Friday, 2 November 2018

ታሪክ እራሱን እየደገመ ይሆን እንዴ?

ዘፅኣት

ይህንን አጭር ፅሑፍ እንድፅፍ መነሻ የሆነኝ ከቀናት በፊት ከአንድ እጅግ በሳል ወጣት ጋር የነበረኝ እጅግ ግሩም ውይይት ነው፡፡ ከታች ያሉ የሚታወቁ የታሪክ ሁነቶች በተደጋጋሚ ያነበብኳቸው ቢሆንም ከዚሁ ውይይት በፊት ከአሁኑ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያን ያህል መመሳሰል እንዳላቸው በግልፅ አልታየኝም ነበር፡፡


ሶማልያዊ (ሐረሪ ነው የሚሉም አሉ) የአዳል ሱልጣንና ጀነራል አሕመድ ኢብን ኢብራሂም አልጋዚ (አሕመድ ግራኝ) ከ1522- 1535 እ.አ.አ ባሉ 13 ዐመታት ሶስት አራተኛውን የአቢሲንያ ምድር መቆጣጠር ችሎ ነበር፡፡ የግራኝ አሕመድ ዋና ድል የሚጀምረው ታሕሰስ 1524 ዐ.ም በኦቶማኖችና ስዑዲዎች ታግዞ ልብነድንግልን አምባሰል ላይ ካዳከመና በመጋቢት ደግሞ ሽምብራ ቆሬ ላይ የልብነድንግል ሰራዊትን ከጨረሰ በኃላ ነው፡፡ 

አሕመድ ግራኝ መላውን የአሁን የአማራ ክልል በአንድ ዐመት ተኩል ከተቆጣጠረና ወሎን በመላ በቀላሉ ካሰለመ በኃላ ጉዞው ወደ ዋናው ዒላማው ወደ ትግራይ ቀጠለ፡፡ ግራኝ አሕመድ መጀመርያ ድል ቀንቶት አክሱም ድረስ ደርሶ የአክሱም ማርያም ፅዮን ቤተ-ክርስትያንንና ንዋየ-ቅዱሳቱን ማቃጠል ችሎ የነበረ ቢሆንም ቀጣይ ጊዜያት ግን ለግራኝ አሕመድ ቀላል አልነበሩም፤ አሕመድ ግራኝ ትግራይ ላይ የነበረባቸው 11 ዐመታት(1524-1535) በጦርነት ያለፉ ነበሩ፤ አሕመድ ግራኝ በነዚሁ ዐመታት በትግራይ በርካታ ቤተ-ክርስትያናትን ማቃጠል ቢችልም ትግራይን ሙሉ ለሙሉ ማንበርከክም አልቻለም፤ በትግራይ አንድ ሰው ስንኳ ማሰለም የቻለ አይመስልም፡፡


በመጨረሻም በነኦቶማን በብዙ ይደገፍ የነበረውን ግራኝ ሙሉ ለሙሉ ማሸነፍ ስላልተቻለ የፓርቹጊዞች እገዛ ማግኘት የግድ ነበር፡፡ በክሪስቶፈር ደጋማ የሚመሩ የፖርቹጊዝ ሰራዊት በምፅዋ በኩልም ወደ ትግራይ ገቡ፤ በክሪስቶፈር ደጋማ የሚመራ የፖርቹጋል ሰራዊትና በአፄ ገላውዴዎስና በባህር ንጉስ ይሳቅ የሚመራ የኢትዮጵያ (ትግራይ) ሰራዊት ከሚያዝያ 1534 ጀምሮ ግራኝ ወይናደጋ እሰከተገደለበት የካቲት 1535 ዐ.ም ድረስ ብዙ ውጊያዎች ተደርገዋል፡፡

ከጦርነቱ ሸሽታ ያመለጠችው የግራኝ አሕመድ ባለቤት ባቲ ደል ወምበራ የግራኝ ዘመድ ኑር ኢብን ሙጃሂድን የባልዋልን ገዳይ እንዲበቀልላት ቃል አስገብታ አግብታ ከ16 ዐመት በኃላ አፄ ገላውዴዎስን መግደል ችላለች፡፡


የግራኝ አሕመድ ወረራና የግራኝ አሕመድ ፍፃሜ ውጤት የትግራይ፣ የአማራና የሱማሌ መዳከም ሆነ፤ ይህ ደግሞ ኦሮሞዎች ከባሌና ከጉጂ ዞኖች ተነስተው ወደ ሰሜን፣ ምስራቅና ምዕራብ እንዲስፋፉ ምቹ ሁኔታ ፈጠረ፡፡ ደብተራው አባ ባህሬና ፍራንሲስኮ ዴ አልሜይዳ የኦሮሞዎች መስፋፋት የጀመረው በ1520 ዐ.ም እንደሆነ ነው የሚስማሙት፡፡ ኦሮሞዎች የአሕመድ ኢብን ኢብራሂም ዱካ እየተከተሉ ወደ ሰሜን የሚያደርጉት መስፋፋት ጀመሩ፤ በአሕመድ ግራኝ ወረራ የተዳከሙ አካባቢዎችን በትንሽ ዋጋ ከቁጥጥራቸው ስር ማስገባት ቻሉ፤ ከግራኝ አሕመድ ሞት በኃላ ደግሞ ወደ ምስራቅም መስፋፋት ቻሉ፤ ጉዟቸው ወደ ምዕራብም ቀጠሉና ሰፊ የኢትዮጵያ አካባቢ ከቁጥጥራቸው ስር አስገቡ፡፡

ታሪክ ራሱን እየደገመ ይሆን?

1.      አሁን አዲሱ የኦሮሞ ኤሊት የኢትዮጵያ መንግስትን በመጠቀም የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል እጅግ እንድትዳከም፣ መንግስቷ እንዲፈርስ ሆኗል፤

2.       የአማራና የትግራይ ልሒቃን ውሉ ጠፍቷቸዋል፤ በውጤቱም የአማራና የትግራይ ክልሎች የመደራደር ዐቅም በየጊዜው እያሽቆለቆለ ነው፤ ይባስ ብሎም የአማራ ልሒቃን የመስፋፋት አምሮታቸውን ለማስታገስ ብቻ በትግራይ ላይ ወረራ ለመፈፀም፣ ህዝቦቹን ደም ለማቃባት ሁሉ እያሰቡ እንደሆነ እያየን ነው፡፡ ውጤቱ ለሁለቱም ሕዝቦች ኪሳራ ብቻ እንደሆነ ማንም ያውቀዋል፡፡ የፌደራል መንግስቱ ይህንን እያንዣበበ ያለውን ግጭት ለመግታት የሚያደርገው ጥረት እንደማይኖር እሙን ነው (ቤንዚን ካልጨመረበትም ተመስገን ነው የሚሉም አሉ)፤


በአጠቃላይ አሁን ያው ሁኔታ ለኦሮሞ ልሒቃን እጅግ የተመቸ ይመስላል ፤ እንደውም የግራኝ አሕመድ ወረራና ሞት የፈጠረው ዕድል ዐይነት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ አሁን የኦሮሞ ልሒቃን እንደ 16ተኛው ክ/ዘመን ተራ መስፋፋትን ብቻ ሊመኙ አይችሉም - በትንሹ በቅርቡ አቶ ሌንጮ ባቲ እንደነገሩን ለቀጣይ 3000 ዐመታት ኢትዮጵያን dominate ማድረግ፤ ከተሳካ ደግሞ ወደ አፍሪካ ቀንድም ተሻግሮ የዞኑ የበላይ መሆን፡፡

(ምንጭ :አይጋ ፎረም )

No comments: