Tuesday, 8 January 2019

የኤትዮ-ኤርትራ የድንበር መክፈትና መዝጋት፤ የብቀላና የሴራ ፖለቲካ ድራማ ተከታታይ ትዕይንቶች

ከ "/ "

አብይ አህመድ ኢትዪጵያን መምራት ከጀመሩበት ግዜ አንስቶ በሃገሪቱ አዳዳስ ክስተቶችን ቶሎ ቶሎ መመልከት ልማድ ሆኖአል፡፡ ክስተቶቹ ግን ባብዛኛው ሃገሪቱ ባለፈው 27 አመት የተጉዋዘቻቸውን መልካም መንገዶች የሚያክፋፉ፣ ያስመዘገበቻቸውን በጎ ውጤቶች የሚያራክስ፣ በምትኩ ግጭትና ጥላቻን የሚያባብሱ ንግግርና ሴራ ያመዘነባቸው ሆነው ይታዩኛል፡፡ ከነዚህም ውስጥ በኢትዪ-ኤርትራ ‹‹የድንበር ውዝግብ›› በ‹‹ሰላም›› መፍታት በሚል የሴራ ‹‹ፖለቲካዊ ድራማ›› የተተወነበት ትዕይንት ዋነኛው ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በፊት በዚሁ የአይጋ ፎረም አምድ ‹‹የኢትዪ ኤርትራ ስምምነት የሰላም ፍላጎት ወይስ የብቀላና የፖለቲካ ትርፍ ስሌት›› በሚል አንድ ጽሁፍ ለንባብ አብቅቻለው፡፡ አሁን ደግሞ ሰሞኑን የተዘጉትን የዛላምበሳና የራማ ድንበሮች፤ ትናንት የተከፈተውን የሁመራ-ኡምሃጀር ድንበር ስመለከት የ‹‹በቀልና የሴራ›› ፖለቲካ ድራማ ቀጣይ ትዕይንቶች ሆነው አግኝቻቸዋለው፡፡

በመሰረቱ እኒህ የሁለቱ አገራት መሪዎች አንድ ግዜ ስርዓት ያለውና ቀናነት የተሞላበትን የድንበር ላይ ሰላም በንድፈ አስቀመጠው ወንበራቸውን ወደ ሚመጥን ስራ መግባት ሲኖርባቸው ኤርትራና ኢትዪጵያ በአራት አቅጣጫ ብቻ የሚዋሰኑ ይመስል ድንበር ‹‹አስከፈትን›› እያሉ ሲጉዋተቱ መዋላቸው አንድም የቱን ያህል ስራ ማጣታቸውን ሲያሳይ አንድም የቱን ያህል ለብቀላና ለሴራ ፖለቲካ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ለኔ ግን ጎላ ብሎ የታየኝ ሁለተኛው አንድምታ ነው፡፡

የዛላምበሳና የራማ ድንበሮች መዘጋት

ኤርትራን በትግራይ በኩል ከኢትዪጵያ ጋር የሚያዋስኑት የዛላምበሳና የራማ ድንበሮች ከተከፈቱ መንፈቅ እንኳን ሳይሆናቸው መልሰው መዘጋታቸው አስቀድሞ ድንበሩንም ስለመክፈት በተለይ ለኤርትራ ህዝብ የተሰጠ አንዳችም መግለጫ እንዳልነበር፤ ሲዘጋም እንዲሁ ለኢትዪጵያም ሆነ ለኤርትራ ህዝቦች አንዳች ማብራርያ አለመሰጠቱ ሁለቱ መሪዎች ጉዳዪን ለግል አላማቸው እንጂ ለህዝቡ አስበው እንዳልያዙት ያሳበቀባቸው ነበር፡፡ ድንበሮቹ የተዘጉበት ምክንያት ግን አብዛኛው ሰው እንደተንሾካሸከበት የኤርትራ መንግስት በቀድሞው መከላከያ ሚኒስትሩ ጀነራል ስብሃት ኤፍሬም ላይ የግድያ ሙከራ ያደረገብኝ ‹‹ወያኔ›› ነው የሚል የዘመኑን ፍሽን ‹‹ሰበብ›› አድረጎ እንደሆነ ነው፡፡ መቼም ዘንድሮ በኢትዪጲያና በኤርትራ ለሚፈጠሩ ማናቸውም ችግሮች ገና ችግሮቹ ሳይፈጠሩ ጭምር መንስኤአቸው ‹‹ወያኔ›› ነው የተባለ ይመስላል፡፡ ማንም ሰው ተነስቶ የሰማውን ወንጀል ሁሉ ከ ‹‹ወያኔ‹‹ ጋር ማስተሳሰር የዚህ ዘመን ‹‹ፋሽን›› ሆኖአል፡፡ ለማንኛውም የኤርትራው መሪ ምናልባትም ከኢትዪጵያው መሪ ጋር በተቀናጀ መልክ የተወኑት ድራማ ሁለቱን ድንበሮች በመዝጋትና በምትኩ አንድ አዲስ ድንበር በመክፈት ቀጥሏል፡፡

በዛላምበሳና በራማ ድንበር መከፈት ተፈጥሮ በነበረው የሁለት ወንድማማች ህዝቦች ተፈጥሮአዊ ጉድኝት የኤርትራውም ሆነ የኢትዪጵያው መሪ ደስተኞች እንዳልነበሩ መገመት አያስቸግርም፡፡ ምክንያቱም የሁለቱ መሪዎች ዋነኛ አጀንዳ ‹‹ወያኔ›› ን ማክሰም እንጂ ሁለቱን ‹‹ትግሬዎች›› ማቀራረብ አይደለም፡፡ ሁለቱ ትግሬዎች መቀራረባቸው ጥቅሙ ለሰፊው ህዝብ እንጂ ለኢሳያስ ወይም ለአብይ ሊሆን አይችልም፡፡ ኢሳያስ በባህርያቸው የትምክህትና የንቀት በሽታ ሰለባ በመሆናቸው የመረብ ወዲህ ትግራዋዪችን ከመረብ ወዲያ ወንድሞቻቸው እኩል መጎዳኘታቸው መቼም ቢሆን የሚፈልጉት አይደለም፡፡ ‹‹ትምክህት ያሳውራል›› እንዲሉ ኢሳያስ ራሳቸው ግማሽ ወገናቸው የሚመዘዘው ከመረብ ወዲህ ትግራይ ሆኖ ሲያበቃም እርሳቸውን የያዘ የእብሪት ልክፍት ግን በአደባባይ መሸፍን በማይችሉት ደረጃ ጥላቻና ንቀታቸው ሲገለጥባቸው ይስተዋላል፡፡ በርግጥ ጥቂት የማይባሉ የመረብ ‹‹ወዲያ›› ትግሬዎች ‹‹የወዲህ›› ወገናቸውን ከኢሳያስ በማያንስ ደረጃ ሲንቁ ይስተዋላሉ፡፡ እኒህም ሰዎች የድንበሩ መከፈተና የህዝቦችን መቀላቀል አይስደስታቸውም፡፡ አብይ አህመድም ዋና ፍርሃታቸው ወያኔ ‹‹መቃብር ፈንቅሎ›› ያንቀኛል ከሚል ፍርሃታቸው እንዲያርፉ ትግራይ በሰቆቃ እና በስንክሳር እንጂ በፍስሃና መረጋጋት ውስጥ እንዳትቆይ ሊመኙ ይችላል፡፡ አብይ አህመድ የትግራይን ህዝብ ይፈሩ እንደሆነ እንጂ እንደ ‹‹የጠላት ጠላት ወዳጃቸው›› ኢሳያስ አይንቁም ይሆናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ዋናው ጉዳይ የጋራ ጠላትህን ለማጥፋት ከማትመሳሰለው ሰው ጋርም ቢሆን ማበር ነውና የትግራይ-ኤርትራን ድንበር በማዘጋት ጉዳይ ሁለቱም ከተለያየ አቅጣጫ በአንድነት ለእኩይ አላማ ተሰልፈዋል፡፡

የአሰብ/ቡሬ ድንበር ሳያዘጋ መቅረት

አንዳንድ ሰዎች ሁለቱ የትግራይ-ኤርትራ ድንበሮች የተዘጉት የድንበር ላይ ንግድና ዝውውር ህገ ደንብ ለማውጣት ታስቦ ነው ይላሉ፡፡ ለኒህ ሰዎች የአሰብ/ቡሬ ( አፋር-ኤርትራ) ድንበር አለመዘጋቱን አላወቁ ካልሆነ በስተቀር የሴራው ደጋፊዎች መሆናቸው ነው፡፡ በነገራችን ላይ የትግራይ-ኤርትራ ድንበሮች ላይ የሚጠየቀው ከኢትዪጵያ ፌደራል መንግስት የይለፍ ደብዳቤ በአፋር-ኤርትራ በኩል የማይጠየቅ መሆኑ አብይና ኢሳያስ ትግራይን ለማኮስመን የተበተቡት ሰይጣናዊ ተንኮል ለመሆኑ ብዙም ምርምር አያስፈልገውም፡፡

የሁመራ-ኡምሃጀር ድንበር መከፈት

አዲሱ የሁመራ-ኡምሃጀር ድንበር ሲከፈትም ከላይ ከተቀመጠው ትንተና ጋር የሚተሳሰር አካሄድ ታይቶበታል፡፡ ድንበር ከፈታው ስነ ስርዓት ላይ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ገዱ አንዳርጋቸውን መጋበዝ፤ መርሃ ግብሩን ‹‹የጎንደር-ኤርትራ›› ብሎ መሰየም፣ ስነ ስርዓቱን በትግራይ መሬት ላይ ሳይሆን በኤርትራ መሬት ውስጥ ማድረግ የሴራው ቀጣይ ትዕይንቶች ናቸው፡፡ ገዱ መጋበዙ ይህ ድንበር የትግራይ ሳይሆን አዲስ በተቋቋመው የአስተዳደርና የማንነት የወሰን ኮሚሽን አማካይት ለአማራ ተቆርሶ ሊሰጥ ከታሰበው የወልቃይት መሬት ጋር የተያያዘ ለማስመስል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አሁን ባለው ህዝቦችን፤ ባህልና ቋንቋን መሰረት ባደረግ የማንነት ፌደራላዊ አከላለል መሰረት ጎንደርን (አማራን) እና ኤርትራን የሚያገናኝ አንዳች ድንበር የለምና፡፡

እንግዲህ ይህን ሆኔታ አይቶ አብይና ኢሳያስን ከተለያየ መነሻ ግን ደግሞ አንድ እኩይ መድረሻ ላይ የተገመደ የብቀላና የሴራ ፖለቲካዊ ድራማ በንጹሃን ሰላም ፈላጊ የኤርትራና የትግራይ እናቶች፣ አባቶችና፣ ወጣቶችና ህጻናት ስም ሲጫወቱ መመለከት እጅግ ያሳዝናል፡፡ ይህ ሆኔታ የሁሉ ዳኛና ቅን ፈራጅ የሆነ አምላክ ባለበት አለም ውስጥ ብዙም ሳያቆይ ነፋስ መጥቶ አደርቆ ይረግፈዋል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ያን ግዜ ሰላምና ፍቅር የተራቡት ወንድማማች ህዝቦች ሴረኛና በቀለኛ መሪዎቻቸውን አስወግደው ያለ ማንም ከፋችና ዘጊ በመሬታቸው እንደልባቸው ሲንቀሳቀሱና ህዝብ ለህዝባቸውም ሲቀላቀሉ ማየት የሩቅ ግዜ ህልም እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለው፡፡
 
 

No comments: