡፡
የፓርቲው ሚናና የአስተዳደሩ
ተግባር ሲዳከም ፖሊስ
ስራውን መስራት ይተወዋል፡
ፖሊስ ራሱ በወጣቶች ይደፈራል፡
ፖሊስ ሲደፈር ዓቃቢ ሕግና
ፍርድ ቤቶችም ክብር የማይሰጣቸውና
ለውሳኔያቸውንም ያለመገዛት
አባዜ ይሰፍናል፡፡ እነዚህ
አካላት ስራቸውን ማከናወን
ሲያቅታቸው ደግሞ ሕጉ
ወደ ግለሰቦች እጅ ይገባና
የደቦ ወይም የመንጋ ፍርድ
ሁሉ በመንደር ጎረምሳ
ሲፈጸም ይውላል፡፡ ዜጎች
ሕይወታቸውና ንብረታቸው
አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡
ባሁኑ ወቅት በደቡብ ክልል
ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ
አብዛኛው አካባቢ እየተፈጸመ
ያለው ድርጊት የዚህ ሂደት
አንዱ ማሳያ ሆኖ ይገኛል፡፡
የአቶ ኃይለማርያም
ትሩፋት እንግዲህ በደቡብ
ብቻ ተወስኖም አልቀረም፡፡
አገሪቱንም የሚያስተዳድረው
ኢሕአዴግን ከማዳከሙም
በላይ የፌዴራልና የክልል
መንግስታትንም የዚያኑ
ያህል ተዳክመው ይገኛሉ፡፡
የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች
ባሁኑ ጊዜ ባገራዊ ጉዳዮች
ላይ ቁጭ ብለው ተነጋግረው
መፍትሔ የሚቀይሱበትና
ወደ ተግባር የሚገቡበት
አካሄድ ብዙም አይታይም፡፡
ባንድ ላይ ሆነው አገርን
እየመሩ ስለመሆናቸው በሚያጠራጥርና
ግራ በሚያጋባ ሁኔታ በየክልላቸው
እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡
ይህ አካሄድ ለአገሪቱ
መጻኢ ሕልውና አደገኛ
ከመሆኑም በላይ በጊዜው
ካልተስተካከለ ወዳልተፈለገ
ግጭትና መበታተንም ሊያደርሳት
ይችላል፡፡ ታዲያ ለዚህ
ሁሉ ኃላፊነት ወስዶ መስራት
የሚኖርበት አሁንም አገሪቱን
በማስተዳደር ላይ ያለው
ኢሕአዴግ ነው፡፡ አቶ
ኃይለማርያምን በሚመለከት
ላሁኑ ከተጠያቂነት አምልጠው
በክብር የጡረታ ጥቅማጥቅማቸውን
እያጣጣሙ ሊሆኑ ይችላል፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ለተፈጸሙ
በደሎችና ለተከሰተው ቀውስ
ግን በተለይም በደኢሕዴን
ላይ ለፈጸሙት ክህደት
አንድ ቀን የሚመለከተው
አካል ይጠይቃቸው ይሆናል፡፡
(ምንጭ: ዓይጋ ፎረም)