Friday 29 November 2019

ኦሮማይ የኢህአዴግ ህልውና አከተመ፤ በቀጣይ እንዴት እንቀጥል?

ከህዳሴ ኢትዮጵያ

ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ አገረችን በርካታ በጎ ነገሮች ሰርቷል፡፡ በስራላይ ያለ እንደሚሳሳተው ሁሉ ኢህአዴግም የተሳሳተው ነገር ይኖራል፡፡ አገራችን ለዘመናት ከኖረችበት የድህነት እና ሀላቀርነት አዘቅት ለማውጣት በተደረገው ጥረት ኢህአዴግ ከፍተኛ ዕድገት በማስመዝገብ መጓች ህብረተሰብ ፈጥሯል፡፡  ነገርግን በአሁኑ ጊዜ ኢህአዴግ ይህን የተፈጠረው ሞጓች ህብረተሰብ ለማርካት የሚያስችል ቁመና ሊኖረው አልቻለም፡፡ ይህን ቁመና የመገንባት እና የማስተካከል ዕድል ተሰጥቶት ዕድሉ ሳይጠቀምበት ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ አለፈው፡፡ የኢህአዴግ ኮር አመራር የድርጅቱን ቁመና ከማስተካከል እና ከመገንባት ይልቅ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ውስጡን እርስ በራሱ መፋጀት መወነጃጀል ብሎም ድብቅ ሰራ መሸራረብ ስራዬ ብሎ ተያይዞታል፡፡ ይህ ድብብቆሽ የመጨረሻው የዕድገት ደረጃው ደርሶ እነሆ በዛሬው ዕለት የኢህአዴግ የመጨረሻ ዕድል መፈራረስ መሆኑ መርዶ ተነገረ፡፡ ኢህአዴግ በሁለት ተከፈለ፡፡ አንዱ የመደመር ፍልስፍና ይዞ በውህደት ስም አጋር ድርጅቶችን በማካተት የብልፅግና ፓርቲ ሲመሰርት፣ ሌላኛው ክፍል ደግሞ ህወሓት ሆኖ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ልማታዊ ዴሞክራሲ ፍቱን የአገራችን መድሀኒት ነው፣ አሁን አገራችን ኢትዮጵያ ከገባችበት ቀውስ የምትወጣም በዚህ መስመር ብቻ ነው ይላል፡፡ 

                                    ቪደዎው ከአክሱም ፖስት አዘጋጆች (ምንጭ YouTube)

በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ልማታዊ ዴሞክራሲ ይመሩ የነበሩ ኢህአዴግ እና አጋር ድርጅቶች አሁን ከስሟል፣ ኢህአዴግ ወይም አጋር የሚባል የለም፡፡ አሁን ያለው የብልፅግና ፓርቲ ወይም ህወሓት ነው፡፡ 
አሁን ያለን አማራጭ በቃ ካልተስማማን እስክንስማማ ተቻችሎ መኖር ነው፡፡ መዋሀድ አንድ ዓይነት ዓላማ ሲኖር ነው፣ አንድ ዓይነት መስመር ሲኖር ነው፡፡ የማይገናኙ አላማ ይዞ መዋሀድ ማለት እርስ በርስ እየተነታረኩ ጊዜ ማጥፋት ነው፡፡ መዋሀድ ውጤታማ የሚሆነው መተማመን ሲኖር ነው፡፡ ካልተማመኑ ቢዋሀዱም ሁሌም በጥርጥር፣ በተንኮል እየተሸራረቡ መኖር ነው፡፡ ስለዚህ የማይተማመኑ፣ የጋራ ዓላማ የሌላቸው ተዋህደው አንዱ ሌላውን እንቅፋት ከመሆን ይልቅ ተለያይተው ግን ደግሞ አንዱን የሌላኛው አመለካከት ባይቀበለውም አክብሮ መኖር አለበት፡፡ ስለዚህ የተለያዩና የማይገናኙ ዓላማና መስመር ይዞ በአንድ አገር መኖር የሚቻለው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተቻችሎና ተከባብሮ ነው፡፡ ለዚህም የአገሪቱ ሕገመንግስት በማክበር እና በማስከበር ነው፡፡
ከዚህ ውጭ ዕርቅ ወይም ሽምግልና የሚባለው ትክክል አይደለም፡፡ የግለሰቦች፣ የቤተሰብ፣ ወይም የቡድኖች ችግር ሲፈጠር በሽምግልና በእርቅ ቢፈታ የተለመደ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የተፈጠረው ልዩነት በግለሰቦች እና በአመራሮች ውስጥ የተፈጠረ ችግር ሳይሆን የዓላማ፣ የመስመር ልዩነት የፈጠረው ችግር ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ችግር ደግሞ የሚፈታው በዓላማ፣ መፕሮግራም በመስመር ላይ ሰፊ የውይይት መድረክ በመክፈ መቀራረብ የሚችሉ ማቀራረብ እንጂ በግለሰቦች እንደሚደረገው እርቅ ወይም ሽምግልና በማድረግ የሚፈታ አይደለም፡፡
እንደሚታወቀው በዶ/ር አብዪ እና በዶ/ር ደብረፂዮን በግላቸው የተፈጠረ ልዩነት ወይም ጥላቻ የለም፡፡ አብረው ይበላሉ ይጠጣሉ፣ ይጫወታሉ ይስቃሉ ኣብረው ይጓዛሉ፣ ስብሰባም ይቀመጣሉ፡፡ ነገር ግን አሁን በውህደት ላይ የተፈጠረው ውዝግብ ዋነኛው ምክንያት ሁለቱም ጎራ ይዘውት የመጡ የፖለቲካ አሰላለፍ ልዩነት ነው፡፡ ዶ/ር አብዪ ይዘውት የመጡ የመደመር ፍልስፍና ለአገራችን ትክክለኛ መፍትሄ ነው የሚል ሲሆን ዶ/ር ደብረፂዮን ደሞ አይሆንም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው የሚበጀው የሚል ነው፡፡
ይህን የተፈጠረው አለመግባባት መፍታት የሚቻለው በሁለቱም ሀሳቦች ያለውን አንድነትና ልዩነት በመዘርዘር ማቀራረብ በሚቻለው ማቀራረብ፤ ማቀራረብ በማይቻለው ደግሞ በልዩነት ይዞ ተቻችሎ መቀጠል ነው፡፡
አሁን እንደታዘብነው ከህወሓት በስተቀር ሁሉም የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች እና አጋር ድርጅቶች ውህደቱ ተቀብለው አፅድቆውታል፡፡ ህወሓት ይህን ትክክል እንዳልሆነ፣ እየተሳሳቱ እንደሆነና ለአገራችን እንደማይጠቅም አሁን እያየነው ያለ የሰላም እጦት፣ አለመረጋጋት እና የንሮ ውድነት የዚህ መደመር ውጤት እንደሆነ በይፋ ይገልፃል፡፡ በሌላው ወገን ደግሞ ውህደት እና መደመር ለአገራችን መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ እንደሆነ፣ አሁን በአገራችን እየታየ ያለው ችግር በለውጥ ሂደት ላይ የሚያጋጥም የተለመደ ክስተት ነው ይላል፡፡
እነዚህ አስተያየቶች ፍፁም ተቃራኒዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የሁለቱም ጫፎች አራማጅ ሃይሎች በዴሞክራሲ ግንባታ እስካመኑ ድረስ፣ በአገራችን ያለው የፖለቲካ ጨዋታ ህግ አሁን በስራ ላይ ያለው ህገመንግስታችን መሆኑ አምነው ለህገመንግስቱ ተገዢ እስከሆኑ ድረስ እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ተቻችለን ተከባብረን መኖር ብቻ ነው ፍቱን መድሀኒታችን፡፡
በሚቀጥለው ምርጫ የብልፅግና ፓርቲ፣ ህወሓት፣ እንዲሁም ሌሎች ተቃዋሚi ተፎካካሪ ድርጅቶች ሁሉም ለህዝብ ይጠቅማል የሚሉትን ነገር በነፃነት ያለምንም ጫና ወይም ያለምንም ገደብ ለህዝቡ በማቅረብ ህዝቡ የሚፈልገው እንዲመርጥ ዕድል ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሁላችንም የህዝብ ድምፅ ለማክበር ቃል ገብተን እንፈፅም፡፡ ከምርጫው ቦሀላ የህዝብ ይሁንታ ያገኘ አንድ ፓርቲ ወይም የጣምራ ፓርቲዎች አገሪቱን የማስተዳደር ሀላፊነት ተሰጥቷቸው ህገመንግስቱ በሚፈቅደው አገባብ አገሪቷን የማስተዳደር፣ የማልማት እና ዴሞክራሲው የማጎልበት ጥረቱ ይቀጥል፤ ሌሎች ያልተሳካላቸው ደግሞ በተፎካካሪ ወይም በአጋር ይቀጥላሉ ማለት ነው፡፡ ከዘህ ውጭ ሽምግልና እርቅ እየተባለ ሽማግሌ መላክ ተገቢ አይደለም፡፡ የዓላማ ና የመስመር ልዩነት በሽምግልና አይታረቁም፡፡ 
ስለዚህ ከአሁን ቦሀላ ኢህአዴግ፣ አጋር፣ ውህደት የሚባሉ አጀንዳዎች ይዘጉ፡፡ የምርጫ አጀንዳ ይከፈት፡፡ ያለፉት ሁለት ዓመታት ያሳለፍነው ስንፍላል ይብቃ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ በላይ መታገስ አይችልም፡፡ ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት የተከሰተው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ጫናው አሁን በያንዳንዱ ዜጋ እየተገለፀ ይገኛል፡፡ የንሮ ውድነቱ ጎልቶ መታየት ጀምሯል፡፡ ከዚህ ቀውስ በቀላሉ መውጣት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ቶሎ ምርጫ በማካሄድ ህዝቡ የሚመስለውን ይምረጥ፡፡ ፓርቲዎች ለህዝብ ይዘውት የመጡ ሀሳቦች ያቅርቡ፣ ነፃ ዴሞክራሲያዊ ውይይት ክርክር ይደረግ፡፡ አሁን የደረስንበት የዴሞክራሲ እድገት ደረጃ ወደፊት የሚወስድ ነገር እንዲሰራ ከመንግስት ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ መንግስት በተቻለ ፍጥነት ወደ ምርጫው ዝግጅት ይግባ፡፡
አስተያየት ያለው hidaseethiopia@yahoo.com ወይም hidaseethiopiaa@gmail.com ማድረስ ይቻላል

No comments: