Friday, 29 November 2019

“27 ዓመት” ታሪክን የማጠልሸት እና የታሪክ ቦምብ ቀበራ

ክፍላይ ገብረሂወት (kflay77@gmail.com, @kfloma)

ሰዎች ታሪክ የኣሸናፊዎች ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ይሄንን ኣባባል ኢትዮጵያ ዉስጥ ተቀባይነቱ ኣጠራጣሪ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ዉስጥ ታሪክ የኣሸናፊዎች ሳይሆን፣ ብዙ ግዜ የጸሓፊዎች ነው፣ ምናልባት ኣሸናፊዎች ነው የሚጽፉት ካልተባለ። ኣሸናፊ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ለምን ታሪካቸው ኣይጽፉም? የእኔም ጥያቄ ነው።

ይሄንን ለማወቅ በትንሹ ከዘመነ-መሳፍንት ዉድቀት በኋላ ከአጼ ቴዎድሮስ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚንስተር መለስ ዜናዊ የተጻፉ ታሪካዊ መጻሕፍቶች ብንመለከት ይህንን ግልጽ ያደርጉልናል። ብዙ ጊዜ እንደ አጼ ዮሃንስ እና ጀ/ኣሉላ ኣባነጋ የመሳሰሉት የሀገር ባለዉለታዎች እና ጀግኖችን ታሪካቸዉን የተጻፈበት መንገድ ስናጤነው ልዩነቱ ፍንትው ብሎ ይታየናል። አጼ ዮሃንስ ለሀገራቸው ሲሉ በመተማ ሰማዕት ሲሆኑ ታሪክ ጸሃፊዎቹ ግን ራሳቸው በሰሩት ስህተት እንደሞቱ ለማስመሰል የሚጓዙት ርቀት ማየት ይቻላል። በኣንጻሩ ደግሞ የሀግር ከሃዲዎችን ከጎንደር ወደ ጎጃም እና ሸዋ መመለሳቸው ተገቢ እንደነበር ለማሳየት ይሞክራሉ።

በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ዕድገት በጣም ቁልፍ ሚና መጫውት የሚችሉትን ኤርትራ፣ጅቡቲ እንዲሁም በከፊል ኦጋዴን በፈቃደኝነት ሸጠው ሲያበቁ ጦሱ በእጅጉ ሀገርን ሲጎዳ ሀላፊነት ከመውሰድ ይልቅ ጥፋቱ ባለቤት ይፈለግለታል እንጂ ሀገር ሻጮቹ ሁሌም ቢሆን ጀግኖች ናቸው። ምድሪ-ባሕሪን (የኣሁኗ ኤርትራ) ሸጠው ሲያበቁ ወያኔ ገንጣይ በማለት ታርጋ ሲለጥፉ ትንሽ ኣይሰቀጥጣቸዉም፣ እንዲሁም የጅቡቲን ስም ማንሳት ኣይፈልጉም። በተጨማሪም ሻዕብያ ከህወሓት በፊት 13 ዓመታት የተዋጋው ለየትኛው ጽድቅ እንደነበር እንኳን መጥቀስ ኣይፈልጉም። ሻዕብያም ከህወሓት በፊት በ13 የትግል ዓመታት የትኛው የኤርትራ ክፍል ነጻ እንዳወጣ ኣይነግሩንም።

ብርዥዋው አጼ ሃይለስላሴ ህዝብ ሲራብ የውሾቻቸው ልደት ማክበራቸው እና ከፈረንሳይ ኣስር ሺዎች ኣውጥቶ ኬክ ገዝተው ሲዝናኑ ህዝባቸውን መርሳታቸዉን ሳይሆን ጃማይካ ሂደው ዝናብ ማስዘነባቸው፣ በስማቸው ዩኒቨርሲቲ ማስገንባታቸው እና ብጹእነታቸውን ነው የሚግቱን። ኣብዛኞቹ “ኢትዮጵያውያን ታሪች ጸሃፊዎች” እንዲህ ናቸው።

ሰው-በላው እና ፈርጣጩ መንግስቱ ሃ/ማርያም በሰዓታት ውስጥ ብቻ በሓውዜን ከ2,500 በላይ ንጹሃን ዶግ-ዐመድ ሲያደርጋቸው ለኣብዛኞቹ “ኢትዮጵያውያን ታሪክ ጸሃፊዎች” መንጌ ቆራጥ እና በሀገር ኣንድነት የማይደራደር ጅግና ነው፣ አንድ ኣንዶቹ እማ የክብር ሐወልት ቢሰራለት ሁሉ በደስታ ጮቤ ይረግጣሉ። ምክንያቱም የአብዛኞቹ “ኢትዮጵያውያን ታሪክ ጸሃፊዎች” መታወቅያ ይህ ነውና።

የአብዛኞቹ “ኢትዮጵያውያን ታሪክ ጸሃፊዎች” ዓላማ የእኔ መንግስት ብሎ ካሰቡ ወርቅ እየቀቡ ኣስፈላጊ ሆኖም ሲገኝ የሃይማኖት መማርያ ዉስጥ እየከተቱ አምላክ ኣስመስለው ሲስሉት፣ የእኔ ኣይደለም ብለው ያሰቡትን ደግሞ ጥላሸት በመቀባት ጭራቅ አድርገው ሲስሉት እና ለኢትዮጵያ ውድቅት ተጠያቂ ለማድረግ ሲፍጨረጨሩ ይታያሉ። ይህ እጅግ አደገኛ የሆነ የረጅም ጊዜ ቦምብ እየቀበረ የእኔ ታሪክ ከኣንተ ታሪክ የተሻለ ኣንጸባራቂ ነው የሚል እንድምታ እንዲኖረው ያደርጋል።

ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ የሚስተጋባው 27 ዓመት የሚል ኣሰልቺ፣ ምክንያታዊነትን ቀርጥፎ የበላ፣ የተጎታችነት ማሳያ የሆነ እንዲሁም የእልቂት ኣታሞ የሚመታበት የሚድያዎች ድምጽ ከላይ የተገለጸውን “የኢትዮጵያውያን ታሪክ ጸሃፊዎች” የሚያስቀጥል ኣካሄድ እንደሆነ ኣያወላዳም። ለ“ኢትዮጵያውያን ታሪክ ጸሃፊዎች” እና ኣጫፋሪዎቻቸው ህወሓት ትግል ውስጥ እያለ ባንዳ ነው፣ እንደ ኮሶ እየጎመዘዛቸው 4 ኪሎ ከገባ በኋላም ባንዳ ነው። ምክንያቱም በደማቸው ዉስጥ የማይነጥፍ የጥላቻ ውቅያኖስ ኣለ። ይህንን ቅርሻታቸው በነበሩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች፣ መጻሕፍቶች፣ ቴያትር፣ ፊልሞች ሲግቱን ኖሯል። እንዳውም ኣንዳንዶቹ “ኑ ከ ናዚ ጀግንነት እንማር” ብልው በጋዜጣቸው ስለጻፉ የምንግዜም ጀግናችን ተብሎ ሲወደሱ እያየን ነው። በኣንጻሩ ታሪክ ሰሪዎቹ ደግም ምንም ሲጽፉ ኣናይም። ከዝያ ይልቅ ታሪካቸውን ለማይጽፍላቸው ህዝብ ታሪክ ሲሰሩ ኖሯል። ኣብዛኛዎቹ “ኢትዮጵያውያን ታሪክ ጸሃፊዎች” ግን ታሪክ ተሰርቷል ግን ማን ሰራው ብለን እንጽፈዋለን በማለት በተቃራኒው ታሪኩን በማጠልሸት የተሻለ ጸሃፊ ለመሆን ሲፎካከሩ ኑሯል።

ይህንን ድርጊታቸው ደግሞ ገዢ ደርጅቱን በማስታከክ የወጣበትን ማህበረሰብ ታሪክ እንዳይኖረው የተጠነሰሰ እጀ-ረጅም ሴራ ነው። ይህ አካሄድ ደግሞ “የእኛ ካልሆነ የእነሱ መሆን የለበትም” የሚል የወደቀ ኣካሄድ ነው። የዚህ ኣንዱ ማሳያ በሃይማኖት-ለበስ ፖለቲከኞቻችው የሚያስተጋቡት፣ የእኽሱም ፈላስፋው ዘርዓ-ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ኣይደለም ቅዱስ ያሬድ ኣክሱማዊ ኣይደለም እስከማለት ደርሷል። አጼ ዮሃንስም ሆነ ጀ/ኣሉላ ኣባነጋም ሓውልት እንዳይኖራቸው የሚፈለገው ለዚህ ነው። ያሳዝናል!!!

የ27 ዓመት ጉዳይም ከዚህ የተለየ ኣይደለም። በተደጋጋሚ ጊዜ እንደሚነገረው 29 (+2 ዓመት ከለውጥ በኋላ) ህወሓት ብቻዉን ሀገር ሲመራ እንዳልነበር ቢታወቅም እንደተለመደው ሁሉም ጉድፍ ለህወሓት እና ለሚወክለው ማህበረሰብ በመለጠፍ፣ በእነሱ ስኬት ግን እነሱ ሲንፈላሰሱ ይታያል (እዉነትን ሰቀሏት ነው ያለው ገጣሚው)። ይህንን የሚያደርጉት ከ100 ዓመት በኋላ የመጣ የእኛ ያልሆነ መንግስት ጥሩ ታሪክ ሊኖረው ኣይገባም፣ኣርቀን መቅበር ስላለብን በደምብ መስራት ኣለበን ብለው ተቀናጅተው እየሰሩበት ይገኛሉ። ለስኬታቸው ደግሞ ወጣቶች እና ህጻናት ላይ እስኪሰርጽ ድረስ በደንብ እየሰሩበት ይገኛሉ ለሚቀጥሉት ዓመታትም አበክረው እንደሚቀጥሉበት ኣልጠራጠርም። በቅርቡ ደግሞ “ኢትዮጵያውያን ታሪክ ጸሃፊዎች” የጻፉት በጥቁር ጠባሳዎች የተሞሉ የታሪክ መጻሕፍቶች እንካችሁ እንደሚሉን መጠበቁ ኣይከፋም።

ታሪክ ባይሰሩም የሌላውን ታሪክ በማጠልሸት የተካኑ በመሆናቸው በደንብ ኣድምተው ይጽፉታል። ሆኖም ግን ይህንን በምያደርጉበት ጊዜ ታሪክን እያቆሰሉ እና የታሪክ ቦምብ እየቀበሩ የኢትዮጵያውያን ስቃይ እያራዘሙ እና እያደሱ ይኖራሉ። እውነታው ግን እንደ ሁል-ጊዜ እየጎመራ ይሄዳል።

ለዚህ መፍትሄ መሆን ያለበት ታሪክ ሰሪዎች የሰሩትን ታሪክ በተቻለ መጠን ሚዛናዊ ኣድርገው ጽፈው ለትውልድ ማስተላለፍ ካልቻሉ “ኢትዮጵያውያን ታሪክ ጸሃፊዎች” ታሪካችንን እያጣመሙ የታሪክ ቦምብ እየቀበሩ ይኖራሉ።

ማስታወሻ፦
በ27 ዓመት ዘረኝነት ተዘራ ለሚሉ፣ ኦሮሞው፣ትግራዋይ፣ቤንሻንጉል፣ጋምቤላው፣በርካታ የደቡብ ብሄረሰቦች እንዲሁም ሌሎች ስማቸውን ተጥሎ በማይፈልጉት ስም ሲጠሩ የኖሩት በዚህ 27 ዓመት ኣይደለም በልሉኝ።
ከቆየን እያየን እንጨምራለን።

ናይ ባዕልኻ ማዕጾ ከይዓጸኻ፣ ናይ ጎረቤት ማዕጾ ምዕጻው ካብ ዝብኢ ምብላዕ ኣየድሕንን።