Saturday 24 November 2018

አንዳንድ ነጥቦች ስለ”ዘር ፖለቲካ” – በቀለ ጉተማ (ፕሮፌሰር)

ኢትዮጵያ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ገደማ በማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ ትገኛለች፡፡ እንደምናውቀው አብዮቱ በ1966 ዓ. ም. ከተጀመረ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊትም የተወሰኑ ዓመታትን ወደኋላ ሄዶ የነበረውን የለውጥ ፍላጎት ማየት ይቻላል፡፡ የ1953ቱ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት፤ እሱን ተከትለው የመጡ የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴዎች፤ በባሌና በሌሎችም ቦታዎች የተቀሰቀሱ አመፆች፤ የመጫና ቱለማ ማህበር እንቅስቃሴ በተለይም ደግሞ የዩኒቨርሲቲና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንቅስቃሴዎች ወደ አብዮቱ ያመሩ ክስተቶች ሲሆኑ በነዚህ ሁሉ ውስጥ የሚታዩት የለውጥ ፍላጎቶች የመሬት ጥያቄን፤ የህዝቦች የመብት ጥያቄን፤ የዕኩልነትንና ሌሎች መብቶችን የተመለከቱ ነበሩ፡፡

የእነዚህን ዓመታት ትግሎች በምናይበት ጊዜ፣ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን ያማከሉት ጎላ ብለው ይታያሉ፡፡ እነርሱም የመሬት ጥያቄና የህዝቦች መብቶችን የተመለከቱት የሚጎሉባቸው ሲሆን በእርግጥ ከዚያው ሥር ሊታቀፉ የሚችሉ የማደግና የመልማት፤ እንዲሁም የማህበራዊ ፍትህ ጥያቄዎችና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
የ1966 አብዮት በተወሰነ ደረጃ በተለይም የመሬት ጥያቄን ለመመለስ ሞክሯል፡፡ በዚሁ መሠረት ጭሰኝነትን ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለማስወገድ ችሏል፡፡ ደርግ አሮጌውን ሥርዓት አሰወግዶ፤ መሬትን ለአራሹ አድርጎ በሶሻሊስታዊ አብዮት ኢትዮጵያን እለውጣለሁ ብሎ በሚታትርበት ወቅት ከፍተኛ ተግዳሮት የገጠመው ከብሔራዊ ንቅናቄዎች መሆኑ የሚካድ አይመስለኝም፡፡ በዋነኛነት የኤርትራ የአርነት ንቅናቄ፤ ሕወኃትና ኦነግ በዚህ ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በእነርሱ የተነሱት ጥያቄዎች ያለፉትን በርካታ አሥርተ ዓመታት የኢትዮጵያ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ የወሰኑ መሆናቸው የማይካድ ከመሆኑም በሻገር እነኚህ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ ሁኔታ ለሚቀጥሉት በርካታ ዓመታትም ቁልፍ ጥያቄዎች ሆነው የሚቆዩ ይመስላል፡፡

እነዚህ ጥያቄዎች በቀላሉ ልንተዋቸው ወይንም ልንገላገላቸው የማንችላቸው ናቸው፡፡ በኢህአዴግ አገላለጽ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመባል የሚታወቀው ጉዳይ ስለሕዝቦች የራሳቸውን መብት በራሳቸው የመወሰን መብት በተለይም እራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደርን የተመለከተ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በቀላሉ ልንገላገለው እንደማንችል የተገነዘቡ በርካቶች ቢኖሩም ተገቢውን መፍትሔ መስጠት ሊያመጣ የሚችለውን ለውጥ ካለመፈለግ ግማሹ ጉዳዩን የሌለ ጉዳይና ወያኔ ወይም ኦነግ የፈጠረው የሌለ ነገር ሊያስመስለው ይሞክራል፡፡

ሌላው ላይ ላዩን በመቀባት ጉዳዩ እንዲፈታ ይመኛል፡፡ ችግር በምኞት የሚፈታ ቢሆንማ ዛሬ ዬት በደረስን ነበር፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ እንደ ኢህአዴግ የደከመበት ያለ አይመስለኝም፡፡ የችግሩን መኖር ከመገንዘብ ጀምሮ የችገሩ መፍትሄም ሕዝቦች የእራሳቸውን መብት በራሳቸው እንዲወስኑ ማድረግን የተመለከቱት ናቸው፡፡ ባለፉት የኢህአዴግ ዘመናት ያየናቸው አከላለሎችና እነሱን ተከትለው የመጡት ለውጦች እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ቢሆኑም ኢህአዴግም እንደቀደምት የኢትዮጵያ ገዥዎች ከተለመደው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል መውጣት ባለመቻሉ እውነተኛው የአገዛዝ ወራሽ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ጆን ማርካኪስ እንደሚሉት ከረጅም ጊዜ ልፋት በኋላ ኢህአዴግ ሁለት ድንበሮችን ማለፍ/ማቋረጥ ባለመቻሉ ከአባቶቹ ብዙም አልተለየም፡፡ ሁለቱ ድንበሮች ማርካኪስ የደጋና የቆላ ድንበሮች የሚሉአቸው ሲሆኑ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ገዥዎች ወራሾች የኣባቶቻቸውን ፈለግ በመከተል እንዴት ሥልጣንን ከታሪካዊቷ ኢትየጵያ ውጭ ላሉ ወገኖች ለማካፈል ዝገጁነት እንደሌላቸው ለማሳየት የተጠቀሙበት አገላለጽ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ኢህአዴግ ያመጣው የፌዴራል ሥርዓት ተጠቃሽና ተገቢው መፍትሔ ቢሆንም ሥርዓቱ የይስሙላ ሆኖ ከማዕከል የሚዘወር በመሆኑና በዚህም የተነሳ የሕዝቦች መብቶች እየተረገጡ በመሄዳቸው፤ ማህበራዊ ፍትሕ በመጥፋቱ እና በመሳሰለው ሁኔታ ከ2008 ዓ. ም፣ ጀምሮ ያየናቸው ከፍተኛ የህዝብ ዓመጾች በተለይም በወጣቱ በመካሄዳቸው ከ2010 ዓ. ም. አጋማሽ ጀምሮ ያየናቸው ለውጦች ሊከሰቱ ችለዋል፡፡

ለውጡ ገና በጅምሩ ላይ ያለ ከመሆኑ የተነሳ በርካታ ተግዳሮቶች እያጋጠሙት ይገኛል፡፡ ለውጡ ብዙ ድጋፍ ያለው ቢሆንም ሊያደናቅፉት የሚፈልጉ እንዳሉም አይካድም፡፡ ዋናዎቹ ጥያቄዎች እራስን በራስ የማስተዳደር፤ የብዝኃነት፤ የመሬት ጥያቄና በነዚሁ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ማንነትን፤ የማሀረበራዊ ፍትሕንና ሌሎችንም ጉዳዮች የሚያካትቱ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ አሁን የምንከተለውን ሥርዓት ከማይፈልጉ ሰዎች ሥርዓቱን “የዘር ፖለቲካ” እና የመሳሰሉትን ብለው ለማጥላላት ስለሚፈልጉና እየሰሩም ስለሚገኙ ስለነዚህ ነገሮች የተሻለ ግንዛቤ ማግኘት ጠቃሚ ስለመሰለኝ ይህንን አጭር ፅሑፍ ለመጻፍ አሰብኩ፡፡

ያለው ፌዴራሊዝም በክልሎች ላይ የተመሠረተ እንደመሆኑ መጠንና ክልሎቹም የትግራይ፤ የአፋር፤ የአማራ፤ ኦሮሚያ ወዘተ የሚል ስም ስላላቸው ይህ “የዘር ፖለቲካ” ነው የሚሉ የተወሰኑ በከፍተኛ ደረጃ የተማሩትን ጨምሮ ይገኛሉ፡፡ “የዘር ፖለቲካ” ማለት ምን ማለት ነው? “የዘር ፖለቲካ” የሚባል ነገር አለ ወይ”? “ዘር” ማለት ምን ማለት ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ሃሳቤን ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

ዘር የሚለው ቃል race በሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ይተረጎማል፡፡ ይህ ከሆነ ዘር ወይም race ምን ማለት እንደሆነ በመመለስ መጀመር ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ዘር የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ጎልቶ ለፈላስፎች፤ ለአንትሮፖሎጂስቶችና ለሌሎችም የመወያያ ርዕስ የሆነው በዘመናዊት አውሮፓ ውስጥ ነበር፡፡ የተወሰኑ ልሂቃን በዚህ ፅንሰ ሃሳብ ላይ ጽፈዋል፤ ተጠበዋል፡፡ በመሆኑም ዘርን ከቆዳ ቀለምና ከመሳሰሉት ወጭያዊ ምልክቶች በማንተራስ የተለያዩ የሰው ዘሮች እንዳሉ፤ እነዚህም ዘሮች መሠረታዊ የሆነ ልዩነት እንዳላቸው አድርጎ መረዳት ነው፡፡ ዘሮች በተዋረድ (hierarchically) እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ ይህም ማለት ከፍተኛና ዝቅተኛ ዘሮች እንዳሉ፤ በዚህም የተነሳ ከፍተኛው ዘር ዝቅተኞቹን ዘሮች መግዛትና ማሰልጠን እንደሚገባቸው ጽፈዋል፡፡ በእርግጥ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብን መሠረት የሚሰጡት እንደዚህ ዓይነት የዘር ክፍፍሎች እንደሆኑ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ከታወቁት የአውሮፓ ፈላስፎች አንዱ የሆነው ኢማኑኤል ካንት የሰው ዘርን በአራት ከፍሎ፤ የነጭ፤ የቢጫ (ኤዥያ)፤ የጥቁርና የቀይ ዘሮች እንዳሉ አሳይቶ ማንነታቸውም በዚያው ልክ በተዋረድ የተቀመጠ፤ ከፍተኛ የተባለው ዘር ዝቅተኛውን ማሠልጠን/መግዛት እንዳለበት አድርጎ ጽፏል፡፡ ባጭሩ ዘር ማለት ይህንን ይመስላል፡፡ ዘሮች በመሠረቱ የተለያዩ ናቸው ይላል፡፡ የመለያየታቸውን ሁኔታ የሚያስረዳውም የቆዳ ቀለማቸውንና ተመሳሳይ ውጭያዊ ገጽታዎችን በመጠቀም ነው፡፡ ዘርን ባዮሎጂያዊ መሠረት ያለው ክስተት አድርጎ ይገልጻል፡፡

ይሁንና ይህንን ከመቀበላችን በፊት ዘር የሚለውን ሃሳብ ከሳይንስ አንጻር ምንድነው የሚለውን መመለስ መቻል አለብን፡፡ በሳይንስ ውስጥ በዚህ ጉዳይ ላይ ግንዛቤ ሊያስጨብጠን የሚችለው በባዮሎጂ መስክ ጄኔቲክስ የሚባለው ዘርፍ ሲሆን ፓሊዎ አንትሮፖሎጂና የመሳሰሉትን ብናይ ዘር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ልንረዳ እንችላለን፡፡ በነዚህ የሳይንስ መስኮች ላይ ተመስርተን ዘር ምንድነው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ብንሞክር በቀለምም ይሁን በደም (DNA)ም ወይም በሌላ በሰው ልጆች መካከል መሠረታዊ ልዩነት እንደሌለና የሰው ዘር በሙሉ አንድ ብቻ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በDNA ረገድ የተደረጉ ጥናቶች የሚያመለክቱት የሰው ልጆች እስከ 99.90 በመቶ አንድ ናቸው የሚል ነው፡፡

ይህ ከሆነ ታድያ የቆዳና ሌሎች ልዩነቶችን እንዴት ነው መረዳት ያለብን የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ የቆዳ ቀለምና ሌሎች የቅርጽ ሁኔታዎች የሚያሳዩት በሰው ልጆች መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት ሳይሆን (መሠረታዊ የሆነ ልዩነትም የለም) ከምንኖርበት አካባቢ ከባህላችንና ከመሳሰለው ጋር የተያየዘና በረጅም የሰው ልጆች አዝጋሚ ለውጥ የመጡ ልዩነቶች፤ እነሱም መሠረታዊ ሳይሆኑ በሁኔታዎች ውስጥ የተፈጠሩ መሠረታዊ ያልሆኑ (contingent) ገጽታዎች መሆናቸውን ነው፡፡

እንደ ናኦሚ ዛክና (Naomi Zak) ክዋሜ አንቶኒ አፒያህ (Kwame Anthony Appiah) ግንዛቤ የዘርን ምንነት የሚያሳዩ ምንም ባዮሎጂያዊ ምክንያቶች የሉም፡፡ የዘርን ዕውነታነት መግለጽ የሚችል ነባራዊ ነገር የለም፡፡ ጂኦገራፊ፤ ውጭያዊ ቅርጽ (phynotype); ውስጣዊ ይዘት (genotype)፤ የሰው ልጅ አመጣጥ (genealogy) የዘርን ምንነት እንደሚያሳዩ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የሚያሳዩት በሰው ልጆች መካከል ምንም መሠረታዊ ልዩነት እንደሌለ ነው፡፡ Phenotype ውጭያዊና ድንገተኛ ነው፤ genotype በአብዛኛው (99.90 በመቶ) የሰው ዘር ልዩነት የለውም ይላል፡፡ በዚህም የተነሣ ዘር የሚያሳየው ምንም ነባራዊ ባህሪ የለም ይባላል፡፡

ይህ ከሆነ ዘንዳ ዘረኝነት የሚባለው ክፉ ኣባዜ ከዬት መጣ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ እንደምናውቀው ዘረኝነት በዓለም ላይ በሰፋት ከመኖሩም በላይ ለብዙ ጥፋቶች ምክንያት እንደሆነ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ዘረኝነት መኖሩ እርግጥ ከሆነና ባዮሎጂያዊ የሆነ የዘር መሠረት ከሌለ ዘረኝነት ከዬት መጣ? የዘረኝነት መሠረቱ ምንድነው?
የዘረኝነት መሠረቱ ደም ወይም DNA አይደለም፡፡ ምክንያቱም በዚያ ረገድ የሰው ልጆች ሁሉ እስከ 99.90 በመቶ አንድ ስለሆኑ፡፡ ሰለዚህ ዘረኝነት የሚመሠረተው በሌላ ነገር ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዘረኝነት የቆዳ ቀለምንና ሌሎች የቅርጽነት ባህሪ ባላቸው እንደቁመና፤ ፀጉርና በመሳሰለው ላይ የተመሠረተ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ዘረኝነት በማህረሰብ የሚፈጠር ነገር ግን ምንም የባዮሎጂም ወይም የሌላም ነገር መሠረት የሌለው ነገር መሆኑ ነው፡፡
በእንግሊዝኛ “racism is a social construct” እንደሚሉት ማለቴ ነው፡፡ ለዚህም መነሻው እላይ እንደተባለው የቆዳ ቀለም፤ፀጉር፤ ቅርጽ ባጠቃላይ phenotype በስው ልጆች መሐል ያለን ምንም መሠረታዊ ልዩነት አያሳዩም፡፡ ዘረኝነት ግን በነዚህ ላይ ተመሥርቶ እንደራስ ያልሆነን መጨቆን፤ ማግለል፤ ማንኳሰስ ነው፡፡ ዘረኝነት በአንዱ የበላይነትና በሌላው የበታችነት የተመሠረተ ነው፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ሥርዓት በነጭ የበላይነት ላይ የተመሠረተና ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ሕጎችን አውጥቶ ሥራ ላይ ያውል ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ነጭ ያልሆኑ ሰዎች የመኖሪያ ቦታቸው፤ ትምህርት ቤታቸው፤ የሚገለገሉበት የሕክምና ተቋማት፤ ሬስቶራንቶች ከነጮቹ የተለዩ ነበሩ፡፡ እንደ አሜሪካ ባሉ አገሮችም በህግ ላይ የተመሰረተ ባይሆንም ነጭ ያልሆኑ የአሜሪካ ዜጎች ላይ በርካታ መድሎዎች ይካሄዳሉ፡፡ ከሀብት ክፍፍል ጀምሮ በሌሎች የማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ነጭ ያልሆኑ ዜጎች ያላቸው ቦታ ዝቀ ያለ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በነጭ ፖሊሶች አማካይነት በጥቁሮች ላይ የሚደርሰው ጭቆናና ግድያ የዘረኝነት ማሳያ ሆነው፤ ነጭ ያልሆኑ የአሜሪካ ዜጎች ባልተጻፉ የዘረኝነት ህጎች እንደሚጨቆኑ የሚያሳዩ ናቸው፡፡

ስለዚህ ዘርንና ዘረኝነትን ለያይቶ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የሰው ዘር አንድ ነው፡፡ ሳይንስም ሆነ ኃይማኖቶች የሚያስተምሩን የሰው ዘር አንድ መሆኑን ነው፡፡ ዘረኝነት ግን ሳይንሳዊም ሆነ ኃይማኖታዊ መሠረት በሌላቸው መሥፈርቶች ላይ በመመሥረት የሰው ልጆችን ለክፉ ዓላማ የሚከፋፍል ነው፡፡ በዘረኝነት ውስጥ ያለው ዋና ሃሳብ አንዱ የበላይ ሌላኛው የበታች ስለሆነ የበታቹ መገዛት አለበት የሚል ነው፡፡
እነኚህን ነገሮች በመረዳትም ሆነ ባለመረዳት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ሰዎች በማንነት ላይ የተመሠረተውን የአሁኑን ፌዴራሊዝም “የዘር ፖለቲካ” ይሉታል፡፡ እውን አሁን በኢትዮጵያ የሚካሄደው “የዘር ፖለቲካ” ነው? “የዘር ፖለቲካ” ማለትስ ምን ማለት ነው?

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ማንነታቸው፤ ባህላቸው፤ ታሪካቸውና የመሳሰለው እንዲከበርላቸው ረጅም ትግል አካሂደዋል፤ ከፍተኛ መሰዋዕትነትም ከፍለዋል፡፡ ማንነት የሚመሠረተው በተለያዩ መሥፈርቶች ላይ ሲሆን በዘር ላይ አለመመሥረቱ ግን ሊሠመርበት ይገባል፤ ምክንያቱም ዘር የሚባል ነገር ስለሌለ፡፡ የብሔር ማንነት እንደሚታወቀው የሚመሠረተው በቋንቋ፤ በታሪከ፤ በሥነልቦና፤ በመኖሪያ አካባቢና በመሳሰለው ላይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ አፅንኦት ሊሰጠው የሚገባው የብሔር ማንነት በደም ላይ የተመሠረተ አለመሆኑ ነወ፡፡ የአንድ ብሔር አባላት የጋራ መሠረት አለን ብለው ሊያምኑ ይችላሉ፡፡ ይህም ከአንድ መሰረት የመሆን እሳቤ (myth of origin) የሚባለው ነገር በደም ወይም በDNA ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡

ማንነት እንደሚታወቀው ከላይ በተዘረዘሩት ነገሮች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ማንነት ብዙ መብቶችን የያዘ ሆኖ የራስን መብት በራስ የመወሰን መብት የሚያካትት ነው፡፡ እንደ ሕዝብ የራስን መብት በራስ መወሰን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ሰብዓዊ መብት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከሩብ ምዕተ ዓመታት ላለፈ ጊዜ “የዘር ፖለቲካ”፤ “የጎሳ ፖለቲካና” የመሳሰሉተ ሃሳቦች በተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም በተማሩት ሲንጸባረቅ ይታያል፡፡ ዘር የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ምንም ሳይንሳም ሆነ ኃይማኖታዊ መሠረት የለውም፡፡ የብሔርን ማንነት ለማስከበር የሚታገሉ ወገኖችን “የዘር ፖለቲካ” የሚያራምዱ ሰዎች ናቸው ብሎ መክሰስ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉና ለመብታቸው መከበር (ከሌሎች በላይ ለመሆን ሳይሆን ለዕኩልነት) ለረጅም ዓመታት ሲታገሉ የኖሩ እንደ ኦሮሞ፤ ሲዳማ፤ ትግራይ፤ ሶማሌ፤ አፋር፤ በቅርቡ ደግሞ አማራ እና ሌሎች በርካታ ብሔረሰቦ አሉ፡፡ እነኚህ የተጠቀሱት በምንም መለኪያ ዘሮች ሊባሉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም እላይ እንደተጠቀሰው ዘር የሚባል ነገር ባለመኖሩ፡፡ ጎሳ የሚለው ፅንሰ ሃሳብ እነዚህን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕዝቦችን መግለፅ አይችልም፡፡ በመሠረቱ ጎሳ ከቤተሰብ ከፍ ብሎ የሚገኝ ምናልባትም በደም መተሳሰርን የሚያመለክት ፅንሰ ሃሳብ ነው፡፡ ጎሳ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የተወሰኑ ትውልዶችን የሚመለከት ሆኖ በጎሳው አባላት መካክል የስጋ ዝምድና ከመኖሩ የተነሳ ጋብቻ እንኳን በጎሳ አባላት መካከል አይፈጸምም፡፡ ጉዳዩ ይህ ሆኖ ሳለ ቢያንስ አርባ ሚሊዮን ሕዝብ ገደማ ላለው የኦሮሞ ሕዝብ ማንነትና መብት መከበር የሚደረገውን ትግል የጎሳ ፖለቲካ ማለት ይቻላል? ይህ ደግሞ ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለብሔራቸው መብት የሚታገሉትን ሁሉ ይመለከታል፡፡

ለዕኩልነት፤ ለማነነትና ለማህበራዊ ፍትሕ የሚደረግን ትግል “የጎሳ” ወይም “የዘር ፖለቲካ” ማለትና በዚህ ዓይነት የብሄሩን አባላት ወይም መሪዎቹን “የጎሳ ፖለቲካ” አራማጆች ማድረግ የጋራ ሀገርን ለመገንባትና አንዱ ሌላውን ለመረዳት ፋይዳ አለው? ዘር፤ ጎሳ፤ ነገድ፤ ወዘተ የመሳሰሉ በግልፅ ምን ማለት እንደሆኑ የማንረዳቸውን ፅንሰ ሃሳቦች በፖለቲካ ሐቲት (discourse) ውስጥ ማስገባት ጥቅሙ ምንድነው? እኛ ራሳችን በቅጡ ያልተረዳነውን ፅንሰ ሃሳብ በመጠቀም ሌሎችን ለማሸማቀቅ መሞከር ከጋራ ግብና ዓላማ አንፃር ፋይዳው ምንድነው?
“የዘር ፖለቲካ”፤ “የጎሳ ፖለቲካና” ሌሎችም ህብረተሰባችንን በትክክል የማይገልፁ ፅንሰ ሃሳቦችን የማንነት ፖለቲካ የሚያካሄዱ ሰዎችን ለማሸማቀቅ ሆን ተብለው በጥቅም ላይ የሚውሉ ቃላት ህዝቦችን ለማቀራረበም ሆነ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ምንም የማይፈይዱ በተቃራኒም የሚያራርቁ ናቸው፡፡ የማንነት ፖለቲካን በቀላሉ የምንገላገለው ነገር አይደለም፡፡ የማንነት ፖለቲካም “የዘር ፖለቲካ” አይደለም፡፡ የማንነት ፖለቲካ የዕውቅና ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ማን ነን የሚለውን እራስን በራስ ማን እንደሆንን የመግለፅ መብት የሚመለከትና እንዳለን እኛን ከማወቅ ይልቅ እኛን ለመግለጽ ለምን ትሞክራላችሁ የሚል ነው፡፡

በህብረተሰብ ሳይንስ ውስጥ የተናጋሪው ማንነት ወሳኝ እንደሆነ የሚጠፋን አይመስለኝም፡፡ ማን እንደሆንኩ የማውቀው እኔ ነኝ ወይስ ጎረቤቴ ነው የሚወስንልኝ የሚል መሠረታዊ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ማንነት የሚመሠረተው ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው በ DNA ላይ ሳይሆን በቋንቋ፤ በጋራ ታሪክ ፤ በስነ ልቦናና በመሳሰሉት ላይ ነው፡፡ የማንነትን ፖለቲካ ማራመድም ሀገርን የማፍረስ ጉዳይ አይደለም፡፡ የማንነት ፖለቲካ ልዩነትን ለመደፍጠጥ የሚደረጉ አካሄዶችን የሚገዳደር፤ ነገር ግን በልዩነት ላይ ተመሥርቶ አንድነትን መመሥረትና ማፅናት የሚቻል መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የማንነት ፖለቲካን ማካሄድ አደጋ የለውም ማለት አይደለም፡፡ አደጋውን ማስቀረት የሚቻለው ግን ለልዩነት ተገቢውን ዕውቅና መስጠት፤ የጋራ ነገሮችን በጋራ ማሳደግ፤ አንዱ ሌላውን እንዲረዳ ማድረግ፤ ከዚያም ባለፈ ልዩነትን ለማጥፋት ከመጣር ይልቅ መቻቻልን መምረጥ ተገቢ ነው፡፡
በእርግጥ ለማንነት ፖለቲካ የተደራጁ ወገኖች/ቡድኖች ጥፋት አይሰሩም፤ ሁሉም ለመብታቸው ብቻ በሃቅ ይታገላሉ፤ መድልዎ የለም ማለት አይቻልም፡፡ እንዲያውም እንዲህ ዓይነት አደረጃጀት ለመድልዎ፤ በዝምድናና በቡድን ለመሥራትና ለሙስና የተመቻቸ ሁኔታ እንደሚፈጥር ጥርጥር የለውም፡፡ ያም ሆኖ ግን ይህንን ስላደረጉ ተግባራቸውን ዘረኝነት አድርጎ መፈረጅ አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ መቀራረባቸውን፤ ዝምድናቸውን፤ አንድ ቋንቋ መናገራቸውን ወዘተ ይጠቀሙበታል፡፡ይህ እንዳይሆን ተቋማዊ መፍትሔዎችን ማበጀት እንጂ ነገሩን ያልሆነውን ስም መስጠት ችግሩን አባብሶ ያራርቅ እንደሆነ ነው እንጂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም።

የኛና የነሱ የሚባሉ ነገሮች ብዙ ጊዜ አሉ፡፡ ችግር የሚፈጠረው የኛ የምንላችው ነገሮች ብቻ ተቀባይነት ይኑራቸው፤ የነሱ ከፋፋይ ወይም ኢትዮጵያዊ ስላልሆኑ የነሱን ትተን አንድ ዓይነት ብቻ እንሁን ስንል ነው፡፡ ይህ በቋንቋም፤ በእምነትም፤ በባህልም በሌላውም ሊንጸባረቅ ይችላል፡፡ ይህ ዓይነት አካሄድ ግን ለብዙ ጊዜ ተሞክሮ ረጅም መንገድ እንዳላስኬደ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ያየናቸው ክስተቶች አስረጅ ናቸው፡፡

አንዱና ዋነኛው የማንነት ፖለቲካ መገለጫ እራሳችንን እንሁን፤ እራሳችን ማን እንደሆንን እንግለጽ ስንል በሌላ በኩል ሌሎች እኛ እናውቅላችኋለን፤ እኛ የምንለውን ተቀበሉ ሲሉ ችግር ይፈጠራል፡፡ እኛ አናውቅላችኋለን፤ እኛ እንዳልናችሁ ብቻ ሁኑ የሚለው አስተሳሰብ ዘመኑም ከደረሰበት ሁኔታና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከዘመናት ትግል በኋላ ከደረሱበት ደረጃ አኳያ ብዙ የሚያስኬድ ባለመሆኑ ወደ መከባበርና መቻቻል ብሎም ዕውቅና መስጠት ደረጃ ከፍ ብንል ችግሮቻችንን ለመፍታት የጋራ ቀና መንገድ ይሆናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሁለት ነጥቦችን ባጭሩ አንስቼ ይህችን አጭር ፅሑፍ ላጠቃልል፡፡

የግልና የጋራ መብቶች የተሰኙት ፅንሰ ሃሳቦች በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ ብዙ የሚያከራክሩ ናቸው፡፡ የግለሰብ መብቶች ቢከበሩ ችግሮቻችን ይፈታሉ የሚሉ ሰዎች ብዙ ሃሳቦችን ከተለያዩ ምንጮች በመጥቀስ የግል መብቶች መከበር ለሁሉም ችግሮች ፍቱን መድኃኒት (panacea) መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ ምሳሌ ለመስጠትም ሳይቸገሩ የአውሮፓና ሌሎች በዲሞክራሲ አስተሳሰብ የሚመሩ አገሮችን ሁኔታ ይጠቅሳሉ፡፡ ዲሞክራሲን ለማስፈን ዓይነተኛው መፍትሔ ይህ ብቻ መሆኑን ለማስረዳት ጥረት ያደርጋሉ፡፡

በሌላ በኩል የጋራ መብቶች ወሳኝ መሆናቸውን የሚከራከሩ ሰዎች፤ ሕብረተሰቦች በራሳቸው ሁኔታ ላይ ተመሥርተው ለውጥ ማካሄድ እንዳለባቸው ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ ከሌላ ሕብረተሰብ የምንማረው ነገር የመኖሩን ያህል የራሳችንን ተጨባጭ ሁኔታ ማገናዘብ እንዳለብን ይከራከራሉ፡፡ በአውሮፓ የተተገበሩት ሊበራል ዲሞክራሲም ይሁን ሶሻሊዝም ለአፍሪካና ለሌሎች ሀገሮች ምን ያህል አመቺ ናቸው የሚል ጥያቄ በማንሳት ማንኛውንም የህብረተሰብ ንድፈ ሃሳብ እንዳለ መገልበጥ እንደማያዋጣ ይከራከራሉ፡፡ እሩቅ ካለ ሊበራል አስተሳሰብ ይልቅ የጋራ መብቶችን የሚያማክለው አስተሳሰብ የበለጠ ወደእኛ በአኗኗራቸን ሁኔታ፤ በባህላችንና በታሪካችን የተነሳ ለኛ ይቀርባል ይላሉ፡፡ Individualism vs Communitarianism በሚለው ክርክር ውስጥ ግለሰብን ከህብረተሰብ ውጭ ማሰብ እንደማይቻል ከማሳየት በተጨማሪ የረጅም ጊዜ አኗኗራችንም የበለጠ ወደ ሁለተኛው ያዘነበለ መሆኑን ለማሳየት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ማንነት የሚቀረጸው በህብረተሰቡ ውስጥና አማካይነት እንደመሆኑ መጠን ሊበራሊዝም የሚነግረን ዓይነት ግለሰብና ግለሰበኝነት ከእውነት ይልቅ ወደልበወለድነት ያደላ ነው የሚል ክርክር ያነሳሉ፡፡ በዚህ ረገድ በታወቁ የፖለቲካ ፈላስፎች ያለውን ክርክር ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ በአውሮፓ በርካታ የግል መብትን የሚያጎሉ ያሉትን ያህል በሌላ በኩል ደግሞ እዚያው በአውሮፓና ሌሎች በርካቶች ደግሞ ከኤዥያና አፍሪካ የጋራ መብቶችን የሚደግፉ እናገኛለን፡፡ እንግዲህ ያለው ክርክር በግለሰብና በህብረተሰብ ዲያሌክቲክ፤ በባህላችንና በታሪካችን ላይ ተመሥርተን በምናይበት ጊዜ የጋራ መብቶች ከግል መብቶች ይልቅ ወደኛ ይቀርባሉ የሚል ነው፡፡

ዞሮ ዞሮ ከሁለቱ ከመምረጥ ሁለቱን የሚያስተናግድ ነገር መሥራት አንችልም ወይ የሚለው ሃሳብ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ፎርሙላ ባይኖረኝም የግለሰብ መብትን ለማስከበር ብለን የጋራ መብቶችን መርገጥ የለብንም፤ የጋራ መብቶችን ለማስከበር ብለንም የግል መብቶችን መደፍጠጥ የለብንም፡፡ ሁለቱን እንደተፃራሪ ከማየት ይልቅ እንደተደጋጋፊ ማየት እኛ ባለንበት ሁኔታ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ሁለቱንም ከማጦዝ ለሁለቱም ማዕከላዊ የሆነ ነገር ማግኘት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

እዚህ ላይ ያለው ክርክር እውነቱ የትኛው ነው የሚለው ይመስለኛል፡፡ በሁለቱም ረገድ ፍፁም እውነት የሆነ ነገር የለም፡፡ ፍፁም የሆነው ነገር ይህ ብቻ ነው፤ የኔ ብቻ ነው ካልን የትኛውንም ችግር መፍታት አንችልም፡፡ የኛ ብቻ የሆኑ ፍፁም እውነቶች አሉ ብለን እንኳን ብናምን የራሳችንን ፍፁም እውነቶች ሌሎች ላይ መጫን አንችልም፤ ምክንያቱም የእኛ እውነቶች የነሱ እውነቶች መሆን ስለማይችሉ፡፡ በዚህ ረገድ እውነትንና ዕውቀትን ከፍላጎት/ጥቅም ለይተን ማየት እንችላለን የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እውን እውነት ከፍላጎትና ከሥልጣን ተለይቶ ታይቶ ያውቃል? ይቻላልስ ወይ? በመሆኑም አማካይ ቦታ የመፈለጉ ጉዳይ ተገቢ ነው፡፡ እላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በህብረተሰብ አስተሳሰብ ውስጥ ብዙ ወገናዊ ያልሆነ ወይም neutral የሆነ ነገር ለማግኘት አዳጋች ስለሆነ የኛን ፍፁም ዕውነቶች በሌሎች ላይ መጫን ባንሞክር፤ አንዱ አንዱን ለመረዳት፤ ነገር ግን መሠረታዊ መግባባቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ብንረዳ፤ የግድ እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ የሚለው አስተሳሰብ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል በመገንዘብ እንደኛ ሊያስብ ከማይፈልገው ሰው ጋር ላለመግባባት ብንግባባና በመቻቻል መንፈስ ብንሠራ ሕመሞቻችንን ቀንሰን የጋራ ሀገር መገንባት እንችላለን፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ትክክለኛው ኢትዮጵያን የምናዋቀርበት የፖለቲካ ሥርዓት የቱ ነው የሚለው ጉዳይ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመሥርቶ ቢሆን ብዙ ቅራኔዎችን ለማስወገድ ይረዳናል፡፡ ኢትዮጵያ አሜሪካ ወይንም ጀርመን ወይንም ሌላ ሀገር ሳትሆን ኢትዮጵያ ነች፡፡

በርግጥ ከሌሎች የምትማረው ብዙ ነገር ቢኖርም እራሷን ካልሆነች ግን የትም ልትደርስ አትችልም፡፡ ይህንን የምልበት ምክንያት በአንዳንድ ሀገሮች (በተለይም በምዕራቡ ዓለም) ሁኔታ ላይ በመመሥረት በዜግነት ብቻ ላይ የተመሠረተ፤ የግለሰብ መብት የተከበረበት ሕብረተሰብ አማራጭ የሌለው ነው የሚሉ አሉ፡፡ ይህ አካሄድ ለአሥርተ ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የታገሉለትን ጥያቄ ይመልሳል ወይ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ሕብረተሰብን በሞዴል ላይ ተመሥርቶ መገንባት ይቻላል ወይስ የራስን ሁኔታ አጢኖ ለራስ የሚሆን ይዘት ያለው ህብረተሰብ ለመገንባት መጣር ይሻለል የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡

የላይኛውን ሃሳብ የሚደግፉ ሰዎች ያሉትን ያህል በሌላ ወገን ደግሞ እንደዚህ ዓይነት አካሄድ የሀገሪቱን ሁኔታ አያገናዝብም በማለት ብዝኃነታችንን ያማከለ ከውጭ ልምድም ጠቃሚ ሃሳቦችን የወሰደ ነገር ግን ለአሥርተ ዓመታት ትግል የተካሄደበትን የማንነት ጉዳይ የማይሽር አካሄድ ተከትለን ህብረተሰባችንን ብናዋቅር ይሻላል የሚሉ አሉ፡፡ ይህ ጉዳይ በዚህ ምክንያት ከአካዳሚ ክርክር በላይ ነው፡፡ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ከተካሄደው የትጥቅ ትግል በተጨማሪ ባለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት ገደማ የተካሄው ለውጥ መሠረታዊ ከመሆኑም በላይ ይህንን ለመቀልበስ መሞከር ብዙ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፡፡ ዜግነት ብቻ ለይ የተመሠረተ መዋቅር ይሥራ ማለት እስከአሁን የተካሄደው ትግል ምንም አስፈላጊ አልነበረም ማለት ነው፡፡ የህብረተሰብ መዋቅርን የሚወስነው በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ መሆን አለበት እንጂ የልሂቃን ምኞት መሆን የለበትም፡፡ ተጨባጭ ሁኔታው የሚፈቅደውና የሚወስነው ነገር ነው ተግባራዊ የሚሆነው፡፡

በአሁኑ ሁኔታ የልሂቃንን እናውቅላችኋለን አስተሳሰብ ለመቀበል ዝግጁ የሆነ ብዙ የኢትዮጵያ ህዝብ ካለመኖሩም በላይ በኦሮሚያ፤ በደቡብ፤ በትግራይ፤ በሶማሌ ክልል፤ በቤኒሻንጉል፤ በጋምቤላና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክልሎች ህዝቦች አሁን ስላለው ፌዴራሊዝም ያላቸውን ግንዛቤ ማጤን ለወደፊት እርምጃችን ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ቢያንስ ሰሞኑን በደቡብ ክልል የሰገን ዞን ሕዝቦች የሚጠይቁትን፤ የሲዳማን ሕዝብ ጥያቄ፤ በአማራና በትግራይ ክልሎች ራያን፤ ወልቃይትን፤ ጠገዴን አስመልክቶ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎችን በጥሞና ያጤነ የጉዳዩን ክብደትና ሂደት ለመገንዘብ አይቸገርም፡፡ ይህንን መገንዘብ ደግሞ ስለመፍትሔው በጥልቀት እንድናስብ ያስገድደናል፡፡

No comments: