ከሰላምወርቅ ሁላገር
ዛሬ ስለራሳችን
ስለ አማራና አማራነት
መረር ያለ እውነትን በልኩ
ተነጋግረን ወደ ዘላቂ
መፍትሔ መምጣት አለብን
የሚል እምነት አድሮብኛል።
ስለ አማራ ህዝብ ከሩቅም
ከቅርብም፣ በውጭም፣ ከራሱ
ከህዝቡ በወጡ ሰዎችም
ጭምር ብዙ የተወላገዱ
አስተሳሰቦች መኖራቸው
እሙን ነው። አሁን እኛ
ከራሳችን በላይ ጥብቅና
የምንቆምላቸው የድሮ ገዢዎቻችን
በፈፀሙት በደል ህዝቡ
በሌሎች ህዝቦች በትርፍ
ተጠቃሚና አልፎ አልፎም
ራሱ ገዢ ተደርጎ የሚታይበት
ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል
አሁንም አለ። ከተሳሳተ
የታሪክ ንግርት ተነስተው
ተበድለን ነበር የሚሉ
ወገኖች ሒሳብ በዚህ ምስኪን
ህዝብ ለማዋራረድ ግዚያቸው፣
ገንዘባቸው፣ ጉልበታቸውና
ሙሁራዊ ህሊናቸውም ጭምር
ሲያባክኑ እናያለን። ገዢዎችና
ጨቋኝ መደቦች የአማራን
ህዝብ መጠቀምያ ለማድረግ
ለዘመናት ማንነቱ ረስቶ
የወል ካባ አስተሳሰብ
አልብሰው በራበው አንጀቱ
እነሱ በበሉት እንዲያገሳ፣
በታረዘው ሰውነቱ እነሱ
በለበሱት ተኩራርቶ በተበጫጨቀችና
አፈር መስላ በቆሸሸች
ነጠላው አፉንና አፍንጫውን
ሸፍኖ ቀብረር እንዲል፣
እነሱ ለዝናቸው፣ ለሃብታቸው፣
ለልጅ ልጃቸው ክብርና
ለንግስናቸው ብለው የሚለኩሷቸው
የእስ በርስ ጦርነቶች
ጧሪ አልባ የሆኑ ቤተሰቦቹን
ትቶ ወደ ጦርነቱ እንዲማገድ
በማድረግ ከሞት የተረፈውን
“እገሌ ገዳይ” እያለ እንዲፎክርና
ከሌላ የተለየ እንደሆነ
ለማሳመን ለዘመናት በሰሩት
ስራ እውነተኛ ማንነታችን
አጥተን እኛ ብቻችን አገር
ሙሉ ኢትዮጵያ፣ ሌላው
ኢትዮጵያዊ፤ እኛ መሪ
ሌላው ተከታይ፣ እኛ ጀግኖች
ሌላው ደካማ፣ እኛ ትልቅ
ህዝብ ሌላው ከኛ ካሉ ደረጃዎች
በታች፣ የኛ አስተሳሰብ
ሰፊ ሌላው ጠባብ በመሳሰሉት
የተዛቡ ምስሎችና ትርክቶች
በአየር እንደተሞላ ፊኛ
ወጥረው ሲያንከባልሉን
ቀይቷል።
ሌላው ቀርቶ
ራሱን ከመሰሉ የተጨቆኑ
ህዝቦች ጋር በመሆን ታግሎ
ያመጣው የ1983 ለውጥ ተከትሎ
ባለው የፌደራል ስርአት
ውስጥ አማራዊ ማንነቱ
እንዲከበር የተደረገ ጥረት
እንኳን ድርጊቱ ከፋፋይ፣
ስርአቱም የሌላ “የጎጠኞች”
ስርአት እንደሆነ ማሰቡም
ሆነ እስካሁንም እየተቃወሙ
ያሉ ወገኖቼ አብዛኛዎቹ
ይመስሉኛል።
አሁን አሁን
በተወሰነ ደረጃ ማንነታችንን
ለመፈለግ የሚደረጉ ሙከራዎችና
አደረጃጀቶች በበጎ ጎናቸው
መታየትና መደገፍ ያለባቸው
ሆነው ሳለ ብዙዎቹ እውነተኛ
ማንነታችን ለማስከበርና
ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ
ሳይሆን በአደረጃጀት እና
በትግል ስልት ብሔራዊ
ግን ደግሞ የገዢዎች ማንነትና
ታሪክ ለማስመለስና በራሱ
ህዝብና በሌሎች ህዝቦች
ከፍተኛ በደል ለፈፀሙ
ገዢዎች ክብርና እውቅና
ለመስጠት ያለመ ሆኖ እናገኘዋለን።
ስለሆነም ትክክለኛ አማራዊ
ማንነታችን ለማግኘት እውነተኛ
ትግል ገና ያልጀመርነው
መሆኑንና ትግሉም ከእያንዳንዳችን
ቤት ብቻ ሳይሆን ከራሳችን
ሰውነትና ስብእና ላይ
መጀመር እንደሚገባን
የሚያሳይ ነው።
ከቅርብ ግዜ
ወዲህ በኛ ጉዳይ ተደጋግመው
እየተነሱ ባሉ ጉዳዮች
ከሌሎች ብሔር ተወላጆች
በላይ የእውቀት ጣርያ
ደርሰናል በሚሉ አማራዎች
ሌላው ቀርቶ በዚህ ባለንበት
አገራዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ
ሆነው እንኳን “አማራ የሚባል
ብሔርም ጎሳም የለም” የሚል
ክርክር ማጧጧፋቸው ሁላችንም
እኔ ማነኝ? እኛስ ማነን?
እንድንል አስገድዶናል።
ደግነቱ መንግስቱ ኃይለማርያም፣ፕሮፌሰር
መስፍን ወልደማርያም፣አንዳርጋቸው
ፅጌና ሌሎችም “አማራ የሚባል
የለም” ባሉበት ዲስኩራቸው
የሚገልፁዋቸው ታሪካዊ
መሰረቶች የተለያዩ መሆናቸው
ነው።
እኛ ለምንድነው
ራሳችንን ሆነን ራሳችንን
መስለን ራሳችንን መግለፅ
የማንችለው? ማንነታችን
ማሳወቅ፣ ማንነታችን ማስከበር
የማንችለው? ብዙዎቹ የአማራ
የፖለቲካ ኃይሎች፣ የአማራ
የታሪክ አዋቂዎች(ሙሁራን)
የአማራ ማንነት ላይ ተመስርተው
መደራጀት አይፈልጉም።
በአማራና አማራዊነት ተመስርተው
መፃፍ አይፈልጉም። ሁሉ
ግዜ በኢትዮጵያዊነት ካባ
ውስጥ መኖር ይፈልጋሉ።
በጎውም ጉድለቱም የአማራን
ታሪክ፣ የአማራን ተጋድሎ
በኢትዮጵያዊነት ታሪክ
ውስጥ ተድበስብሶ እንዲቀር
ያደርጋሉ። በመሆኑም እንደሌላው
ህዝብ ሁሉ የኔ የሚለው
ማንነት፣ የኔ የሚለው
ታሪክ፣ የኔ የሚለው ባህል
እንዳይኖረው ከማድረግ
ጀምረው በድፍረት ደጋግመው
“እንዲህ የሚባል ህዝብ
የለም” እስከ ማለት ደርሷል።
በሌላ በኩል
ደግሞ እነኝህ ሰዎች ራሳቸው
“አማራ የሁሉም የበላይ
ነህ” አማራን የመሰለ ተኳሽ፣
አማራን የመሰለ ቀዳሽ፣
አማራን የመሰለ አራሽ፣
አማራን የመሰለ ፈዋሽ
የለም እያሉ በማወደስ
ኢትዮጵያ ማለት አንተ፣
ኃይማኖት ማለት አንተ፣
ባንዴራ ማለት አንተ ነህ።
ስለዚህ እንዳንተ ያለ
ትልቅ ህዝብ የለም ይላሉ”።
ሌላውስ? ለሚለው ሌላው
ሁሉ ባንዳ፣ ገንጣይ፣
አስገንጣይ፣ አንዳንዱ
ደግሞ ከሩቅ ደሴት የመጣና
ጥቂቶቹ ደግሞ ላንተ አገልጋይ
እንዲሆኑ የተፈጠሩ ናቸው
ብለው የውስጥ እቃው በሙሉ
በንፋስና አቧራ ሞልተው
ካሳበጡት በኃላ በማንኛውም
ግዜና ሁኔታ ዙፋናችው
የሚነቀንቅ ሁኔታ ሲፈጠር
“ኢትዮጵያ ተነስ!” ብለው
ጠመንጃ ነካሽና ቋሚ ዘበኛቸው
አድርገውት ኖረዋል አሁንም
በአብዛኛው የአማራ ልሂቅ
ከዚህ ስር የሰደደ በሽታ
መላቀቅ ያልቻለ እንደሆነ
ይሰማኛል።
በዚህ ዙርያ
አማራውንና ሌላውን ቀጥቅጠው
የገዙ፣ ስጋውን ግጠው
በአጥንት ያስቀሩ የአማራውን
ማንነት የወከሉ ገዢዎቻችን
ዋናው መገለጫ ሲሆኑ ከጥንት
ከቀደምት ጀምሮ በታሪክ
ተመራማሪነትና ደራሲነት
የሚታወቁ ስማቸው የገዘፉ
የአማራ ሊሂቃን ስራዎቻቸው
በሙሉ ካየነው አንዳንድ
የቦታ ስም ሊጠቅሱ ካልሆነ
በስተቀር አማራዊ ማንነትን
አይነኩም። አይነኩም ብቻ
ሳይሆን እንዳይነካቸው
ይፈሩታል።
አሁን ወዳለው
ሁኔታ መለስ ብለን እንይ
ከተባለ የሩቁን ትተን
በአሁኑ ስዓት ፌስቡክ
ወይም ዩቲዩብ ስትከፍት
ስማቸውና ፎታቸው ከፊት
ለፊት ድረ-ገፆች ከማይጠፉት
መካከል ፕሮፌሰር መስፍንና
አንዳርጋቸው ፅጌ የትውልድ
ማንነታቸውና አስተዳደጋቸው
የራሱ የሆነ ሳንካ ነገር
ያለው ቢሆንም አማራዊ
ስነልቦና በውስጣቸው እየታየም
ቢሆን ለሆነ ምክንያት
አማራ የለም ይሉሃል።
እና “ኢትዮጵያ ብቻ ብለህ
አስብ፤ በዚህ ደረጃ ካላሰብክ
አንተም እንደ ዘቀጡት
ዝቃጭ ነህ” ይሉሃል። እነ
ዶክተር ዳኛቸው፣ ልደቱ
አያሌው፣ እነ ዶክተር
ደረጀ ዘለቀ፣ እነ ኢንጅነር
ይልቃል፣ እነ ታማኝ በየነ፣
አበበ ገላው፣ ሃብታሙ
አራጌ፣ ሃብታሙ አያሌው፣
እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን
ደሳለኝ፣ ሄኖክ እያልኩ
ብዙ አስርት ሺ ሰው እጠራለሁ።
ከግል ሚድያዎችም ብዙ
በጣም ብዙ እንደነ ኢሳት፣
አባይ ሚድያ፣ ዘሐበሻ
ወ.ዘ.ተ እና ብዙ ተከታይ
ያላቸው እንደ ኢትዮጵያን
ዲጄ የመሳሰሉ ነገረ ስራቸው
ትግላቸው ሁሉም ለአማራው
የወገነ ሆኖ ሳለ አማራዊ
ማንነታቸው መግለፅ፣ በግልፅ
በአማራው ስም የተደራጀ
የፖለቲካ ፓርቲና ሚድያ
አደራጅቶ በህዝቡ ላይ
የሚደርሰውን ችግር መታገል
አይፈልጉም። የነሱ ማንነት
ድሮ ተሰፍቶ የተሰጣቸው
ትልቅ ኢትዮጵያ የሚባል
ማንነት አለ።
እኔም ሆንኩ
እናንተ ብዙዎቻችን በጣም
የምናደንቀው አንድ በታዋቂው
የአሜሪካ የጠፈር ማእከል
NASA ሲሰራ የነበረ አሁን በህይወት
የሌላው ድንቅ የአማራ
ልጅ ኢንጅነር ቅጣው እጅጉ
በዚህ ሁሉ ምጡቅ አእምሮው
ሳይቀር ይችን መሻገር
አቅታው ለኔ የሚመጥነኝ
ባለው “ትልቅ የኢትዮጵያ
ማንነት” ወስጥ ገብቶ ነው
ህይወቱ ያለፈው። እሱ
“ይህንን መንግስት በማንኛውን
ሁኔታ መታገል ያስፈልጋል”
ብሎ ስያስብ የኢትዮጵያ
ብሔራዊ አንድነት ግንባር(Ethiopian
national united front) የሚል ድርጅት መስርቶ
ግዜውን፣ ገንዘቡንና ጉልበቱን
ሲያፈስ ስሜቱ የአማራ
ማንነት፣ አላማው በኢትዮጵያ
ማንነት ስም የአማራን
ጥቅም ያስጠብቃል ብሎ
ባሰበው ሲታገል ቢታይም
የአማራነት ማንነቱ ስም
ሳይጠራ ህይወቱ አለፈ።
የእነዚህና
የሌሎች ተመሳሳይ አስተሳሰብና
ተግባር ያላቸው ሰዎች
ውስጣዊ ስሜት ምን ይሁን
ምን የዚህ ተግባር የመጨረሻው
ግቡ ሄዶ ሄዶ የሚወድቀው
አማራውን እንደ ሌላው
ህዝብ ቀጥቅጠውና አንቀጥቅጠው
የገዙትን እንዲሁም ባልበላውና
በማያውቀው በሌላው ህዝብ
ዘንድ በላተኛ አድርገው
በሁለት ቢላ ያረዱትን
የገዢ መደቦችን ጥቅም
የሚያስጠብቅ መሆኑ አንድና
ሁለት የሚባል የለውም።
በእርግጥ እዚህ ላይ መነሳት
ያለበት መነሻቸው አሁንም
ሌላ ጠላት ፍለጋ፣ በቀል
ፍለጋ ስለሆነ ተመልሶ
ያንን ስህተት የሚደግም
ሆነ እንጂ የመአህድ፣
የአዲሃንና አብን ብያንስ
በግልፅና ፊትለፊት ብሔራዊ
ማንነታቸውን ይዘው መደራጀታቸው
እንደ አንድ በጎ እርምጃ
እወስደዋለሁ።
አሁን አሁን
ደግሞ ከዚህ በላይ የከፋ
የህዝቡን ማንነትና ስነልቦና
የማይገልፅ በማንነታችን
ልንሸማቀቅ የሚጋብዙን
አስተሳሰቦች እየተራመዱ
ናቸው። ከህዝቡ ወጣን
የሚሉና ለህዝብ እየታገልን
ነን የሚሉ ግብዞች የአማራን
ህዝብ የማንነትነት ስነ
ልቦናው ቀብረው ተስፋችንና
እምነታችን ሌሎች ላይ
እንደሆነ ለማሳየት እየተንቀሳቀሱ
ናቸው። ከምንታወቅበት
የእንግዳ ተቀባይነት ባህላችን
ወርደው የአሽቃባጭነት፣
አሽከርነትና ተላላኪነት
ባህሪ በተደጋጋሚ በማሳየት
የተሳሳተን ነገር እንደ
የማንነታችን መገለጫ ተደርጎ
እንዲታይ ይተጋሉ። ይህ
ከክልሉ ገዢ ፓርቲ ከፍተኛ
አመራሮች የሚጀምር ቢሆንም
በብዙ ፖለቲከኞቻችን፣
አክቲቪስቶቻችንና ምሁሮቻችን
እየተበራከተ መጥቷል።
በፍፁም አማራ
ጠልነቱና የኤርትራዊያን
ህፃናት ልጆች ሲያለቅሱ
ወይ ሲረብሹ “አማራ መጣብህ/መጣብሽ”
እያሉ በማስፈራራት አማራን
ከአያጅቦ እኩል እንዲታይ
በልጆች አእምሮ ተቀርፆ
እንዲያድግ ያደረገውን
ጠላታችን አቶ ኢሳያስ
አፈወርቂ ጎንደር የመጡ
እለት እዛው ነበርኩና
“ክቡር ፕሬዝዳንት ኢሳያስ
በህወሃት መቃብር ላይ
የመሰረት ድንጋይ ጣልልን”
የሚል አየሁ። ሌሎች “ወዲ
አፎም” በሚል ቁልምጫ ከፊት
እያስቀደሙ ቀጥለው የነበሩ
ቃላቶች ስታይ እንዲሁም
በቅርቡ ከሃይማኖት ጋር
በተያያዘ ከአንዳንድ ፅንፈኞች
መካረር ተፈጥሮ ወደ ሰልፍ
ስንገባ አሁንም ጎንደር
ላይ የቭላድሚር ፑቲንና
የራሻ ጳጳስ ምስል በባነር
በማሰራት እንደሚያግዙን
የሚገልፅ ሃሳብ ተፅፎበት
አደባባይ ወጥቷል። የሚገርመው
ነገር ይህ ሁሉ እየሆነ
ያለው ሰልፍ ለወጣንበት
አላማ በፅናት የቆሙና
እየታገሉ ያሉ የአገራችን
ጳጳስ ስምና ፎቶ በማይገኝበት
“ሃይማኖታዊ” በተባለ ሰልፍ
ነው።
ከዚህ በወረዱ
ሃሳቦችና ድርጊቶችም የህዝቡን
ክብርና ማንነት ዝቅ የሚያረጉ
ጉዳዮችም ታዝበናል።
“አከሌ የተባለ ትግሬ ልሙጠን
ባንዴራ ይዞ ሰልፍ ላይ
ተገኘ እልል በሉ፣ አከሌ
የተባለ የኦሮሞ ተወላጅ
ምኒሊክን የሚያወድስ ንግግር
አደረገ ኢትዮጵያችን ከፍ
አለች፣ አከሌ የተባለ
የሌላ ክልል ተወላጅ አምባሳደር
የሹመት ወረቀት ለአገሪቱ
ፕሬዝዳንት ሲያቀርብ እንዲሁም
ጃዋርና ብርሃኑ ነጋ የአጼ
ቴድሮስ ልብስ ጃኖ ልብስ
ለብሰው ታዩልን ብሎ በአማራ
መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር
እንደ ድንቃድንቅ አንዳንዴም
እንደሰበር ዜና መቀወጥ
ከምን የመጣና ለምንድነው?
እኛ ግን?
ከላይ በመነሻነት
ለመግለፅ እንደሞከርኩት
ብአዴን/አዴፓ የአማራ
ህዝብ የማይመጥን የተላላኪነትና
አጃቢነት ፓርቲ በመሆን
የቆየባቸው የዘመናት ርዝመት
እንደ ስራ ልምድ ተቆጥሮበት
አገር ለመምራት ደረጃ
ባያደርሰውም በዚህ በተላላኪነት
ረገድ የመሪነት ደረጃውን
ለሌላ አሳልፎ ባለመስጠት
የኢህአዴግ አባልነቱን
አስጠብቆ ቆይቷል። አሁንም
አለ። ለብአዴን ምንም
ነገር ቢሆን የሚመዘነው
“መሪዎች” ከሚባሉ ሰዎች
ስልጣን፣ ምቾትና ክብር
በታች ነው። የአማራ ህዝብ
ጥቅም ብቻ አይደለም የራሱንም
ክብርና ጥቅም በመሸጥ
በውጭ ገፅታው የውሸት
ክብር ለማግኘት የሚኳትንና
በዛም የሚረካ ድርጅት
ነው።የሩቁን ትተን በለውጥ
ሃዋርያ ስም ኦህዴድ እንደ
ቆመ ሃወልት ሲጫወትበትና
የአማራን ህዝብ ጥቅምና
ፍላጎት ለድርድር በማቅረቡ
ደመቀ ከዚህ ቀደም ተቀምጦ
ጌም ሲጫወትበት ይውል
የነበረ ወንበር ሌላ ሰው
እንዳይቀመጥበት የማድረግ
እድል አግኝቷል።
ባለፈው የደሴ
ህዝብ ባገኘው መድረክ
ብአዴን አስቀድሞ ማንሳትና
መታገል ሲገባው ባለማድረጉ
ህዝቡ በድፍረት ለአብይ
“አገሪቱ በኦሮሞ የበላይነት
ለምን መተካት ፈለግክ”
ብሎ ሲጠይቅ አብይም “አንድ
ትርፍ የኦሮሞ ሹመኛ ካመጣቹ
ስልጣኔን ልልቀቅ” በሚል
በሚድያ ለሰማው የሚያዝናና
መልስ ሲሰጥ የአማራው
ልጅና የአማራ መሪ ደመቀ
ጠ/ሚንስትሩ ለህዝቡ ለሚሰጠውን
መልስ ማስታወሻ ሲይዝለት
ነበር።በኃላም ካባ አልብሶ
አጅቦት ተመልሰዋል። በማህበራዊ
ሚድያ አብይ ሁሉም ነባር
አጃቢዎች እንዲባረሩ ካደረገ
በኃላ ደመቀ የተባለ አንድ
ሰው አስቀረ ተብሎ እስኪተረትለት
ደረሷል። “አብይ ቤተ መንግስቱን
አሰርቶ ለቱሪስት ክፍት
የሚያደርገው ለመጎብኘት
ከተዘጋጁት ውስጥ ደመቀ
የሚል ስም የወጣለት ለማዳ
እንስሳ አንዱ መነሻ ስላለው
ነው” የሚል የሚያስቅም
የሚያናድድም ቀልድ ሰምተናል።
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ
አንተነትክን መንካቱ ስለማይቀር
ነገሩ በጣም ያበሳጫል።ሌላው
ግን እውነት ነው የምላቹ
እንደ ታማኝ በየነ በአሜሪካ
መሬት ላይ ወድቆ የአብይን
ጫማ እንደመሳም ናላየ
ያዞሮው ግን አልነበረም።
በአማራ ክልል
አመራሮች ግድያ ወቅት
ገዱ ቃል በቃል እንደነገረን
አዴፓዎች “በአማራ ህዝብ
ጥያቄ ዙርያ በሁሉም አዴፓ
ልዩነት አልነበረም” ብሎናል
ስለዚህ የጠባቸውና የመበላላታቸው
ምክንያት ከአማራ ህዝብ
ጥቅም ውጭ እንደሆነ ነው
ያስረዳን። “ከእንግዲህ
በኦሮሞ መንገድ ብቻ ነው
ስልጣንንና የግል ምቾትን
ማስጠበቅ የሚቻለው” ብሎ
ያሰበ የአዴፓ/የብአዴን
አመራር የአዲስ አበባን
ጉዳይ ጨምሮ በበርካታ
የህዝቡን ጥቅም በቀጥታ
በሚነኩ ጉዳዮችን በመድረክም
ሆነ በመግለጫ እንኳን
ሳያወግዝ ሊቀመንበር ደመቀ
መኮነን አምቦ ተገኝቶ
ቄሮ ነፃነት ስላመጣህልን
እናመሰግናለን ሲል በርካታ
የብአዴን አመራር ደግሞ
ቄሮ አሸባሪ ነው ይላል።እንዲያና
እንዲህ እያሉ ይቀጥላሉ
እኛም እንቀጥላለን። ግን
ለምን?
በአጠቃላይ
እስከአሁን ከተዘረዘረው
ሁኔታ አንፃር የአማራ
ህዝብ ጠላቱ ማነው? ህወሃት?
የትግራይ ህዝብ? ኦዴፓ?
አሮሞ? ቅማንት? ግብፅ? በኔ
እምነት ሁሉም አይደሉም።
የአማራ ህዝብ ጠላቱ ከላይ
ጀምሬ ስዘረዝራቸው የቆየሁ
ከማንነታቸው መጥላት ጀምሮ
ህዝቡን ያስጠቁና ያስናቁ
ያሉ የሱ የራሱ ልጆች ናቸው።
በታሪክም በአሁናዊ ሁኔታም
አይደለም የትግራይ ህዝብ
እንደ ህዝብ ህዋሃትም
የአማራ ህዝብ ጠላት አይደለም።
አዴፓ ታድያ ምን እያለን
ነው? “ትህነግ ሲፈጠር ጀምሮ
የአማራ ህዝብ ጠላት ነው”
ብሎናል። ሚጣ ልጄ እንኳን
አንድ ጥያቄ አላት “ታድያ
ያ ሁሉ ዘመን ለምን አብረህ
ከረምክ?ስለዚህ አንተም
ጠላት ነህ?” ብላለች። እዚህ
ላይ ግን አዴፓ በትህነግ
ስም ካወጣው መግለጫ በላይ
በታሪኩ አበጀህ ተብሎና
ተሞግሶ አያውቅም። ይህ
በራሱ እኛ ማነን? ምን እየሆን
ነው? የሚያስብል ስሜት
ፈጥሮብኛል። (በነገራችን
ላይ ለዚህ ሁሉ ጫጫታ የዳረገው
የህዋሃት መግለጫ ብአዴን
“ከተሃድሶ በኃላ ራሱ ያወጣው
መግለጫ እንደሆነ ተገንዝባቹሃል?
በራሱ ሚድያ አለላቹ እዩት።)
ብአዴንየ ለውጡ
ህዝቡ ቢደግፈውና ቢሳካ
የለውጥ ሃወርያት እኔ
አመጣሁልህ ለማለት፣ ለውጡ
እንደ ጋሼ በቀለ ማታ ማታ
ከጠጅ ቤት ሲወጡ አይነት
መቆምያ አጥቶ ግራና ቀኝ
ሲረግጥ ለውጥማ ለውጥ
ነበር አልረጋ ያለው በህዋሃት
ነው ለማለት፣ ለውጡ ህዝቡ
ለውጥ እንዳልሆነ አውቆ
መቃወም ሲጀምር ችግሩ
አብዮታዊ ዴሞክራሲ መሆኑ
ደርሸበታለሁ ለሰው የማልነግረው
አዲስ አማራጭ አለኝ ጠብቁኝ
ብሎ ከመዘላበድ ባለውና
በነበረው ሁኔታ ውስጥ
ሆነህም ቢሆን እስኪ ሰላም
አምጣ ፣ እስኪ ልማት አምጣ፣
እስኪ ዴሞክራሲ አምጣ፣
እስኪ መልካም አስተዳደር
አምጣ! ግን ከየት ታመጣሎህ
?
እንደገና ሳልወድ
ወደ ህዋሃት ልገባ ነው።
የአዴፓ መግለጫ ህወሃት
ሲጀምር ጀምሮ አማራን
በጠላትነት በመፈረጅ ትግል
እንደጀመረና ታሪኩም ከፋፋይ፣
ሴረኛና ዘረኛ እንደሆነ
ያትታል። የሰማሁትና ያነበብኩት
ከዚህ የተለየ ስለነበር
ከመግለጫው በኃላ አንድ
ህዋሃት ጠል እንደሆነ
ሁላችን የምናውቀው የኢህዴን/ብአዴን/አዴፓ
መስራች ጥሮተኛ ሰው የጤና
መታወክ ውስጥ ስላለ ገርጂ
በሚገኘው ኮርያ ሆስፒታል
አግኝቸው ረጅም ስዓታት
አውርተን የተረዳሁት ህዋሃት
በህዋሃት ጠሉ የድሮ አመራርም
የሚነግረንም ጭምር አንድ
ግልፅ ያለ እውነት አለ።
ህወሃት ከብአዴን/አዴፓ
መግለጫ በተቃራኒው የሆነ
ድርጅት ነው።
ህወሃት እንደ
አንድ ብሔራዊ ድርጅት
ሲመሰረት በማናቸውም የብሔራዊ
አደረጃጀት ውስጥ ያሉ
ድርጅቶች አድርገውት የማያውቁ
ከመስራቾቹ አንዱ የአማራ
ብሔር ተወላጅ እንደሆነ
መካድ አትችልም። አዎ
የህዋሃት “አማራ ጠል” የተባለው
ማኒፌስቶ ሲረቀቅና ወደ
ተግባር ሲሸጋገር አንድ
የሰሜን ጎንደር ተወላጁ
አማራ አብሮዋቸው ነበር።
ሌላው ከምስረታው ከአንድ
አመቱ ጀምሮ ያለ ምንም
ጥርጣሬ በርካታ የአማራ
ክልል ተወላጆች በብሔር
የተደራጀ ፓርቲ በዛ ክፉ
ዘመን አምኖ እነሱም አምነውት
ታግሏል። እኔን ያስገረመኝ
ነገር ማታገሉ አይደለም።
ልክ እንደ ብሔሩ ተወላጆች
ግዳጅ ይሰጣል፣ በአፈፃፀማቸው
ልክ እንደሌላው ያለ አድልዎ
ይመዝናል፣ ያለ አድልዎ
ሃላፊነት ይሰጣል። ለዚህም
አሁን በህይወት የሚገኝ
ወንድወሰን አስረጂ ነው።
ወንድወሰን አማራ ሆኖ
ከረጅም አመታት በፊት
ጀምሮ የህወሃትም ሆነ
ትግራይ ህዝብ እጣ ፈንታ
የመወሰን ስልጣም በነበረው
የማእከላዊ ኮሚቴ የተባለን
አካል አባል በመሆን ከገጠር
ትጥቅ ትግል እስከ መንግስት
ምስረታ የዘለቀ ሰው ነበር።
ሌላው አስገራሚ
የሰማሁት ታሪክ በ1972 አካባቢ
“ዘረኛ” ወደ ተባለው ህወሃት
የተቀላቀለው የወላይታ
ብሔር አባል ነው። ስሙ
ጰጥሮስ በለጠ ይባላል
እነሱ “ብሃበሎም” ብለው
ይጠሩታል። ይህ ሰው ከአሰልጣኝነት
ጀምሮ ከተዋጊነት አልፎ
ወደ አዋጊ አመራርነት
የደረሰ ሰው ነው። አሁን
በህይወት የሌላው ባመነችውና
ባመናት ድርጅቱ ውስጥ
በውግያ ህይወቱ መስዋእት
ያደረገው ባሃበሎም ወያኔ
ሻዕብያን በደርግ ከመደምሰስ
የታደገችበትን የቀይ ኮኮብን
ዘመቻ ካከሸፉት መካከልም
አንዱ ነበር። ሌሎች አሁን
ያሉትን እንደነ ጌታቸው
ሴኮቱሬና አዜብን የመሳሰሉ
የአማራ ብሔር ተወላጆችን
አቅፎ እዚህ የደረሰ ድርጅት
መሆኑን ለመረዳት ታሪክንና
እውነትን በእውነትነቱ
ለመስማትና ለመቀበል ዝግጁ
መሆንን እንጂ ብሔርን
አይጠይቅም። እኔ ያደረግኩት
ይህንኑ ነው። እዚህ ላይ
እንዳትሳሳት ወዳጄ ኢህዴን
ከዛ በላይ የብሔር አባላት
እንደነበሩት ለንፅፅር
እንዳታቀርብ። ኢህዴን
ህብረ-ብሔራዊ እንጂ ብሔራዊ
ድርጅት አልነበረም። በኃላ
ብአዴን ሲሆን ከመጡበት
ሁኔታና በክልሉ ከመወለዳቸውም
አንፃር እነ በረከትን
መቀበሉ አሌ አይባልም።
ታድያ ዘረኛው ማነው?
እኔ እንደማንኛውም
ሰው ሰው በመሆኔ በማንነቴ
ልደራደር አልችልም። የኔን
ማንነት ተገን በማድረግ
በሌሎች ማንነቶች ጥቃት
ለማድረስ የሚንቀሳቀስን
ኃይል ደግሞ በዛው ልክ
አጥብቄ እቃወማለሁ፣ እታገለዋለሁ።
የምቃወመው መጀመርያ ሰው
በመሆኔ ሲሆን በሌላ በኩል
ደግሞ ይህ ሰው ከሰው የወረደ
አስተሳሰብ ስላለው ነገ
በአንድ ማንነት እያለንም
ቢሆን ያንተ የቀይና የነጭ
ደም ሴል ከኔ ይለያል።
ወይም ቁጥሩ ላይ ልዩነት
አለው በማለት ሊከፋፍለኝ
ወደኃላ እንደማይ ስለማውቅ
ነው። በመሆኑም በቅማንት
ብሔረሰብ እየደረሰ ያለው
ግፍና ኢሰብአዊ ተግባር
እቃወመዋለሁኝ።
በቅማንት ህዝብ
የሆነው ምንድነው? ቀደም ሲል ገዱ
አንዳርጋቸውና ግዛት አብዩ
በዚህ ህዝብ ላይ ያወረዱት
ግፍና መከራ ከ- እስከ ተብሎ
የሚገለፅ አይደለም። ሌላው
በህይወት ስለሌለ ነብሱን
ማረውም አትማረውም በሚል
በሱና በእግዚአብሔር መካከል
መግባት የማልፈልገው አሳምነው
ፅጌና ተከታዮቹ ቅማንትን
እንደ ህዝብ እንዲንበረከክ
ወይም እንዲጠፋ በሚል
ፍርድ በይነው ይህንን
ለማድረግ ወደ ተግባር
ገብተው ግድያ ሳይሆን
ጥፍጨፋ ለማካሄድ ተንቀሳቅሰዋል።
በ2008 አከባቢ ይመስለኛል
ገዱና ግዛት ለክልሉ የፀጥታ
አካላት አዘው ከሁሉም
አከባቢ የሚሊሻ ሃይል
አሰባስበው ሽንፋ በተባለ
ቦታ ሴት፣ ህፃን፣ አዛውንት፣እንስሳት፣
ቤት ከነቁሳቁሱ ሲያጋዩት
በጣም ዘግናኝ ሁኔታ ነበር።
በኃላ ቅማንት ተደራጅቶ
መከላከል ሲጀምር ጨፍጫፌው
ኃይል ተበታተነ። በዚህ
ወቅት ከተሰሙ በጣም የሚዘገንኑ
ክስተቶች መካከል አንዲት
የቅማንት እናት ምላሳቸው
መቆረጡ ሲሆን በወቅቱ
መተማና ሽሂዲ የነበሩ
የአማራ ተወላጅ ሽማግሌዎችም
ጭምር ያስለቀሰ ጉዳይ
እንደነበር ብዙ ሰው የሚያስታውሰው
ነው።
ከዚህ ቀጥሎ
ሮቢት ማውራ የተባለ የቅማንት
መንደር ገብቶ ቅማነቶችን
ልክ አስገብቶ እንዲመለስ
ከነ ገዱና ግዛት የተላከ
የአምባጓሮ(ልዩ) ኃይል
የአገር ሽማግሌዎች ጭምር
አትሂዱ ሲሏቸው ታዘናል
በሚል ወደ መንደሩ ሲገባ
የቅማንት ገበሬ ተደራጅቶ
መመከት ብቻ ሳይሆን ልዩ
ኃይሉ ገብቶበት ከነበረ
ቦታ ሸሽቶ ከሩቅ በመሆን
በረጅም ርቀት መሳርያ
ወደ መንደሩ በመተኮስ
እንደተለመደው በጎጃቸው
የነበሩ ህፃናትና ልጆች
ገድሎ ወደ ጎንደር ከተማ
ሲመለስ አሁንም አሳዛኝ
ክስተት ተከሰተ ልዩ ኃይሉ
በተኮሰው መትረየስ ቤትዋ
ተኝታ የነበረች አራስ
እናት ከተወለደው ህፃን
ጋር ተገድለዋል።
ይህንን ጉዳይ
በቅማንቶች የተለየ ቁጣ
ስለቀሰቀሰ ከፍተኛ የመንግስት
ተወካዮች ቀበሌዋ ድረስ
መጥተው ስብሰባ ሲያካሂዱ
እንዳይገባብን ካሉት ገዱ
በስተቀር ደመቀን ጨምሮ
አብዛኛው የብአዴን አመራር
ይህንን ችግር መከሰቱ
አረጋግጦ እንደ አዲሱ
ለገሰ ያሉትን ደግሞ ከህዝቡ
ጋር አብረው አልቅሰው
ተምልሰዋል። በወቅቱ እኔ
አባቴ ታሞ ጎንደር ስለነበርኩኝ
ከልዩ ኃይሉ አባላት አንድ
ሰው አግኝቸ ሳነጋግር
“እንዲህ አድርጎ ያባረረን
ኃይል የቅማንት ሊሆን
አይችልን።ሌላ መንግስት
ያላወቀው ኃይል አለ” ካለኝ
በኃላ ቅማንት የምናውቀው
እንኳን ከአማራ ከሌላም
ጋር ከሰው እኩል የማይቆጠር
ልብሱ እንኳን አፅድቶ
የማይለብስ ይህንን ማድረግ
አይችልም ብሎ ያደግንበትን
ተረት ደገመልኝ። ከዘህ
ቀጥሎ በተናጠል የተገኘን
ቅማንት እየታገተና እየታረደ
የተገኘ ብዙ ነው።
ሌላ ግዜ ሁሉም
ነገር ወደ ቅማንት! ተብሎ
በክልሉ የተነሳሳ ኃይል
ሽሄዲ መሰባሰብ ጀምረዋል።
ከክልሉ ያልተገኘ ታጣቂ
ከሰሜን ሽዋ ብኛ እንደነበር
ሰምቻለሁ። በወቅቱ የገባ
ኃይል ቍጥሩ፣ ፉከራው፣
ስንቁ ወዘተ የ1990 የሻዕብያ
ወረራ ለመቀልበስ የተደረገ
ዝግጅት ያስንቃል። በተለይ
እንደ ነገ ለመዝመት እንደ
ዛሬ ማታ የታረዱ በሬዎች
የተበላ ስጋና የተጠጣ
ዳሽን ቢራ ቁጥር የሽሄዲ
ህዝብ ዛሬም ድረስ በግርምት
ያነሳዋል። ታድያ በነገታው
71 መኪና ተጭኖ ወደ ቅማንት
መንደር ጉዞ ሲጀመር ኮነሬል
ተራራ በሚባል ቦታ ሲደርስ
ቅማንቶች በመሃል ገብተው
መኪኖቹን ለሁለት በመክፈል
ጥቃት ሲሰነዝሩ ወደኃላ
የነበረ ሃይል ሽሄዲ ለመግባት
የወሰደበት ግዜ አስገራሚ
ነበር። ሌላውስ ካላቹ
ከሙት የተረፈው በእነ
ገዱ ጥያቄ በመከላከያ
ሽንግልና ተሰብስቦ ወደየ
ሚስቱና ልጆቹ ተመለስ
ሲባል ሁሉም የሚደጋግማት
አንዲት ቃል ናት። ይህ
ሃይል የቅማንት አይደለም።
የከፋ የመጣው
“ለውጥ” መጥቶ አሳምነው
ፅጌ ተፈቶ የፀጥታ ሃላፊ
ሆኖ ከተመደበ በኃላ ሲሆን
ቀጥ ብሎ ነጋዴ ባህር በተባለ
ቦታ አማራውን ለይቶ ስብሰባ
በማድረግ ሁሉም ልምድ
ያለው ወታደር የነበረና
ሽፍታ የነበረ በሙሉ ይሰብሰብ
ተብሎ ከተሰባሰበ በኃላ
በሁለት አቅጣጫ አሳምነው
በበላይነት እየመራው ወደ
ቅማንት ሲሰማራ አይደለም
መሬት ሰማይም የሚቀር
አይመስልም ነበር። በወቅቱ
በነበረ እልቂት ቅማንት
መንደሩ ተቃጥሎ ብዙ ጉዳት
ቢደርስበትም፣ ህዝቡ በከፍተኛ
ደረጃ ቢፈናቀልም የቅማንት
ተዋጊው ኃይል ከአሳመነው
ሃይል እንደነ ሽባባው
አንዳርጌ የመሳሰሉ መሪዎች
ተብለው የተመደቡትን መርጠው
ከገደሉ በኃላ ሁሉም ነገር
መቆሙ ሰምተናል። በመሆኑም
በቅማንቶች ድል አድራጊነት
ተጠናቋል። እናም በዛ
ሰሞን አንድ የቆየ ዘፈን
ሲዘፈን ሰማን “ሌላ ኃይል
አለ”። በቅርቡ በጭልጋ
በነበረ ሁኔታም ይህ የማይሰለቸው
“አንድ ኃይል አለ” መዝፈን
ሲጀመር የጎንደር ህዝብ
“አይ አሁንስ በዛ ካሴት
ቀይሩ” በሏቸዋል።
አንድ የኢህዴን
ታጋይ የነበረ የቅማንት
ማህበረሰብ አባል አሁን
በጎንደር በአንድ ሆቴል
በጥበቃ ስራ የተሰማራ
ሰው ከጓደኛየ ጋር እንዳወራን
ድርጊቱ በሙሉ ደርግ በአንድ
ወቅት በትግራይ፣በሰሜን
ወሎና የተወሰኑ የሰሜን
ጎንደር ነፃ መሬቶች ሰውም፣
ቤትንና የቤት እንስሳትን
ቀላቅሎ በአውሮፕላን ያደረጋቸው
ጭፍጨፋዎች እንዳስታወሰውና
ለክልሉ ህዝብ ነፃነት
ብሎ ታግሎ ባመጣው ስርአት
ከመስዋእትነት ተርፎ ከድል
በኃላ የወለደውን ልጁን
እንደበላበት ሲናገር ያፈሰሰው
እምባ ሳስብ ቀጥሎ ስለሚሆነው
ነገር ሳወጣና ሳወርድ
እንቅልፍ በአይኔ ያልዞሩበት
ቀናት ነበሩ።
በዚህ ከቅማንት
ጋር የነበሩ ተደጋጋሚ
ግጭቶች የተሸነፈ ማነው?
የአማራ ህዝብ ወይስ የእነ
ገዱ፣ እነ አሳመነው ነውጠኛ
ሃይል? የተዋጋው አማራ
ስላልሆነ የተሸነፈው አማራ
አይደለም። የተሸነፈው
ነውጠኛው ነው። የተሸነፈው
ልማቱ ለራሱ ከበላው በኃላ
ህዝቡ “ልማት አምጣ” ሲለው
ማምጣት ሲያቅተው፣ የተለያየ
ወንጀል ፈፅሞ አገር ከተረጋጋ
በህግ እንደሚጠየቅ የሚያውቅ
የመንጀለኛው ኃይል ስብስብ
ነው። የአማራ ህዝብ ሰለባ
መሆኑ ግን አልቀረም።
አሁንም ህዝቡ በአዴፓ
ስም የተደራጀ ረብ የለሽ
ቡድንን በቃህ ብሎ ከውስጡ
አውጥቶ ካልተፋው ሌሎች
በርካታ ምጣዶች ጥዶ በባዶ
ትእቢት የተወጠረው ስሜቱን
ለማስተንፈስ እንደ እንጨት
ሊማግደው ዝግጅቱ አጠናቋል።
እኔና ሌሎች
ብዙዎቻችን የክልሉ ተወላጆች
ምን እየሆን ነው? እኛስ
ማነን? ለምንድነው ከሌላው
በተለየ እንዲህ እየሆን
ያለነው? ለምንድነው ነገሮች
እኛ ጋር እየጠነከሩ ያሉ?
ለምንድነው ሌላው ህዝብ
በኛ ህዝብ ላይ የተሳሳተ
እምነት እንዲኖረው የሆነ?
ለምንድነው በብዙዎቹ ክልሎች
ጥቃት የሚደርስብን? እያልን
እንጠይቃለን። አሁንም
አብዛኛው ሰው በተለይ
ወጣቱና የተማረው ሃይል
መልሱ የተሳሳተ ሆኖ አየዋለሁ።
አሁንም መልሱ “እነሱና
እኛ” ነው። ከህወሃት ለመበሻሸቅ
ብሎ የደርግ ስርዓት ሳይቀር
እንደራሱ ስርዓት ቀጥሮ
ይከራከራል፣ በአስተሳሰብም
በአደረጃጀትም የሚወክለው
ለሌላ አካል ሆኖ ሳለ ኦሮምያና
ደቡብ ትምክህተኛና ነፍጠኛ
ብለው ሲጣሩ “እኔ ነኝ” ብሎ
አቤት ይላል።
ስለዚህ የዚህ
ሁሉ ምክንያት ፈጣሪዎች
እኛ፣ ተጠቂዎችም እኛ
መፍትሄ ለማምጣት መወሰን
ያለብን እኛ እንደሆን
ውስጣችን ማሳመን ካልቻልንና
ጥቂቱን የአምባጓሮ ቡድን
ላይ ዘምተን ይህንን ከመሰረቱ
ቀይረን ህዝቡ ከሌላው
ወንድም የአገሪቱ ህዝብ
በፍቅር፣ በሰላም፣ በመተሳሰብና
በወንድማዊ ስሜት ማኖርና
ዘላቂ ጥቅሙ ማረጋገጥ
ይቻላል። ለግዜው ፈተና
ውስጥ መውደቁ ባይቀርም
ይህንን አስተሳሰብ የሚቀበልና
በዚህ አስተሳሰብ የሚመራ
የአዲሱ ትውልድ ፍሬ የሆነ
በአይነቱ አዲስ ፓርቲ
ያስፈልጋል። ይህ በሚሆንበት
ሁኔታ እኔም በታሪኬ ለመጀመርያ
ግዜ ፖለቲካውን ተቀላቅየ
የዚህ ፓርቲ የመጀመርያው
ተመዝጋቢ አባል እሆናለሁ።
No comments:
Post a Comment