Friday 29 November 2019

የተሳከረው ኢትዮጵያዊው ልሂቅና ፖለቲካው (የፓርቲዎች ዉህደት እንደምሳሌ)

ከበቀለ ብርሃኑ                                                                

ልሂቅ አዋቂ፣ ምሁር፤ ተጸእኖ ፈጣሪ እንደማለት ነው ይመስለኛል። በኢትዮጵያ ዉስጥ ግን አንዳቸዉንም ሲያደርግ አይታይም። ምናልባትም ተጸእኖ ፈጣሪ ነው ከተባለ ለማይበጅ ነገር ነው።

በፓርቲ ምስረታና ዉህደት የምናየው ክርክር እጅግ የሚገርም ነው። ፓርቲዎች ተመሳሳይ ወይም አንድ የሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም፤ ራእይ፤ ፍልስፍና ያላቸው ሰዎች ወይም ቡድኖች ተስባስበው የሚመሰርቱት ስብስብ እንጂ አንድ የነበሩ ግን የተፋቱ ድርጅቶች የሚዋሃዱበት መድረክ አይደለም።

ይህች ኢትዮጵያ ግን ጉድ የሚሰማባትና የሚነገርባት አገር እየሆነች ነው።

ጠ/ሚኒስቴር አቢይ የተለያየ የፖለቲካ ርእዮተ-አለም ያላቸውን ቡድኖች ተወሃዱ፤ ራሳችሁን አክስሙ ሲሉ መለኮታዊ ሃይል በኢትዮጵያ ይነግሳል የሚል አስተሳሰብ ከሌላችው በስተቀር አለም በተለያዩ የፖለቲካ እሳቤዎች እንደምትመራ ጠፍቷቸው አይመስለኝም ።

"ዓለማዊው" ዓለም ግን ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የዉህደት ሂደት በአርምሞና በአግራሞት እየተመልከተው ዪገኛል። ምናልባትም ብዙዎቹ የዓለም ታዛቢዎች እየተዛበቱብን ይገኙም ይሆናል።

እንደምናየዉና ከታሪክ እንደምንማረው ፓርቲዎች ግራ-ዘመም፤ ቅኝ ዘመም፤ ደሞክራት፤ ሊበራል፤ ኮንሰርቫቲብ፤ ወዘተ.. እየተባሉ በር ዕዮተ-ዓለም እሳቤያቸው ይመደባሉ። እናስ እንዴት አድርገው ነው ያሁኖቹ ኢህአደጎች የሚዋሃዱት? እንዲህ ዓይነት ዉህደትስ እንዴት አድርጎ ነው ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠቀሜታ የሚሰጠው?

ያሁኖቹ እሃአደጎች እኮ እርስ በራሳቸው ለመጠፋፋት ቆርጠው የተነሱ በሚመስል አኳሃን በሽኩቻ ላይ ያሉ ቡድኖች ናቸው። እናም ነቢዩ ጠ/ሚኒስቴር አብይ ከፓርቲዎች ዉህደት በፊት የፓርቲዎች የዓላማ አንድነትና ዕርቅ መቅደም እንዳለባቸው ሳያውቁ ቀርተው ይሁን?

የሳቸዉስ ይቅር፤ ታድያ ኢትዮጵያዊው ምሁርስ ምን ታይቶት ይሆን ግራ የሚያጋባ ሚና የሚጫወተው?

ይህ ከላይ የተጠቀሰው አንድ ነገር ሆኖ ሌላኛው ግርምት ላይ የሚጥለው ደግሞ አሁን ያሉት ፓርቲዎች በክልል ደረጃም ህልውናቸው ይጠፋል የሚለው አባባል ነው።

አሁንም ልሂቆቻችንና ፓርቲዎቻቸው የ ፈደራል መንግስት አወቃቀርና አስተዳደር የጠፋቸው አይመስለኝም። ጠፍቷቸው ከሆነ የከፋ አደጋ ዉስጥ ገብተናል ማለት ነው።

ክልሎች ወይም ፈደራል አስተዳደሮች (ስቴትስ) በፈደራል ፓርቲ ይተዳደራሉ ማለት አይደለም። እነዚህ ክልሎች በዉስጣቸው ባሉ የክልል ፓርቲዎች የምርጫ ውድድር ውጤት የሚመሰረት እንጂ የብሄራው (ባገር ዓቅፍ)ደረጃ የሚሳተፍበት ምርጫ አይደለም። እናም አሁን ያሉት የክልል ፓርቲዎች ይምከኑ የሚለው ፈሊጥ ከየት እንደመጣ ለማወቅ አስቸጋሪ ይሆናል።

ይህ ምን ማለት ነው?

አሜሪካ፤ ካናዳ በፈደራል ደረጃ የሚተዳደሩ አገሮች ናቸው። እንግሊዝ አሃዳዊ (ዩኒታሪ) አገር ነች። በነዚህ አገሮች እንደየ ርዕዮተ አለማቸው የተደራጁ አገራዊ ፓርቲዎች (ሶስት ወይም ከዚያ በላይ)ላገራዊ አስተዳዳሪነት ይወዳደራሉ። በዚህ ትይዩ ክልሎች ክልላዊ ፓርቲያቸውን ለክልል መሪነት ይወዳደራሉ። እንኳንስ በብሄርና በጅዮግራፊ የተከለለችው ካናዳ፤ አሃዳዊት የምትባለው እንግሊዝ ሳትቀር ግዛቶቿ ሁሉ የሚተዳደሩት አገራዊ ባልሆኑ የግዛት ፓርቲዎች ነው።

እነዚህ የክልልና የፈደራል መንግስት ፓርቲዎች ተመሳሳይነት ቢኖራቸውም ባስተዳደር፤ በጥቅም፤ በኤክኖሚ ፖሊሲያቸው አንድ ናቸው ማለት አይደለም። በክልል ደረጃ ያክራሪ መንግስቶች ሲመሰረቱ በ ፈደራል (ብሄራዊ) ደረጃ ሊበራል ውይም ልዝብተኛ መንግስት ሊኖር ዪችላል።

ፓርቲዎች በዋናነት የሚያስፈልጉት የተለያዩ መርሃ ግብሮችና አስተሳሰቦች፤ ፕሮግራሞች በመያዝ ህዝቡ የተለያዩ አማራጮችን በማየት የሚሻዉን ለመምረጥ እንዲያገለግልው በማለት ነው::

ከዚህ አንጻር ሲታይ ለምን የክልል ፓርቲዎችን መጨፍለቅ እንዳስፈለገ ለማወቅ ይከብዳል።

የ ኢሃአደግ ሰዎች የነሱን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ ፓርቲ መመስረት ከፈለጉ ከመሃከላቸው ይሆናሉ የሚሏቸውን ግለሰቦች መርጠው አገራዊ ፓርቲ መመስረት ይችላሉ። እነዚህ ግለሰቦች ፓርቲዉን የሚቀላቀሉት እንደግለሰብ እንጂ እንደ ክልል ተወካይ አይደለም።

ይህ ፓርቲ በየክልሉ ቅርንጫፍ መ/ቤቶችን በመክፈት ለብሄራዊ ምርጫ የሚሆኑትን ቅድመ-ሁነታዎች ያዘጋጃል እንጂ በክለላዊ አስተዳደር ጉዳይ ዉስጥ ግን ምንም እጅ አይኖረዉም።

ያሉትን ፓርቲዎች ጨፍልቆ አንድ መሆን ግን የፓርቲዎችን ፋይዳ እንደአለማወቅ ይቆጠራል።

የኢትዮጵያ ምሁር ግን ይህ ሁሉ የሚገደው አይመስልም። ትክክለኛዉን መንገድ ከማሳየት ይልቅ እንደ ስጎንዋ አንገቱን መሬት (አሸዋ) ዉስጥ ቀብሮ አገር ስትታምስና ህልውናዋ ሊያከስም በምትዳዳበት ዘመን አልሰማሁም አላየሁም እያለ ነው። ይባስ ብሎ 'እውቀቱን' ለጎሰኞችና ተስፋፊዎች እየለገሰ ነው።

'ምሁሩ' ኢትዮጵያዊነትና (ዜግነትና)ማንነት አብረው አይሄዱም የሚለዉን ተረት እየተቀበለ እውነትነትን ሊያላብሰው እየሞከረ ነው። በኢትዮጵያ ስም እትዮጵያዊነትን እየሸረሸር መስሎም ዪሰማኛል።

ኢትዮጵያዊው ምሁር አገሩን ለመታደግ ከፈለገ ከስሜት ባሻገር ማየት ግድ ዪለዋል። ራሱን መፈተሽ፤ መጠየቅና የመፍሄው አካል ለመሆን ከራሱ ጋር መታገልና ራሱን ማሸንፍ ግድ ይለዋል።

No comments: