Sunday 23 September 2018

“ከኢትዮጵያ ትቅደም፤ወደ ኦሮሞ ይቅደም።”

ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ፤ (ሰሜን አሜሪካ)  

ኢትዮጵያ ከሶስት ሺህ ዓመትታ በላይ ታሪክ ያላት ሃገር ናት ሲባል፤ አሁን ያላትን መልክአ ምድር ይዛ ቆይታለች ማለት አይደለም። እንደማንኛውም በዓለማችን እንዳሉ ሃገራት፤ ኢትዮጵያ የተገነባቸው፤ በሰዎች ከቦታ ቦታ ፍልስት፤ ግጭቶች፤ ጦርነቶች፤ ሕይወታቸውን ከዘላንነት ወደ ቋሚ አራሽነት በቀየሩ፤ በአጠቅላይ፤ ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው በሰፈሩ ሰዎች ነው። ሌላውን “መጤ” የሚል፤ በእራሱ ስሌት እሱም “መጤ” መሆኑን መቀበል አለበት፤ ልክ እንደ ሌላው፤ የእርሱም ዘር ማንዘሮች ከሌላ ቦታ መጥተው ነው ዛሬ “መሬቴ” የሚላትን ቦታ የያዘው።ይህንን መካድ፤ የሕብረተሰብ እድገት ሳይንስን መካድ ይሆናል። እግዚአብሔር፤ ወይም የተለየ ሰማያዊ ኃይል፤ ይህች መልክአ ምድር ለኢትዮጵያ ነች ብሎ ቀርፆ የሰጠን የለም። ይህ ለኦሮሞ፤ ይህ ለአማራ፤ ይህ ለትግሬ ወዘተ ብሎም፤ ያከፋፈለ ሰማያዊ ሃይል የለም። ኢትዮጵያ እንደ ሃገር፤ እንደ ማህበረሰብ፤ በጉልበት የተገነባች ሃገር ናት። እያንዳንዱ ብሔር/ብሔረሰብ ዛሬ የኔነው የሚለውንም ቦታ የተቆጣጠረው በተመሳሳይ መልክ ነው። ድንበር፤ ሃገር፤ ክልል፤ የምንለው ሰው ሰራሽ ነው። ይህ የመላው አለም የሃገራት ግንባታዎች ታሪክ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያን ከሌላው የተለየ አያደርጋትም። ይህን መሰረታዊ የሰዎችን የሕብረተሰብ ዕድገት አመጣጥ ማንሳት የፈለግኩት፤ ይህንን ሀ-ሁ በቅጡ ያልተረዱ “የፖለቲካና ታሪክ ምሁሮቻችን”፤ ወይም ይህን በቅጡ ተረድተው እኩይ አላማ ይዘው፤ በተዛባ ትርከት የሚያተራምሱን ኃይሎች አንዱን መጤ፤ ሌላውን ባለሃገሬ ብለው ሊኮንኑ የሚችሉብት መቆምያ እግር እንደሌላቸውም ለመጠቆም ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ከተቆረቆረችበት ጊዜ ጀምሮ፤ በሃገሪቱ የኖሩ ዜጎች፤ ከየትኛውም ዘር ይምጡ፤ ለበጎ እድገቷም፤ ለተሰራው ግፍና እኩይ ምግባር እንደ ግለሰብ፤ ወይም እንዳደራጁት ቡድን፤ በግለስብ እና በቡድናቸው ሊወቀሱ፤ ወይም ለሰሩት በጎ ሥራ ሊመሰገኑ ይገባል እንጂ፤ ግለሰብ ወይም ቡድን በሰራው፤ የአንደ “ዘር” ማህበረሰብ፤ በጅምላ ሊወቀስም ሆነ ሊሞገስ አይገባውም። በማንኛውም ዘር ውስጥ፤ መጥፎ ሰው እንዳለ ሁሉ ጥሩም ሰው አለ። መጥፎው ሰው የሚወክለው እራሱን ብቻ ነው፤ ጥሩውም ሰው እንደዛው። ምንም እንኳን፤ አንድ ሰው የኖረበት ማህበረሰብ እና አካባቢ በግለሰብ አስተሳሰብ ላይ ተጽእኖ ቢኖረውም፤ ለሚያደርጋቸው ማንኛውም ድርጊቶች ሃላፊነቱ የግለስቡ ነው። ሰውን ከእንስሳ የሚለየውም ከአካባቢው የሚያገኘውን ትምህርት እና የኑሮ ዘይቤ አመዛዝኖ ጥቅምና ጉዳቱን አይቶ የሚወሰደውን እርምጃ ሚዛናዊ ማድረግ መቻሉ ነው። ሆኖም፤ የሰው ልጅ፤ ስስታም እና ግላዊ በመሆኑ፤ ከስብእናው ይልቅ “እንስሳነቱ” ሲብልጥበት በተደጋጋሚ አይተናል።  የሰው ልጅ አእምሮው እየሰፋ፤ እውቀቱ እየዳበረ ሲመጣ፤ ከቤተሰብ፤ ወደ ማህበረሰብ፤ ከዛም ወደ ህብረተሰብ እና ሃገር ግንባታም አድጓል። እነዚህ የእድገት ደረጃዎቹ በሰው ልጅ መካከል የፈጠሯቸው በጎ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ፤ መጥፎ ነገሮችም አሉ።  

ሃገራችንም በዚህ ምስቅልቅል እና የተጠማዘዘ ጎዳና አልፋ እዚህ ደርሳለች። የሰው ልጅ ስልጣኔው ዝቅተኛ በነበረበት ጊዜ፤ “ታላቅነት” ያስገኝልኛል የሚለው አመለካከቱ፤ አንዱ፤ ሌላውን በጉልበት አንበርክኮ በመግዛትና ግዛቱን በማስፋትላይ የተመረኮዘ ነበር። ከዘመናት በኋላ፤ እውቀቱ እየሰፋ ሲመጣ፤ ለሰው ልጅ የሚጠቅመው፤ ተከባብሮ መኖር እና፤ መሪዎቹን መርጦ እራሱ በሚያወጣው ሕግና ደንብ መተዳደር መሆኑን በመረዳት ባዋቀራቸው ተቋማቱ፤ የእኔ ብሎ በከለለው መልክአ ምድር፤ እነሆ ዛሬ ዓለም ላለችበት ሥልጣኔ በቅታለች። ይህ ማለት ግን የሰው ልጅ የመጨረሻ የእድገት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት አይደለም። ዛሬም የሰው ልጅ፤ የአንድን ሃገር ብቻ ሳይሆን፤ መላው ዓለም ላይ ያሉ ዜጎችን ሕይወት የተሻለ ለማድረግ በጥናት እና ምርምር ላይ ይገኛል። ይህ ማለት ሁሉም ሃገራት ተመሳሳይ እና እኩል የእድገት ደረጃ አላቸው፤ ሁሉም ሰዎች ተመሳሳይ የማሰብ አቅም አላቸው ማለት አይደለም። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። ለአሁኑ እዛ ዝርዝር ውስጥ አልገባም።

 

እንደ ሁሉም ሃገራት፤ ኢትዮጵያ፤ ከጋርዮሽ የህብረተሰብ እድገት፤ ዛሬ ያለችበት የእድገት ደረጃ ላይ ስትደርስ፤ ብዙ መሰናክሎችን አልፋ ነው። በዚህ ጉዞ፤ ሕዝብ ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ከትውልድ ትውልድ በተላለፈ ሰንሰለት፤ በተለያየ አካባቢ በመስፈር ማህበራዊ ኑሮውን ገንብቷል። ተጋብቶ በመዋለድ በደም ተሳስሯል፤ በማህበራዊ ኑሮ፤ በኢኮኖሚና በፖለቲካ አስተዳደር ተጣምሯል። አንዱ ገዢ እራሱን ወይም ቤተሰቡን በመወከል፤ ሌላውን አስገብሯል፤ በየትኛውም ወቅት፤ አንድ መላ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ሌላውን የጨቆነበት ወቅት ለመኖሩ ምንም ጭብጥ መረጃ የለም። እንደውም ብዙዊቹ ነገስታት፤ ከአንድ ዘር ብቻ የመጡ ላለመሆናቸው የታሪክ ፀሃፊዎች ዘግበውታል። ብዙ ኦሮሞ ወገኖቼ በአማራነት የሚወቀሱዋቸው ዓፄ ምኒሊክ፤ የኦሮሞ፤ የወላይታ፤ እንዲሁም የአማራ ደም አለባቸው፤ በአማራነት የተፈረጁት ዓፄ ኃይለሥላሴም እንዲሁ የአማራ እና የኦሮሞ ዘር፤ እና የክርስቲያንና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችወላጆች ውጤት መሆናቸውም ታሪክ ፀሃፊዎች ዘግበውታል።

በ1960ዎቹ፤ ጽንፈኛ ኃይሎች፤ ኢትዮጵያን ለማዳከም ባቀነባበሩት ሴራ፤ በማኬቬሊያን የከፋፍለህ ግዛ አስተምህሮት፤ “የትግራይ ነፃ አውጭ”፤ “የኦሮም ነፃ አውጭ”፤ “የኦጋዴን ነፃ አውጭ” ወዘተ በሚል ስያሜ ኢትዮጵያውያንን በማደራጀት እና፤ ከሶማሌው አምባገነን መሪ የተንኮል “ገጽ” የተዋሷትን “የአማራ ገዥ” የሚለውን እኩይ የፖለቲካ መስመር በማራመድ፤ የኢትዮጵያን አንድነት ገዘገዙ። ላለፉት 27 ዓመታትም ሃገራችን በዚህ የጽንፈኞች ፖለቲካ ስታትመስ ቆየች። ሃገሪቱን የተቆጣጠረው ገዥ ፓርቲ የተከተለውን አደገኛ የፖለቲካ መስመር፤የሚሞግተውን፤ የሰብዓዊ መብት አክብር የሚለውን፤ የሚያወግዘውን እና እኩይ ዓላማውን የሚጋፈጠውን ሁሉ፤ ፊውዳሊስት፤ ደርጊስት፤ ወዘተ በሚል ስያሜ ዝም ለማሰኘት፤ የዜጎችን መብት በማፈን በሚወስደው አሰቃቂ የአፈና እርምጃ፤ የግፍ ጽዋው በመፍሰሱ፤ ከየአቅጣጫው የብሶት ማእበል እየገሰገሰ መጣ። ይህ ብሶት፤ ለሃገር ተቆርቋሪ የሆኑ ዜጎችን፤ ከየቦታው ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ሲያደርግ፤ አጋጣሚውን ተጠቅመን፤ እኩይ ዓላማችንን ተግባራዊ እናደርጋለን የሚሉ ጽንፈኞችንም አነሳሳ። እዚህ ግባ የሚባል እውቀትም ሆነ ራዕይ የሌላቸው ሰዎች፤ በአገኙት የታሪክ አጋጣሚ ማይክሮፎን በመጨበጥ እና፤ ቴክኖሎጂ የፈጠረው የማህበራዊ ሚድያ፤ የራሳቸው “የሚድያ ባለቤት” ስላደረጋቸው፤ ፍፁም ጽንፈኛ የሆነና፤ መርዛም የሆነውን በታኝ የፖለቲካ አጀንዳቸውን በማራመድ “የአቤቱታ ፖለቲካውን ፈረስ” እንደፈለጉት መጋለብ ጀመሩ። በዚህ ግርግር መሃከል ነው፤ የኦሮሞ ሕዝብን ብሶት ተጠቅመን ኦሮምያ የሚባል ሃገር እንፈጥራለን በሚል ቅዠት፤“I am an Oromo First” “መጀመርያ ኦሮሞ ነኝ” የሚለውን ጽንፈኛ አመለካከታቸውን መዘው ወደ መድረክ ብቅ ያሉት። ዓላማቸውም፤ ኢትዮጵያዊነትን ለማኮሰስ እና፤ ኦሮሞነትን ለማግነን ነው። ይህንን ተከትሎም፤ “Oromo First” “ኦሮሞ ይቅደም” በሚል መፈክር፤ በአእምሮና በእድሜ ያልበሰለው ወጣት፤ ብሶቱን በማራገብ ሃሳባቸውን እንዲገዛ አደረጉ። ይህም የልብ ልብ ሰጥቷቸው፤ ኢትዮጵያን የምታክል ታላቅ አገር፤ ጓሯቸው የበቀለ አረም ይመስል፤ ኢትዮጵያን እናፈርሳለን ሲሉ ዛቱ። ኢትዮጵያን በጉልበት እየገዛ፤ ዜጎችን በማሰር፤ በመግደል እና በማሳደድ የተካነው መንግስትም፤ በሚሰራው ግፍ፤ ለእነዚህ አክራሪ ሃይሎች፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ተከታይ እንዲያፈሩ መንገድ ከፈተ። “ኦሮሞ ይቅደም” የሚለው መሪ ሃሳብ ምን ማለት እንደሆነ ያልገባው ሁሉ፤ ኦሮሞ ይቅደም የሚለውን መፈክር ማራገብ ጀመረ። ይህም ለጽንፈኞቹ አቅም የፈጠረላቸው መሰላቸው። ለ27 አመታት በተደረገ ከፍተኛ ትግል እና በተከፈለ መስዋዕትነትም ገዥው ፓርቲ ተገዝግዞ፤ የለውጥ ኃይሎች ከውስጡ ብቅ ብለው ሃገሪቱን አቅጣጫ ማስያዝ ሲጀምሩ፤ጽንፈኞቹ የለውጡ መሪዎች እና አሸናፊዎች እኛ በማለት ማጓራት ጀመሩ። ደርግ፤ የሕዝቡን ድል እንደነጠቀ፤ ወያኔ ለ17 ዓመታት ሕዝቡ ያደረግውን ትግል እና መስዋዕትነት ገፍትሮና ክዶ፤ “ደርግን የጣልኩት እኔ ነኝ” ሥልጣንም የሚገባኝ እኔ ነኝ እያለ 27 ዓመታት እንደገዛ፤ ታሪክ እርሷን ልትደግም ቀና አለች። የኦሮሞ ይቅደም “ፈላስፎችም”፤ የታገልነውም ያሸነፍነውም እኛ ብቻ ነን፤ እኛ ሃገሪቱን መግዛት አለብን፤ እኛ ካልገዛን ኦሮምያን እንገነጥላለን፤ እያሉ ያናፉብን ጀመር። የብሔራው አጀንዳ ቀርጸው በሃሳብ መሞገት እንደማይችሉ ስለሚያውቁም፤ በታሪክ አጋጣሚ፤ በብሄራዊ መድረክ ላይ ያገኙትን “ዝናና ክብር” በመጠቀም፤ ባዶነታቸው ሳይጋለጥ፤ የጥላቻ መርዛቸውን በሚቆጣጠሩት ሚድያ በመርጨት የማተራመስ ስራቸውን ተያይዙት። ትላንት፤ በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ ከጽንፈኛ ኃይሎች ጋር ይደረግ የነበረው ትግል፤ ዛሬ መሃል መዲናችን ገብቶ፤ የንፁሃንን ሕይወት ቀጠፈ፤ ንብረትም አወደመ። ያ አልበቃ ብሏቸው፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት፤ ያልተገደለውን ሰው ተገደለ በማለት፤ የሃሰት ፎቶ እየለጠፉ አጥፊ ዘመቻቸውን ቀጥለዋል።

 

ለመሆኑ የ “Oromo First” (“ኦሮሞ ይቅደም) ጽንሰ ሃሳቡ ምንድነው? ይህ ጽንሰ ሃሳብ ከየት መጣ ጥቅሙና ጉዳቱስ ምንድነው? የሚለውን ማየት ለሁላችንም ይበጃል። ይህ እኩይ አመለካከት “America First” (አሜሪካ ትቅደም) እና “Ethiopia First” (ኢትዮጵያ ትቅደም) ከሚሉት ሃሳቦች ጋር በቅርፁ ይለያይ እንጂ በይዘቱ አንድ ነው። የኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግሥት “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለውን መርህ፤ የዜጎችን መብት ለማፈን፤ ያለሕግ ለማሰር እና ለመግደል፤ ጠላት ብሎ የፈረጃቸውን ለማሳደድ ተጠቅሞበታል። በኢትዮጵያ ትቅደም መርህ፤ 17 ዓመታት ሃገሪቱን ረግጦ የገዛው ሥርዓት፤ ኢትዮጵያን ያስቀደመ ሳይሆን፤ ለዓመታት ወደ ኋላ የጎተተ፤ ሃገሪቱን የጦርነት አውድማ ያደረገ፤ እና ሕዝቧን ለስቃይ የዳረገ፤ በሃገሪቱ ታሪክ ትልቅ ጥቁር ነጥብ የተወ ነው። ደርግ፤ “በኢትዮጵያ ትቅደም” ሰም ነግዶ፤ ሕዝብ አሰቃየ እንጂ፤ ሕዝብን ወደፊት አላራመደም። “ኦሮሞ ይቅደም” የሚለው መርህ ስር እየሰደደ ከሄደ የሃገራችን እጣ ፋንታ ከዚህ የተለየ አይሆንም።

 

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ሥልጣን በተረከቡበት እለት፤ አሜሪካን ትቅደም የሚል መርህ እንደሚጠቀሙ ሲገልጹ፤ ይህ ከዚህ ቀደም አሜሪካኖች የሚያውቁት መርህ፤ የመርሁን አደገኛነት የሚያስታውስ ትዝታቸውን ቀሰቀሷል። በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ፤ አሜሪካ ትቅደም የሚለውን መርህ ያቀነቅኑ የነበሩት፤ በአሜሪካው የሪፓብሊካን ፓርቲ ውስጥ የነበሩ ጥቂት ጽንፈኞች እንደነበሩ እና፤ በወቅቱ፤ ይህ መርህ በብሔራዊ መድረክ ላይ ቦታ እንዳላገኘ፤ ሳራ ቸርችዌል የተባሉ የታሪክ ምሁር “Behold, America” በተሰኘው መጽሐፋቸው ይነግሩናል። ይህ ጽንፈኛ መርህ ግን አፈር ልሶ በአሜሪካ ብሔራዊ መድረክ ላይ  በ1915 (እአአ) እንደተነሳ በዚሁ መጽሐፋቸው አስፍረውታል። በ1915 የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዊድሮ ዊልሰን ባደረጉት ንግግር፤ የአሜሪካንን ትቅደም መርህ በመጠቀም፤ አሜሪካ አንደኛው ዓለም ጦርነት ውስጥ እንደማትገባ ገልፀው ነበር። በ1916 በተደረግው የአሜሪካን የፕሬዝዳንት ምርጫ ውድድርም “አሜሪካ ትቅደም” የዊልሰን እና የተቀናቃኛቸው መፈክር ሆኖ እንዳገለገለ ሳራ ቸርችዌል ነግረውናል። ምንም እንኳን ዊልሰን፤ አሜሪካ ትቅደም የሚለውን መርህ የተጠቀሙት፤ አሜሪካ በሌሎች ሃገራት ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባ ለማሳወቅ ቢሆንም። ይህ መርህ በጽንፈኞች ተጠልፎ፤ KKK ለተባለው የነጭ ዘረኞች ዳግማዊ ትንሣኤ መነሻ መፈክር ሆኗል። በዛን ወቅት አሜሪካኖች፤ “አሜሪካ ትቅደም” የሚለውን መርህ ከፋሽዝም ጋር ያመሳስሉት እንደነበርም ታሪክ ፀሃፊዋ ያስተምሩናል።

 

አሜሪካ ትቅደም የሚለው መርህም ይሁን ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለው መርህ ለሃገርና ለሕዝብ ያልበጀ እኩይ መርህ በመሆኑ፤ እስከ 2010 (እአአ) ተቀብሮ ቢቆይም፤ በ2010 ኦሮሞ ይቅደም በሚል ተተክቶ፤ እንዲሁም በ2017 በዶናልድ ትራምፕ፤ አሜሪካ ትቅደም የሚለው መርህ አፍር ልሶ እንደገና ተነስቷል። ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ትቅደም በሚል መርህ፤ በአሜሪካን የሃገር ውስጥ እና የውጭ ሃገር ፖሊሲ የፈጠረው ቀውስ፤ እንዲሁም ተቀብሮ የነበረውን የነጭ ዘረኞች ስሜት ምን ያክል እንዳበረታታ እና፤ እየፈጠረ ያለውን የአግላይነት አንድምታ በገሃድ እያየን ነው። በብዙ ነገር ኩረጃ የሚታሙት፤ አሜሪካን ትቅደም የሚለውንም የኮረጁት፤ የኦሮሞ ይቅደም መርህ አቀንቃኞች አላማ ከዚህ የተለየ አይደለም።

 

የኦሮሞ ይቅደም መርህ ከአሜሪካው ለየት የሚለው፤ የአሜሪካው መርህ፤ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመረጣቸው የሃገሪቱ መሪ የሚቀነቀን መሆኑ ነው። ይህም ሆኖ ግን፤ ይህ አደገኛ መርህ፤ ከአብዛኛው ሕዝብ እና ከበርካታ የዓለም መንግሥታት ተቃውሞ ገጥሞታል። የኦሮሞ ይቅደም መርህ አራማጆች፤ እራሳቸውን በመሪነት የሾሙ፤ ማንም ያልመረጣቸው፤ እንኳን የኦሮሞን ሕዝብ ወክለው ይቅርና፤ የራሳቸውን ቤተስብ እንኳን ወክለው ለመናገር ሥልጣን የሌላቸው ናቸው። ሆኖም፤ የታሪክ አጋጣሚ በከፈተው “የመሪ” ክፍተት፤ የሕዝቡን ትግል፤ በጠለፋ የወሰዱ እና “በአቤቱታ ፖለቲካ” የታጀቡ፤ በሚቆጣጠሩት ሚድያ ጽንፈኝነትን እና ጥላቻን ከማራገብ በስተቀር፤ ለኦሮሞ ሕዝብ ጠብ የሚል ነገር ያልሰሩ ናቸው። እነዚህ ኃይሎች፤ የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን፤ ለሃገሩ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ ሃገሩን ኢትዮጵያን ለመገንባት ያብረከተውን አስተዋጽኦ፤ እነሱ በፈጠሩት ልብ-ወለድ ታሪክ ተክተው፤ ታሪኩን ያጎደፉ እና፤ ጥረታቸው ሁሉ “ኦሮምያን ለመገንጠል” ነው። እነዚህ ኃይሎች፤ የገንዘብ ሃይል ከየት እንዳገኙ፤ ወይም የውጭ ሃይል ከጀርባቸው ለመኖሩ መረጃ ስለሌለኝ እዛ ውስጥ አልገባም። ግን በርግጠኝነት ለመናገር የምችለው፤ እነዚህ ሰዎች፤ ሃሳብን በሃሳብ ማሸነፍ፤ እንዲሁም ጠቃሚ ፖሊሲ በመንደፍ በብሔራዊ መድረክ ላይ ሊሟገቱበትም ሆነ የሕዝብን ልብ ሊያሸንፉ የሚችሉበት አጀንዳ መቅረጽ እንደማይችሉ ነው።

 

ይህንንም በተግባር እያይነ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ በሃሳብ “ተሟግታችሁ አሽንፉ” እያለ የሚማፀን መሪ ባገኘችበት ጊዜ እና፤ ሃሳብ የማፍለቅ ነፃነት፤ ከሌላው ጊዜ በተለየ በተከበረበት ጊዜ፤ የኦሮሞ ይቅደም ፈላስፎች፤ በስራ እጦት እና በሌሎች ማህበራዊ ቀውሶች ወከባ ላይ ያለውን ወጣት፤ በትምህርት የሚጎልብትበትን አቅጣጫ ከመጠቆም፤ የእጅ ሙያ እንዲማር እድል የሚያገኝበትን፤ የራሱን ንግድ ጀምሮ ኑሮውን ሊያሻሽል የሚችልበትን፤ ሥራ ሊፈጥር እና ኑሮውን ሊያሻሽል የሚችልበትን መንገድ ከመጠቆም ይልቅ፤ የተቆጣጠሩትን ሚድያ የሚጠቀሙብት፤ የሌለ ብሶት እየፈጠሩና ያለውን ብሶት እያጋነኑ፤ ያንኑ የለመዱትን የአቤቱታ ፖለቲካ በማራገብ፤ ወጣቱ የእነሱ አምላኪ እንዲሆን በየቦታው ግጭት ለመቆስቆስ ነው። ኦሮሞ ይቅደም የሚለው መርህ አግላይ፤ ጽንፈኛ እና ዘረኝነትን እና አድልዎን የሚያንሰራፋ መርህ ነው። ልክ እንደ ኢትዮጵያ ትቅደም፤ ኦሮሞ ይቅደም፤ የሃሳብ ነፃነት አይፈቅድም፤ እነሱ የሚያራግቡትን የሃሰት ታሪክ ያልተቀበለ ሁሉ “ጸረ ኦሮሞ” ተብሎ ይፈረጃል። ጉልበት እያገኙ ከመጡ ደግሞ፤ የሚሞግቷቸውን ለማስቆም አስቃቂ እርምጃ መውሰዳቸው አይቀሬ ነው። ይህን ጽንፈኛ አመለካከት የሚያራምዱ ኃይሎች፤ ማንንም የማዳመጥ ትዕግስት የላቸውም፤ ሁሉንምነገር እነሱ ብቻ መዘወር የሚችሉ ይመስላቸዋል። የኢትዮጵያዊነት ስሜት በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ “እንዳይሰርጽ” የማድረግ መብት እና ችሎታ ያላቸው ይመስላቸዋል። ብዙሃኑ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊነቱ እና ኦሮሞነቱ እንደማይጋጭበት አልገባቸውም።

 

 የኦሮሞ ሕዝብ፤ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ፤ ጭቆና አንገሽግሾታል፤ ብሶት አለበት። ጽንፈኛ ኃይሎች ግን፤ ይህን ብሶት ተጠቅመው የኢትዮጵያዊነት ስሜቱን ለመሸርሸር ተግተው ይሰራሉ። ሕዝቡ በሃገሩ ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ፤ ይቀሰቅሳሉ፤ አመጽ ያስነሳሉ፤ ያንኑ የፈረደበትን ንጉስ ምኒልክ እና የአማራ ሕዝብ እየኮነኑ፤ የአንድነት ኃይል በሚል ስም፤ መብትህን፤ ሊገፉ ነው፤ ነፃነትህን ሊነጥቁህ ነው፤ የሚል ታምቡራቸውን ይመታሉ። ለኢትዮጵያ አንድነት የሚቆሙትን ሁሉ ይኮንናሉ፤ የ18ኛ እና የ19ነኛ ክፍለ ዘመን ገዥዎች፤ “ለምን ዲሞክራት አልነበሩም? ለምን እንደ 21ኛው ክፍለ ዘመን ሰው አላሰቡም?” ብለው ያላዝናሉ። አንድ ሃገር፤ የእድገት ደረጃውን ጠብቆ እንደሚራመድ ጠንቅቆ አልገባቸውም። ክሳቸው እና ከቀደምት ነገስታቶች ጋር ያላቸው ሙግት፤ ለምን በምኒሊክ ጊዜ ተንቀሳቃሽስልክ አልነበረም? ለምን በዓፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ ኢንተርኔት አልነበረም? የሚል ዓይነት ነው። አርበኛው ኦሮሞው አያቴ፤ ከጣልያን ጋር ለመዋጋት ሲዘምቱ፤ የኢትዮጵያን ክብር እና የግዛት አንድነት ለመከላከል ነበር፤ ለሰብዓዊ መብት ሲሟገት እድሜውን የገፋው ኦሮሞው አባቴ፤ የጮኽው ለመላው ኢትዮጵያዊ ነበር። ዛሬ ዓለም እየሰፋ ባለበት ጊዜ፤ የኦሮሞን ሕዝብ አግላይ ለማድረግ የሚተጉ ሰዎች፤ የሚደክሙት ለኦሮሞ ሕዝብ ነው ብለን ካሰብን በጣም ተሳስተናል። እነዚህ ሰዎች፤ በሺህ የሚቆጠር ኦሮሞ ከሶማሊያ ክልል ሲፈናቀል፤ ምንም ዓይነት እርዳታ እንዳላደረጉ በርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ይልቁንም፤ ቁስሉን፤ ስቃዩን፤ ለፖለቲካ ትርፍ ተጠቀሙበት እንጂ።

 

ኢትዮጵያ ባለችበት በዚህ የሽግግር ወቅት፤ ‘አላማችንን ለማሳካት እድል አግኝተናል’ ብለው የሚያስቡ ጽንፈኛ ኃይሎች ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው። የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር የተባለው ድርጅት፤ ኦሮምያን ከተቀረው ኢትዮጵያ እገነጥላለሁ በሚል ቅዠት ከ40 ዓመታት በላይ ዳክሯል፤ ግን አልተሳካለትም። ኦነግ ያልተሳካለት፤ አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሀገሩ ተገንጠል መባሉ ስላልተዋጠለት ነው። ኦነግ ያቃተውን የመገንጠል አባዜ፤ ነጋ ጠባ የራሳቸውን ድምጽ በመስማት በሚመረቅኑና፤ በአማርኛ ስለአንድነት እያወሩ፤ በኦሮምኛ ጥላቻን በሚሰብኩ፤ እንጭጭ ፖለቲከኞች፤ የኦሮሞ ሕዝብ እነሱ እንደፈለጋቸው የሚቆጣጠሩት ይመስል፤ “ብፈልግ ኦሮምያን እገነጥል ነበር፤ ማን ይከለክለኝ ነበር” የሚል፤ አዙሮ ማየት የማይችል ጨቅላ አእምሮ ያላቸውትዕቢተኞች፤ ያሳካሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም። እነዚህ ጽንፈኞች ግን የጥላቻ መርዛቸውን ዘልቀው ከመትከላቸው በፊት፤ ልጓም ሊበጅላቸው እና በግልጽም ሊጋለጡና ሊሞገቱ ይገባል። እንደ ኢትዮጵያ ትቅደም፤ ኦሮሞ ይቅደምም፤ ለሃገርና ለሕዝብ የሚያተርፈው፤ ሃገራችንን የጦርነት አውድማ ማድረግ እና የሕዝቡን ስቃይ ማርዘም ብቻ ነው። እነዚህ ጽንፈኛ ሃይሎች፤ እንኳን የኦሮሞን ሕዝብ አስተባብረው ለኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም ሊሰሩ ይቅርና፤ ለኦሮሞ ሕዝብ እንታገላለን ብለው እንደ አሸን የፈሉትን ወደ ሰባት የሚሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ማግባባት አልቻሉም። እነዚህ ኃይሎች፤ በአንድ ላይ መቆም ያልቻሉት፤ ከኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም እና ከሃገር ጥቅም ይልቅ፤ በራሳቸው የግል ጥቅም የተቃቃሩ በመሆናቸው ነው። ስለዚህ፤ መላው ኢትዮጵያዊ፤ “ኦሮሞ ይቅደም” የሚለውን የወደቀና የከሸፈ፤ እንዲሁም አፍራሽ አስተሳሰብ፤ ሊሞግተው እና ባዶነቱንም ማጋለጥ ይኖርበታል።
 
(ምንጭ : አይጋ ፎረም )
 
 

No comments: