Sunday 25 November 2018

የሕገ መንግሥት ጉባኤ ወቅታዊነት

ከተስፋየ መኮንን
(የ”ይድረስ ለባለ ታሪኩ” ደራሲ)

ኢሕአዴግ ከሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ መራሽነት ወደ ኦሕዴድ መራሽነት የተሸጋገረበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። የወንበር ሽግግር ተደርጓል። ይህ ግልጽ ነው። ግን ይህ መፍትሔ ነው ወይ? በመሠረቱ እነ ዶ/ር ዐቢይ የኦሕዴድ መራሹን ኢሕአዴግ በማሻሻልና ወያኔያዊ የሆኑ ገፀባሕርይዎችን በማጥፋት ለውጥ አምጥተናል ሲሉ እየታዘብን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫ ግን ወያኔያዊ የነበረውን ገፀባሕርይ በኦሕዴዳዊ ለመቀየር አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት መሠረታዊ ለውጥ ነው።

ወያኔ ሄዷል፤ አልቆለታል። በአገራችን ግን መሠረታዊ ለውጥ አልመጣም። በአገራችን መሠረታዊ ለውጥ የሚመጣው አዲስ ሕገ መንግሥት ተቀርፆ፣ በዚያ ላይ ተመሥርተን ወደምርጫ ስንሄድ ብቻ ነው። እንደዚያ ካልሆነ ለውጥ የለም። የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ላይ ተቀብሯል ከተባለ በኋላ በመፈክር መልክ ስለተስተጋባ ለውጥ መጥቷል ማለት አይደለም። መፈክሩ ያሳየን ሕዝቡ ኢትዮጵያዊ ብሔራዊነት ስሜት እንዳለው ብቻ ነው። የዐቢይ መፈክር ይህን አረጋግጦልናል። ይህን ደግሞ ዐቢይ አሕመድ አውቆ ነው ያደረገው። መለስ ዜናዊ አክ እንትፍ ብሎ የቀበረውን ኢትዮጵያዊነት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ መልሶ እንደጠራው ነው። በአገራችን በተጨባጭ የሚታየው ግን ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ወያኔነቱን አጥቦና ተሻሽሎ ወደፊት እየሄደ መሆኑ ነው። ያለ ጥርጥር፣ አሁን ያለብን እዳ በሥራ ላይ ያለው ኢሕአዴግ ያዋቀረው ሥርዓት እንዳለ ተጠብቆ ወያኔያዊ መልኩ ታጥቦና ኦሕዴዳዊ መልኩ ቅባት ተቀብቶ ወደፊት ይሂድ የሚለው አደገኛ አቋም ነው።

ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ የተቀባባ ለውጥ አድርጎ ወደ 2012 ዓ.ም. ምርጫ እንሂድ እያለ ነው፡፡ ጨርሶ መሆን የለበትም። በሕገ መንግሥቱ ላይ ሳንስመስማማ፣ ስንደራደር፣ ኮንትራት ሳንገባ ወደ ምርጫ መሄድ የለብንም። ኢትዮጵያ በጣም ብዙ ሐሳብና አመለካከት ያላቸው ዜጎችንና ቡድኖችን ያቀፈች አገር ናት። ተሰባስበው መምከር አለባቸው። ስለአገራቸው ኮንትራት መግባት አለባቸው። ይህ ሳይሆን በምን ተዓምር ነው በቀደመው መንገድ የምንጓቸው? አዲስ ኮንትራት መገባት አለበት። አዲስ ጉባኤ መጠራት አለበት። ጉባኤ ካልተጠራና ሕገ መንግሥቱ አሁን ባለበት ሁኔታ ቀጥሎ ምርጫ ይካሄድ ከተባለ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ያሸንፋል፤ የአገሪቱ መሠረታዊ ችግሮች ግን ፈጽሞ አይፈቱም። እዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ነው ያለነው። ሕዝባችን ይህንን ሁኔታ ግልጽ አድርጎ መረዳት አለበት።

ችግር ቀፍቃፊው የቋንቋ ፌደራሊዝም ይቀየር

አሁን ከምንገኝበት አረንቋ ውስጥ የከተተን የትንሽነት ኀይሎች በፈጠሩት ትርክት መሠረት ላይ የቆመው ቋንቋ ተኮር ፌደራላዊ ሥርዓት ነው፡፡ ይህ በአገራችን የታሪክ ጉዞ ያልተደገፈ፣ የታሪክም የኢኮኖሚም የባሕልም መሠረት የሌለው ፌደራሊዝም በተግባር ሊቀጥል እንደማይችል ያለፉት 27 ዓመታት በሚገባ አሳይተውናል። አሁንም መዘዙን እያየነው ነው። በሥራ ላይ ያለው ፌደራላዊ ተብየ ሥርዓት ዲሞክራሲያዊ እንዳልነበርና እንዳልሆነ አሳምረን እናውቃለን፡፡ ዲሞክራሲያዊ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በቋንቋና በነገድ ላይ የተመሠረተ ፌደራላዊ አወቃቀር በግልጽ እንደሚታየው ጠንቀኛ ነው፤ ገፈቱንም እየቀመስነው ነው፡፡ በዚህ ከቀጠልን መዳረሻችን የእርስ በርስ ጦርነት መሆኑ ብዙም አያከራክርም፡፡

በዚህ የቋንቋ ፌደራላዊ ሥርዓት ምክንያት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ችግር ላይ ወድቋል። ካፒታሊዝም በተፈጥሮው ሰፊ ገበያ ይፈልጋል። ከትልቅ ገበያ ውጭ ካፒታሊዝም የለም። ሰፊ ገበያና አንደረ የተጠቃለለ ብሔራዊ ስሜት ይፈልጋል። ሁልጊዜ አገራዊ ስሜት የሚቀሰቀሰው ከአገራዊ ስሜት ጋር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ካፒታሊዝም አልዳበረም። አሁን ያለው አናሳና በግሎባላይዜሽን የመጣ ነው። እሱን እየተቀባበለ ነው የሚሸጠው። እስከመቼ ይዘልቃል? የተሟላ ኢንዱስትራላይዜሽን መምጣት አለበት። አሁን ያለውን አሳፋሪ ሁኔታ በምናይበት ጊዜ፣ የአማራ ከበርቴ ተብሎ ለብቻ፣ የኦሮሚያ ከበርቴ ተብሎ ለብቻ፣ የትግሬ ከብርቴ ወዘተ. እያለ ለብቻው ታጥሮና ተጠርንፎ የተቀመጠበት ነው፡፡ እነዚህ ከበርቴዎች እርስ በእርስ እየተነጋገሩ አንድነታቸውን ሲያጠናክሩ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በአንድ ላይ ያንቀሳቅሳሉ።

ሆኖም የምንከተለው ሥርዓት እንደመደብ አንድ ላይ እንዳይቆሙ፣ እርስ በእርስ እንዲናቆሩ እያደረገና ካፒታላቸው ተበትኖ የነገድ ብሔርተኝነት እየነገሠ ኢትዮጵያ ውስጥ ካፒታሊስ ለመሆን አይቻልም። ኢትዮጵያ ውስጥ ወጥ የሆነ የካፒታሊስት ሥርዓት ካልተመሠረተ እንዴት ነው ይህን ሥራ አጥ ወጣት አንቀሳቅሶ ገበያ ውስጥ ማስገባት የሚቻለው? አማራና ኦሮሞ እየተባለ እንዴት ወደገበያ ይገባል? እንዴት ጠንካራ ብሔራዊ ኀይል ይሆናል?

ስለዚህ አሁን እየተሠራ ያለው የካፒታሊስት ሥርዓትን የሚቃረን ነው። ካፒታሊዝም እንዲያድግ ሳይሆን ካፒታሊዝም እንዲጫጫ እየተደረገ ነው ያለው። ካፒታሊዝም እንዲከፋፈል እየተደረገ ነው። በእንደዚህ ዓይነት መዋቀር ላይ ምን ዓይነት የፖለቲካ መዋቅር ይዘረጋል? ምን ዓይነት አገርስ ይሆናል? ይህ ወጣት ካልበላ ራሱን ይበላል። የወደፊቱ ዕድላችን የእርስ በእርስ ጦርነት ነው። በዚህ ጎዳና ከሄድን የማይቀር ነው። እነ ሶርያን ማየት ነው፤ ሊቢያን ማየት ነው። የእርስ በእርስ ግጭት እንደ ብሔራዊ ጦር የምትዋጋው ጦርነት አይደለም። እርስ በእርስ ባገኘኸው መሣርያ ነው የምትዋጋው።

በኢትዮጵያ ሁኔታ ይህንን መገንዘብ የማይችል የፖለቲካ ኀይል በጣም ኋላቀር ነው። ኢትዮጵያ እንኳን በእንደዚህ ዓይነት መከፋፈል ውስጥ ገብታ ቀርቶ እኛ እንደምንመኘው ጠንካራ የተባበረ አቅም ያለው ካፒታሊስት መደብ፣ የተባበረ መካከለኛ መደብ ማለትም ዕውቀት ያለው ጋዜጠኛው፣ የሕግ ምሁሩ፣ ሐኪሙ፣ መሐንዲሱ፣ ከሥር እያደገ የሚመጣው ሳይንሳዊ ጥናት የሚያካሂደው የኅብረተሰብ ክፍል፣ የፈጠራ ሥራ ያለው አገር ካልሆነ ምን ዓይነት አገር ሊገነባ ነው? ዶክተሩ ሲመጣ እኔ ኦሮሞ ነኝ ይላል፤ ሳይንቲስቱ ሲመጣ እኔ አማራ ነኝ ይላል፡፡ በዚህ መንገድ እንዴት ዓይነተ አገር ይፈጠራል? ፈጽሞ የውድቀትና የትንሽነት መንገድ ነው፡፡

የሕገ መንግሥት ጉባኤ ይጠራ

የሕገ መንግሥት ጉባኤ ይጠራ ሲባል፣ በኢትዮጵያ ያለ ጥያቄ በሙሉ ጠረጴዛ ላይ ይቅረብ ማለት ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ፌደራላዊ አወቃቀር ነው የሚሉ ወገኖች ሐሳባቸውን ያቀርባሉ፤ ከፌደራላዊ አወቃቀር ውስጥም በቋንቋ ላይ ይመሥረት የሚሉትም በሌሎች መሥፈርቶች ላይ ይቁም የሚሉትም እንዲሁ ሐሳባቸውን እያቀረቡ በነጻነት ይከራከራሉ፡፡ አሐዳዊ ይሁን የሚሉትም እንዲሁ ምክንያታቸውን ያቀርባሉ። በሁሉም ኀይሎች መካከል ያለው ክርክር መድረክ ላይ ይውጣና በቴሌቪዥንና በሕዝብ ፊት ቀርበን እንወያይ። ሕዝብ ይወስን። ሕዝብ ተወያይቶበት ካወቀ በኋላ ይምረጥ።

በእንዲህ ዓይነት ሒደት አልፎ ብዙሃኑ ሕዝብ በቋንቋ ላይ የተመሠረተውን ፌደራላዊ አወቃቀር የሚመርጥ ከሆነ ባናምንበትም እንቀበላለን። የሕዝብ ምርጫ ነውና። የሚወስነው ሕዝብ ነው። እንዲህ ዓይነቱ የሕገ መንግሥት ክርክር የግድ መምጣት አለበት። አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የመጣው ሳንከራከር፣ በነጻነት ሳንመክርና ሳንዘክርበት ነው፡፡ ብዙዎቻችን ይህ ሕገ መንግሥት ሕጋዊ አይደለም፤ መሠረታዊ የሆነ የቅቡልነት ችግር አለበት የምንለው ለዚህ ነው፡፡

የዐብይ አሕመድ መንግሥት የሽግግር ሂደቱ ፍፁም ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ካልሠራ በታሪክ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ አገራችንም ተመልሳ ወደ አረንቋ መግባቷ አይቀርም፡፡ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት የሕወሓትና የኦነግ ጥንስስ ነው። ይህንን ሌንጮ ለታ ኢሳት ላይ ቀርቦ ያመነው ነው። “ንድፉን እኔ ነኝ ያረቀቅኩት፤ ካረቀቅሁት በኋላ ተሰኔ ላይ ኢሳያስና መለስ ዜናዊ አዩት፤ ተቀበሉትም፤” ብሏል። ይህ በ1983 ዓ.ም. ነው። በቀጥታ በደኖ ላይ የዘር ማጥፋት መፈፀም የጀመረው በዚያው ዓመት ነው። ይህ ማለት አማራ በሌለበት፣ ድርጅቶቹ ዲሞክራሲያዊ ባይሆኑ እንኳን፣ ፀረ ዲሞክራሲ የሆኑ ድርጅቶች ተሰብስበው አማራንም ወክለው ቢሆን እንኳ የአባት ነው። አሁን ያለው ሕገ መንግሥት አማራ የማያውቀው ሕገ መንግሥት ነው። አማራ ላይ የዘር ማጥፋት ለመፈፀም እንደመሣርያ የሚጠቀሙበት ሰነድ ነው።

የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግሥት “ይህ መሬት/ክልል የኦሮሞ ነው” ይላል። በዚህ ሁኔታ አማራ ቢገፋና ቢገደል ተጠያቂ ያለመኖሩ አያስደንቅም። ምክንያቱም በዚያ አካባቢ አማራ መኖር የለበትም፣ መሬቱ አይደለም ማለት ነው። ጉራጌ መኖር የለበትም፡፡ ከኦሮሞ ወጪ ያለው ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ መኖር የለበትም፡፡ የሚኖር ከሆነ እንደ ኹለተኛ ደረጃ ወይም በዘመኑ አነጋገር እንደ “መጤ” ይቆጠራል፡፡ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ተመሳሳይ ሕገ መንግሥት ነው ያለው። ሐረሪ ተመሳሳይ ሕገ መንግሥት ነው ያለው። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ሕገ መንግሥት ተይዞ በምንም ተዓምር ብትፈቀፍቀው፣ ብታሻሽለው፣ ብትቀባው የሚመጣ ለውጥ የለም።

ይህ ሕገ መንግሥት ገሸሽ ተደርጎ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ያገባኛል የሚል፣ የተደራጀም ሆነ ያልተደራጀ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦች የሚመጡበት፣ ሰፊ የሆነ የሰላም፣ የእርቅና የሕገ መንግሥት ጉባኤ ሊጠራ ይገባል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ተመክሮ፣ ተዘክሮ ለኢትዮጵያ ይበጃታል የሚባሉትን አንኳር ጉዳዮች አጠቃሎ የያዘው ሰነድ ለሕዝበ ውሳኔ መቅረብ አለበት። ሕዝበ ውሳኔው በአብላጫ ድጋፍ ካገኘ በዚያ ላይ የተመሠረተ አዲስ ምርጫ ይካሄዳል።

የእርስ በርስ ጦርነትን እናስወግድ

ስለምርጫ የምንነጋገርበት የቅንጦት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ ከሁሉም ነገር በፊት መነጋገር ያለብን ስለ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ይህን መንገድ አልቀበልም ካለ (እንደዚያ ዓይነት ስሜት እያንፀባረቀ ነው) እና በዚሁ ሕገ መንግሥት ላይ አንዳንድ ማሻሻያዎችን እያደረገ የሚቀጥል ከሆነ፣ ያለ ምንም ጥርጥር ኢትዮጵያ አዲስ ቀውስ ውስጥ ትገባለች። ለምሳሌ የእነሱ ሕገ መንግሥት እንዳለ ምርጫ ተካሄደ እንበል። የተወሰኑ ድርጅቶች ተካፈሉና ኢሕአዴግ አሸነፈ። ሀብቱን ስለያዘ ሊያሸንፍ የሚችልበት ሰፊ ዕድል አለ። ገንዘብ ይዟል፤ የመንግሥት መዋቅርን ይዟል፤ ማወናበዱን ይዟል፤ ሚዲያውን ይዟል። ሊያሸንፍ ይችላል። የተወሰኑ ሰዎችን ይዞ ፓርላማ ገባ እንበል። ያለው መዋቅር እንዳለ ነው። በቋንቋ ላይ የተመሠረተው የክልል አደረጃጀት እንዳለ ነው። በክልሎቹ ውስጥ ያለው ፍላጎትም እንዳለ ነው። ለምሳሌ ደቡብ ላይ ብዙዎቹ የክልል ጥያቄ እያነሱ ነው። መሬት እያሉ ነው። አንዱ አንዱን በኀይል የተያዘብኝን መሬት ልቀቅ እየተባለ ነው በየቦታው፡፡ አይሆንም ሲባል የሚከተለው ጦርነት ነው፡፡

አሁን ያለውን አደገኛ ሁኔታ ካልፈታንና ወደቀልባችን ካልመጣን የእርስ በእርስ ጦርነት መምጣቱ አይቀርም። የእርስ በእርስ ጦርነት እርሾዎቹ እየተሠሩ ነው። እነዚህን ሁኔታዎች ማዳፈን ዋጋ የለውም። እሳት ብታዳፍነው ነገ ጠዋት ይነሳል። መፍትሔ ነው መስጠት ያለብን። እነ ዶ/ር ዐቢይ በማዳፈንና በመቀባባት እየሠሩ ነው። ፖለቲከኛ ማለት ደግሞ መፍትሔ የሚሰጥ ነው። ያን መፍትሔ የማይሰጥ ከሆነ ፖለቲከኛ አይደለም፤ መልቀቅ ነው ያለበት። ምክንያቱም መፍትሔ የማመንጨት ኀይሉ አልቋል ማለት ነው። አንድ ፖለቲከኛ መኖር የሚችለው መፍትሔ የመስጠት ችሎታ እስካለው ድረስ ነው።

No comments: