Wednesday, 9 January 2019

የመጠላለፍ ፖለቲካው ሂደትና ደረጃው

በተክለሚካኤል ኪ/ማርያም

ኢሕአደግ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በከፍተኛ ኣመራር ሲጀምር ለውጡ ተስፋ የተጣለበት እንደ ነበር ብዙዎችን የሚያስማማ ቢሆንም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግሩ በኣርኣያነቱ የሚጠቀስና ለኣፍሪካ አገሮች ተምሳሌት ይሆናል እየተባለ ሲዘመርለት ግን የተጋነነ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ይኸውም ችግሩ የተፈለገውን እርምት ባለመውሰድ እንጂ ክፍተቶችን አንጥሮ በማውጣት የስልጣን ሽምሹር ማድረግ ለኢሕአደግ አዲስ ካለመሆኑም በላይ አሁንም ራሱ በሚመራው ለውጥ ምን ዓይነት ተአምር እንደሚሰራ ግልፅ ኣልነበረምና፡፡

በሌላ በኩል ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ በበዓለ ሲመታቸው ቀን ባደረጉት ንግግር ስሜትን የሚኮረኵሩ ብዙ ቁም ነገሮችን ሲያነሱ እውነትም ኢሕአደግ ለለውጥ ቆርጦ እንደ ተነሳ ፍንጭ የሰጠ ነበር፡፡ከንግግራቸው ከተደመጡ ዓበይት ነጥቦች መካከል አንዱ ባለፉት የስልጣን ዓመታት ለተፈጠሩ ችግሮች ይቅርታ እጠይቃሎህ ሲሉ ያኔ ኢሕአደግን ወክለው እንደ ተናገሩት የተወሰደ ቢሆንም ከተከናወኑ ስራዎች አኳያ ሲታይ ግን ኢሕአደግ ይቅርታ ይጠይቃል ሳይሆን እጠይቃሎህ ማለታቸው የግላቸው መሆኑን ግልፅ እየሆነ የመጣ፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪይስተጋባ የነበረው የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ እንድምታው ሲታይ ኢሕአደግ መስሎ ኢሕአደግን ማፍረስ የተባለውን ስትራተጂ እንደ ተሳካ ለመረዳት ከባድ አልነበረም፡፡አንድ ፓርቲ ይፍረስ ሲባል ግን የሚያራምደውን ፍልስፍና ትክክል እንዳልሆነ በሃሳብ ልዕልና በልጦ መገኘትናህዝቡ ፍላጎቱን የሚያሟላለትፓርቲ እንዲመርጥ አልያም ዓላማውን እንዲያስተካክል ማድረግ እንጂ ሰዎችን በማሳደድና በማሰር እንደ መፍትሄ መወሰድ ገና ከጅምሩ ችግር እንዳለው ግልፅ መሆን ጀመረ፡፡

በተለይ ኢሕአደግ የሚከተለው ፍልስፍና ህወሓት ያመጣው ስለሆነ ህወሓትን ካላጠፋን ሙተን እንገኛለን የሚል የጥላቻ ፖለቲካ በማስፋፋትናበትግራይ ህዝብ ላይ የጥፋት ክንዳቸውን ለማሳረፍ ዙሪያ ጥምጥምደባ መካሄድበአማራ ስም የተደራጁ ፓርቲዎች ግንባር ቀደም ዓላማ ከሆነ ውሎ አደረዋል፡፡ደባው የተለያየ ገፅታ ያለው ሲሆን የወሰንና ማንነት ጉዳዮችንእንደመነሻ በመጠቀም በተለያዩ የአማራና የትግራይ ኣወሳኝ ቦታዎች ግጭቶች እንዲነሱ የሚደረግ ተደጋጋሚ ትንኮሳመጥቀስ ይበቃል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩምየወሰን ጥያቄዎችለመፍታት የሚያግዝ አንድ አገር አቀፍ ኮሚሽን እንደሚቋቋም ሲገልፁ የሚቋቋመው ኮሚሽን የባለሙያዎች ስብስብ ሆኖ ጥናቱ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የሚያቀርብና ፌደሬሽኑን የሚያጠናክር እንደሚሆን ተስፋ የተጣለበት ነበር፡፡ይሁን እንጂ ከሕብረተሰቡ ግምት ውጭ ተጠሪነቱ ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከመሆኑም በላይ የመፍትሄ ሃሳብም እንደሚያቀርብ መደረጉ እንደ ተጠበቀው ሊሆን ኣልቻለም፡፡

አሁንም የህዝብ ተስፋ ያለመለሙንግግሮቻቸው መካከል አንዱ በየጊዜው በሚደረገው የስልጣን ሽግግር እየተወነጃጀሉ ከመኖር በእርቅ ፣ በይቅርታና በምህረት ለኣንዴና ለመጨረሻ ችግሮቻችንን እንደሚፈቱመግለፃቸው ነበር፡፡መሬት ላይ ያለው ግን ከዚሁ የተለየ በመሆኑ የፖለቲካ መጠላለፉ እንዳይቀጥል የብዙዎች ስጋት ሆኗል፡፡

በተለይ ባለፉት የኢሕአደግ የስልጣን ዘመን ተፈፀሙ የተባሉትን የሰብአዊ መብት ጥሰትና ሙስና በህግ እልባት እንዲያገኙ ማድረጉ ሁሉንም የሚያስማማ ቢሆንም በተለያዩ ሚዲያዎች እየተላለፈ ያለው ግን ሌላ ተጨማሪ የሰብአዊ መብት ጥሰት እያስከተለ ነው፡፡ይኸውም በቅንብርና ፈጠራ እየታጀበ በአንድ ብሄር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ዜጎች በጋዛ አገራቸው ክፉኛ የሚሸማቀቁበት ሁኔታ አስከትለዋል፡፡

ከዚሁ ባልተናነሰ መልኩ በአገሪቱ የተጀመሩ መለካም እንቅስቀሴዎች ተቋማዊ ኣለመደረጉ ችግር አይፈጥርም ወይ ተብሎ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ከፓርላማ ኣባላት ጥያቄ ሲቀርብላቸው የእስራኤልን ፓርላማ እንደ አብነት በመጥቀስ ሰዎች ሃሳብ ማቅረብና መደመጥ ቢችሉም የሚያሸንፍ ድምፅ እንደሌላቸው መግለፃቸውና ለመጥፎውም ለደጉም ብዙኃኑ ባሉት መገዛት ግድ እንደሚል ያመላከተ ንግግራቸው የብዙዎች ስጋት ነበር፡፡

በመቀጠልም እያንዳንዱ ግለሰብና ድርጅት በመደመር ፍልድስፍና ለውጡን ደግፎ የዴሞክራሲ ምህዳሩ ማስፋት አለበለዘያ ተገዶ ወደ አምባ ገነንነት የመግባት እድል እንዳለና ጉዳዩ ኣፋፍ ላይ መሆኑን ደጋግመው መናገራቸው ሌላ ስጋት ነው ፡፡

በተጨማሪም የወሰንና የማንነት ኮሚሽን ሲቋቋም ከሕገ መንግሰቱ አኳያ ተቀባይነት የለውም የሚሉ አካላት እያሉ በአብላጫ ድምፅ ሽፋንመፅደቁ የዚሁ ቀጣይ እርምጃ እንደሆነ ከመወሰዱም በላይ ነገሮች እየተካረሩ ይገኛሉ፡፡
ስለዚህ ብዙኃኑም ይሁኑ ኣናሳዎች ባለቸው የህዝብ ብዛት በሃገራቸው ሊኖራቸው የሚገባ ውክልናና ተጠቃሚነት ህገ መንግስቱ መሰረት ያደረገ እንጂ ሁሉም በድምፅ እየተወሰነ ኣዳዲስ ደንቦች የሚወጡ ከሆነ ሌላ ጣጣ እንደሚያስከትል ከወዲሁ ምልክቶች እየታዩ ስለሆኑ ኣከሄዱ የሃገር ህልውናን የሚፈታተን ስህተት ያደርገዋል፡፡
በተለይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከመጀመሪያ ጀምሮ ተቋማዊ እየተደረጉ ካለመምጣታቸው የተነሳ በኦሮሚያ እየታየ ያለው ሁኔታ የህዝቡ ስጋት ትክክል እንደነበረ ህያው ምልክት ነው፡፡ይኸውም ድርድሩ የኦዴፓ ተሳትፎ ያረጋገጠ በኦነግና በፈዴራል መንግስቱ መሆን ሲገባ በሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መደረጉ ለአፈታቱም አመችነት አይኖረውም፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በቃላቸው እንዳልተገኙ ሌላው ማረጋገጫ በተጨባጭ እየታየ ያለው  ልዩነትንየማስተናገድና የዴሞክራሲ ምህዳርን የማስፋት ችግር ነው፡፡ይኽውምበኣንድ በኵል የበቀል ቅስቀሳ በሚዲያዎች እንዲስፋፋ ሲደረግ በሌላ በኩል ደግሞ የተለየ አስተሳሰብ ያለው ግለሰብም ይሁን ድርጅት ፀረ ለውጥ ፣ ያልተደመረና ሌላም እየተባለ ሲሸማቀቅ በዝምታ ማለፋቸው ያልተጠበቀ ችግር ነው፡፡
የወሰን ጉዳይ ሲነሳ በሌላ ኣከባቢ ከሚፈጠሩ ግጭቶች ሲነፃፀር በትግራይና በኣማራ ክልሎች አወሳኝ ቦታዎች የሚኖሩ ህዝብ በሆነ ምክንያት ግጭት የማይከሰትባቸው ናቸው፡፡ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ የዘረኝነት ፖለቲካ የሚስተጋባው በኣማራ ስም በተደራጁ ፓርቲዎች ሆኖ በአማራ ሚዲያዎች ፊታውራሪነት በትግራይ ላይ እየተደረጉ ያሉት ትንኮሳዎች ፈዴራል መንግስቱ በዝምታ መመልከት ሌላ ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ይሆናል፡፡
በተለይ ኢሳት የተባለው ቴሌቪዥን የዘር ማጥፋት ቅስቀሳ በትግራይ ላይ ማካሄድ ከጀመረ ዓመታትን ሲያስቆጥር በአማራ መገናኛ ብዙኃንም ከሓምሌ 2008 ዓ/ም ጀምሮ ኣሁን ደግሞ በፌደራል ሚዲያዎች ጭምር በትግራይ ህዝብ ላይ ግልፅ የስነ ልቦና ጠርነት ከፈቶውበታል፡፡ለዚሁም በሌላ ብሄር ተወላጆች አየወረደ ያለው ግፍ የባሰበት ቢሆንም በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የትገራይ ተወለጆች ላይ ግድያ ፣ ማስፈራሪያ ፣ ዛቻና እንግልት እየደረሰባቸው ከመሆኑም በላይ አጠቃለይ የትግራይ ህዝብ እንዲሸማቀቅ ሲደረግ በዝምታ መታለፉ ሌለው የፌደራል መንግስት ችግርነው፡፡
ይህ አካሄድ ሆን ተብሎ እየተሰራ ለመሆኑ ደግሞ ብዙ ማስረጃዎች ማቅረብ የሚቻል ሲሆን ጥቂቶችን ለመጥቀስ አንድ ተጎጂ በመንግስት ድርጅት ጥቃት ለማድረስ ሲል ፀጥታ አካላት ደርሰውበት ሲሮጥ በእጁ ይዞት የነበረውን ቦንብ ፈንድቶ አካላቱ የተቆረጠው በትግርኛ ተናጋሪዎች ምርመራና ድብደባ እግሮቼ ተቆረጡ ብሎ እንዲናገር መደረጉ፡፡
እንዲሁም በቅርቡ በቡራዩ የማሰቃያ ጉድጓድ ፣ ተጎጆዎችና እነሱን ሲያመላልሱ የነበሩ ሄልኮፕተሮች መገኘታቸውንና እንዲዘገቡ በከተማው ባለስልጣን ለጋዜጠኞች ጥሪ ተደርጎ ምንም ነገር እንደሌለ የተረጋገጠው ሌላ ማስረጃ ሲሆን ይህንን በተመለከተ የዘገበ ኣካል አለመኖሩ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ፕሮፖጋንዳ ብዙዎችን ሊያደናግር እንደሚችል ባያጠራጥርም በቴሌቪዥን እየቀረቡ ለህገ ወጡ አካሄድ በመደገፍ ትንታኔ የሚሰጡ ምሁራን ፣ ባለስልጣናትና የፖለቲካ ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡ነገር ግን ምርመራ እንዴት እንደሚካሄድ ከማወቃቸውም በላይ የእያንዳንዱ ባለ ጉዳይ መዝገብ ማን እንደ መረመረውና መቸ እንደተመረመረ በሰነድ የተያዘ መሆኑን እያወቁ ህዝብን ማደናገራቸው አሁንም ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
ተወደደም ተጠላም በትግራይ ላይ እየቀረበ ያለው የስነ ልቡና ጦርነት ለጥቂት ፖለቲካኞች ፣ ፅንፈኛ ብሄርተኞችና ባለስልጣናት የልብ ልብ ቢሰማቸውም ኢትዮጵያውነትን የሚሸረሽርና የዘቀጠ አስተሳሰብ በመሆኑ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ከማሳዘኑም በላይ የታሪክ ተጠያቅነት እንዳለው መገንዘብ ያስፈልግ ነበር፡፡
በእኔ እይታ ኣሁኑ እየታየ ያለው በትግራይ ላይ ያነጣጠረ ደባ በ1980 ዓ/ም በለገሰ አሰፋው ከተፈፀመው ጋር የተለየ ሆኖ ኣላገኘሁትም፡፡ይኸውም ለገሰ አስፋው ዓሳውን ለማጥፋት ባሕሩን ማንጠፍ ብሎ በትግራይ ህዝብ ላይ ጥፋት በማወጅ ሰኔ 12 ቀን 1980 ዓ/ም ከመቐለ ያንቀሳቀሰው ጦር በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኘው ዓልዓሳ በተባለው ቦታ በቤተ ክርስቲያን ለፀሎት በተሰበሰበው ህዝብ ላይ የጅምላ ግድያ በመፈፀም 340 ሰዎች ሲገደሉሰኔ 15 ቀን ደግሞ ሓውዜን ለገበያ በተሰበሰበው ህዝብ ላይ የአየር ድብደባ በማካሄድ ከ2500 በላይ ንፁኃን ዜጎች ተገድለዋል፡፡
አሁንም በአማራ ስም የተደራጁ ፓርቲዎችና በክልሉ ባለስልጣናት ግፊት ለትግራይ ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት ያሟላሉ የተባሉትን ሁሉ እንዲከለከሉና መንገዶችን በመዝጋት ህዝቡ በችግር እንዲንበረከክ መሞከር ፣ የነጋዴዎች ንብረት በጠራራ ፀሓይ መዝረፍ ወዘተ የለገሰ አስፋው እርምጃ እየተደገመ ነው፡፡
የዚሁ ቀጣይ ሰይጣናዊ ተልእኮም በቅርቡበ12 የኣማራ ከተሞች ሰልፍ ተካሂዶ ዋስትናችን ህገ መንግስቱ ሳይሆን ኣንድነታችንና ነፍጣችን ነው የሚል መፈክር በማስተጋባት በትግራይ ላይ ጦርነት ታውጀዋል፡፡ይባስ ብሎም የአስራ ሁለቱ ከተሞች አስተዳዳሪዎች ጥያቄዎቻቹሁን ዳር ለማድረስ ግንባር ቀደም እንሆናለን ብለው አዋጁን በማፅደቅ ሰልፉ ሲጠናቀቅ አሁንም ፈዴራል መንግስቱ ኣንዳችም ኣላለም፡፡ከዚሁ የተነሳ የትግራይ ህዝብ ራሱን ከመከላከል ሌላ ኣማራጭ እንደሌለው ያረጋገጠበት ቀን ነው ማለት ይቻላል፡፡
የጥንስሱ ሰንሰለት ከየት ወዴት እንደ ሆነም ፕረዚደንት ኢሳይያስ የሰማእታት ቀን ለማክበር ለተሰበሰበው የኤርተራ ህዝብ የኢትዮ-ኤርተራ ችግር በሰላም ለመፍታት በኢትዮጵያ ጥሪ መደረጉና ወደ አዲስ አበባ አንድ ቡዱን ለመላክ መወሰናቸው ሲናገሩ በኢሕአደግ ከሚመራ መንግስት ጋር ለመነጋገር ነበር፡፡
ነገር ግን ቃል በቃል ያሉት ነገር «ኣሽካዕላል ወያነ አብቂዑ ፤ game over ተባሂሉ» ብለው በህወሓት ላይ ብሎም በትግራይ ህዝብ ላይ ምን እንደ ተጠነሰሰ በማያሻማ ቋንቋ ነግረውናል፡፡ኣሽካዕላል ማለት በእሳቸው ትግርኛ ዙሪያ ጥምጥም ኣሻጥር ማለት ይመስለኛል፡፡እንግዲህ ኢሕአደግ ወደ ሚመራው መንግስት የሰላም ንግግር ለማድረግ የሰላም መልእክተኛ እየላኩ ወያኔያበቃለትና የፖለቲካ ጨዋታው አክትመዋል ማለታቸው ምን ያህል ዘልቀው እንደገቡና የለውጡ ቀያሽና ተቋዳሽ እነማንን እንደሚያካትትየተረጋገጠበት ዕለትና የሰላም አጀንዳው ትግራይን ያገለለ እንደሆነ ግልፅ ነበር፡፡
ሌላ ተጨማሪ ማስረጃ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሰላም እንዲታገሉና እስረኞች እንዲፈቱ ወዘተ የሚለው የኢሕአደግ የለውጥ አቅጣጨ በአራቱ የኢሕአደግ ኣባል ድርጅቶች አመራሮች ተመከሮበት ለህዝቡ ይፋ ቢሆንም የግንቦት 7 መሪዎች አዲስ አበባ ሲገቡ ፕሮፌሰር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በስም ተቃዋሚ በመካከላችን ያላችሁ የወያኔ ተላላኪዎች ወዮላችሁ ብለው በመስቀል አደባባይ በተሰበሰበው ህዝብ ፊት መዛታቸው በህወሓትና በትግራይ ህዝብ ላይ ምን እንደ ታሰበ የበለጠ በግልፅ ቋንቋ አስቀምጠውታል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት እንደ ተገነዘብነውም ትግራይን ማዳከም የሚለው ስልት ይሳካ ኣይሳካ ሌላ ጉዳይ ሆኖ በአዴፓ በኩል ወደ መጨረሻው ምዕራፍ የደረሰ ይመስላል፡፡ይኸውም
1.   መጀመሪያ የትግራይ ወይ የህወሓት የበላይነት ነበር የሚል በሰፊው በመስበክ ህዝብን ማደናገርና ሁሉም ወደ ትግራይ እንዲያነጣጥር ማድረግ የሚለው ተሰርቶበታል፡፡
2.   ህዝቡን በጥላቻ ዓይነ ልቦናውን ከሰወሩ በኋላ ዓለም የመሰከረለትን ልማት እንደሌለ በአደባበይ መካድና ልማቱ እንዲደናቀፍ ማድረግ እሱም ተከናውነዋል፡፡
3.   ልክ የጀርመን ናዚዎች እስራኤላውያንን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት በተነሱበት ወቅት ትክክል አይደለም ብለው በተቃወሙ ጀርመናውያን ላይ አስቀድመው ግድያ እንደፈፅሙ ሁሉ በኢትዮጵያ ልማት መኖሩን የሚምኑና ለልማቱም ሆነ ለጥፋቱ ሁሉም የኢሕአደግ ኣባል ድርጅቶች ሓላፊነቱን መውሰድ ይገባል ላሉትም ማሳደድ ፣ ማስፈራራትና ከሓላፊነት እንዲለቁ ማድረግ ፣ ዕድለኞች የሆኑትም በመንግስት ጫና የራሳቸው ጥያቄ በማስመሰል በጡሮታ እንዲገለሉ ማድረግ የሚለው ይህም ተሰርተዋል፡፡
4.   በአማራ ፖለቲከኞችና ልሂቀን የተነደፈ አንድ ክላሽ ለአንድ አማራ የሚለውን የስልጠናና ትጥቅመርሃ ግብር መገባደዱንም መረጃዎች በመውጣት ላይ ናቸው፡፡
ለዚህ ሁሉ ቅድመ ሁኔታ ማሳረጊያው በሌለ የወሰንና የማንነት ጥያቄ ሰበብ በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት መክፈት ነው፡፡ነገር ግንየትግራይ ህዝብ ብቃት በራሳ አቅም መዝኖ ወደ እርምጃ መግባት ውድቀት መሆኑን ከኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም መማር ሲገባቸው የአዴፓና አብን መሪዎች ትግራይን በኃይል እናበረክካለን ብለው ለዳግም ውድቀት ተዘጋጀተዋል፡፡ይኸውም እነሱ አርበኞች የሚላቸውን የሽፍቶች መንጋ በየከተማው እየዙሩ ደማቅ አቀባበል እንዲደረግላቸው በማድረግ ትግራይን እንጨብጣለን፡፡ፋብረካዎቸቸውም ነቅለን እናመጣለን እያሉ ጦርነቱ እንዴት እንደሚመሩና ወጣቱም እንዴት እንደሚከተላቸው ቅስቀሳና መግለጫ በመስጠት ተጠምደው መሰንበታቸው ዝግጀታቸውን እንዳጠናቀቁ የሚያመላክት ነው፡፡
ስለዚህ የፌደራል መንግስትና የኢትዮጵያ ህዝብ በትግራይ ህዝብ ላይ እየተሸረበ ያለው ደባ ትክክለኛ ግንዛቤ ወስደው ግልፅ አቋም እንዲይዙይጠበቃል፡፡በተለይ መሰርይነቱን የሚያንቀሳቅሱት የተወሰኑ የአማራ ፖለቲከኞችና ልሂቃን ቢሆኑም በየመዝናኛ ቤቱ ፣ በየባህል ምሸትና በየስብሰባ አዳራሹ እየተደመጡ ያሉት የጦርነት ዳንኬራዎችየአማራ ህዝብ በቀጥታ እየተከታተላቸው ስለሆነየሁለቱ ክልሎች ንፁኀን ዜጎችየጥፋቱ ሰለባ ከመሆናቸው በፊት ለሰላማዊ መፍትሄ ጊዜው አልመሸምና የተቻለውን ያደርጋል የሚል ተሰፋችን ገና አልተሟጠጠም፡፡

 

No comments: