Thursday 1 November 2018

አገሪቱ መበታተንዋ አይቀሬ እየሆነ ነው

ፍስሃ ከበደው


የአገራችን ፖለቲካዊ ስርዓት በአሁኑ ሰአት ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት ወደ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ፍፁም በማያጠራጥር መንገድ ተቀይሯል ማለት ይቻላል ፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት የመጣው ለውጥ በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አንድ ያደረጋቸው ህገ መንግሥት በማፍረስ በአገሪቱ ስርአት ኣልባ የሆነ አካሄድ እንዲፈጠር በማድረግ በቀጣይ ወደ ተጠነሰሰው የፖለቲካ ስርአት ለውጥ ለመግባት የሚያስችል ምቹ መደላደል ለመፍጠር ራሱን የለውጥ ሃይል አድርጎ የሚንቀሳቀስው ፅንፈኘኛው ሃይል የወሰደው እርምጃ መሆኑ አሁን አሁን ግልፅ እየሆነ መጥቷል ፡፡ በዚህ መሰረት ይህ ሃይል የፈለገውን የስርአት ለማምጣት ሊተገብራቸው ያሰባቸው የማስፈፀሚያ ስልቶች የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል -

1- ኣብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ማዳከምና ከተቻለ ቀስ በቀስ ማጥፋት 

የነበረውን ስርአት ለማስቀጠል የሚፈልግ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሃይሉን ቅድምያ ጠራርጎ በማስወገድ ከታሰበው ለውጥ ጋር የሚራመድ የራሱን ተቀጥያ የሆነ ድርጅትና መንግሥት ማዋቀርና ማጠናከር ፅንፈኛው ሃይል ቅድምያ ሰጥቶ እየተረባረበበት ያለ ስራ ነው ፡፡ይህን ለማሳካት በሶስት መንገድ ነው እየፈፀሙው ያለው፡፡ በዚህ ጎራ እንደቀንደኛ ጠላት የተመደበው እንደ ድርጅት ህወሓት ሆኖ በግለሰቦች ደረጃ የብአዴን ነባር ታጋዮችም በዚህ ምድብ መሆናቸው ግልፅ ነው ፡፡ ይህን ሃይል የመጀመሪያው የተቀመጠው ስልት ፀረ ለውጥ ነው በሚል በመፈረጅ የቀን ጅቦች ፀጉር ልወጥ የሚል ስያሜ በይፋ በተለያዩ ሚድያዎች በመጠቀም ከተቻለ እነዚህ ሃይሎች ከህዝቡ በመነጠል ማፈራረስና በአገሪቱ ፖለቲካ ምንም አይነት ሚና እንዳይኖራቸው በማድረግ አሱ እንደፈለገው የሚየደርጋት አገር መፍጠር የሚል በተለይ በጠ/ምኒስትሩ የሚመራው ቡድን ይህ ለማሳካት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም ማለት ይቻላል ፡፡ ለወደፊትም አይኖርም ፡፡
ሌላው የማስፈፀሚያ ስልታቸው ይህ ሃይል ባሰቡት መንገድ ከህዝቡ መነጠል ካልቻለ በሃይል የህግ ሉአላዊነት እናስከብራለን በሚል ሽፋን የሚፈለገውን ሃይል በቁጥጥር ስር በማስገባት እንዲታሰር እንዲሰቃይ በማድረግ በማስፈራራት ከእንግዲህ ወዲህ ትግል አይቻልም ብለው ተስፋ ቆርጠው እጃቸው እንዲሰጡ የማድረግ አላማ በመያዝ በተለያዩ መንገዶች እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ፡፡ የዚህ ማሳያ ባለፈው ወር በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈፀመው ፀረ ህገ መንግስት ኣካሄድ ኣንዱ ማሰያ ነው ፡፡ ሶስተኛ የሚከተለው ስልት ሁለቱን ከላይ የተገለፁት ስልቶች ካልተሰኩ በተለይ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሃይሉ ኮርና በቀላሉ ሊቀለበስ አይችልም ብለው የሚገምቱትን የትግራይ ህዝብና ድርጅቱ የመጨረሻ ስልታቸው የውስጥና የውጭ ሃይሎች በማቀናጀት ሃይል በመጠቀም ከቻሉ መንግስታዊ መዋቅሩ በማፍረስ ህልውናው ማጥፋት የሚል በተለይ አሁን አሁን ለዚህ ቀንደኛ ማስፈፀሚያ የሆነ የአማራ ክልል መንግሥት ከኤርትራ መንግሥትና ሌሎች የውጭ ሃይሎችን በማሰለፍ በሁሉም ዘርፍ በቂ ዝግጅት በማድረግ ቢሳካም ባይሳካም ለሙከራ ግና በስፋት እየሰሩበት ያለው የትርምስ አጀንዳ ለማንም የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
2- ፌደራላዊ ስርዓቱን ማፍረስ
አገራችን በፈዴራሊዝም የመንግሥት ስርዓት የተዎቀረች ነች ፡፡
ይህ ስርዓት የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እውቅና የሰጠና ህዝቦች በራሳቸው ቋንቋ እንዲናገሩና መንነታቸውና ባህላቸውን እንዲያሳድጉ የሚፈቅድ በፖለቲካም ራሳቸው በራሳቸው ማስተዳደር የሚፈቅድ በኢኮኖሚሞ ባለቸው አቅም ክልላቸውን በማልማት ተጠቃሚ አንዲሆኑ ዕድልና ዋስትና የሰጠ ህገመንግስታዊ ስርዓት ነው ፡፡ ይህ ለህዝቦች ትልቅ ድል እንዲጎናፀፋ ያደረገ ህገመንግስታዊ ስርአት ለማንም ፈላጭ ቆራጭ መሆን የሚፈልግ ስልጣን ላይ ያለ ሃይል እንደማይመች የታወቀ ስለሆነ አሁን እየታሰበ ላለው በውጭ ሃይሎች የሚመራ ተላላኪ መንግሥት ስለማይመች ይህን ለማፍረስ መጀመሪያ በደቡብ ህዝቦች ክልል ቀጥለው ደግሞ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በኢትዮጵያ ሶማሌና ጋምቤላ ህገመንግስታዊ ስርአቱን የማፍረስ ስራው ተግባራዊ ማድረግ ጀምረውታል ፡፡
ይህ አካሄድ በተለይ ዋነኛው የራስምታት የሆነባቸው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕረዚዳንት በአሁኑ ሰአት መቆጣጠር ችለናል ብለው እንደ ትልቅ ድል ስለቆጠሩት በሌሎች ክልልም ማለት በነሱ አገላለጽ ለኛ አይታዘንምም የሚሉትን ክልል በየተራው የመጨፍለቁ ስራ እንደሚቀጥሉበት ምንም ጥርጥር የለውም ፡፡
3 - ሚድያውን በመቆጣጠር የህዝቡን ተቃውሞ ማፈንና ለሚቃወማቸው  አይቀጡ ቅጣት መቅጣት ዋነኛ የማስፈፀሚያ መንገድ ማድረግ ፡፡
የአገራችን ዴሞክራሲያዊ ጉዞ በተፈለገው መንገድ ባለማደጉ በተለይ በስልጣን ላይ የነበረው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ባለፉት ዓመታት መሰረት ቢጥልም ዴሞክራሲው ማደግ በሚገባው ደረጃ እንዲያድግ ባለመስራቱ በተነሳው የህዝብ የለውጥ ጥያቄ ተገን አድርጎ ወደ ስልጣን የመጣው ሃይል ከመጀመሪያው ይዞት የተነሳው የማደናገሪያ ስልት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በቁርጠኝነት እሰራለሁ ማለቱ በተለይ በወጣቱ ክፍል ለአጭር ጊዜ ቢሆንም ተቀባይነት ያገኘለት መፈክር ነበር ማለት ይቻላል ፡፡ ይህ የማደናገሪያ ስልት ግና ብዙ ርቀት ሳይጓዝ ወደ ፍፁም ፀረዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው የተሸጋገረው ፡፡ የአንድ ሉአላዊ ክልል በህዝብ የተመረጠ መሪ ካልተፈለገ ውረድ በሚል ቀጭን ትእዛዝ ማውረድ ማሰር የልማት አርበኛ መግደል የተቃወመ ማስፈራራት በየቀኑ የሚሰሩ የዕለት ተዕለት ተግበራት ሆነዋል ፡፡ መንግሥት ባለበት አገር በጠራራ ፀሃይ አገር ሰላም ነው ብለው ወደ ስራቸው የወጡ ዜጎች ምንም ጥፋት ሳይፈፅሙ በዘረኞች ሲገደሉ ማየት የተለመደ ሆነዋል ፡፡ የዚህ ሁሉ ፍፃሜ መልእክቱ እንደ ትናቱ የደርግ ስርዓት ያደርገው የነበረ ኢትዮጵያ ትቅደምን የሚቃወም ሰው ማሰርና መግደል አሁንም ለውጥ የሚቃወም ሃይል በግልፅ እንደ ደርግ በአዋጅ የታወጀ ህግ ባይኖርም የፀጥታ መዋቅሩ ግና በፈለገው መንገድ ለተቃወመ ዜጋ መቅጣት እንደሚችል በቅርቡ በዜጎች ከተፈፀሙ ጥቃቶች መረዳት ይቻላል ፡፡
በጣም የሚገርመው ይህ ጉድፍ ስራ እየሰራ ያለው መንግሥት የህዝቡን ሚድያ በመቆጣጠር በየቀኑ የሌለ ለውጥ አርትፍሻል ዜናዎች ቅንብሮች በማቅረብ በአንድ ሰው ተአምር ስራ እየተሰራ ነው እያሉ በየቀኑ በመስነክ ላይ ናቸው  ፡፡ የዜጎች ሞት መሰደድ ትተው በሌለ ለውጥ ህዝብን ለማታለል አይናቸው ጨፍነው ህገመንግስታዊ ስርአቱን በማፍረስ ስራ ላይ ተጠምደዋል ፡፡ ይህ ህዝቡን የማታለል ስልት በቀጣይ ሳይሳካ ሲቀርና ህዝቡ ሓቁን እያወቀ መቃወም ሲጀመር በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እንደታየው አይነት የህዝቡ ተቃውሞ መሸከም ስለማይችል መጀመሪያ ተቃውሞውን ማፈን በዛ ከቀጠለ ግና ህዝቡንና በተለይ ተቃውሞውን የመሩት ሃይሎች ማሰር ማስፈራራትና መግደል በስፋት እንደሚቀጥል ከወዲሁ በቂ ምልክቶች እየታዪ ናቸው ፡፡
ሰለዚህ አሁን በሁሉም መንገድ በስልጣን ላይ ያለው መንጋ ስልጣኑን በመቆጣጠር አንድና አንድ መፈክር አንግቦ ወደድክም ጠላህም ለውጡን ተቀበል በሚል ፅንፈኛ አቋም በመከተል የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተከባብረውና ተፈቃቅደው መኖር የጀመሩበትን ፌደራላዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በማፍረስ የውጭ ሃይሎች በሚሰጡት ትእዛዝ የሚመራ አሻንጉሊት መንግሥት በኢትዮጵያ በመትከል ዓላማ ያለው ሃይል በመሆኑ ከእንግዲህ ወዲህ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ መበታተኑ አይቀሬ ነውና በተለይ ኣብዮታዊ ዴሞክራስያዊ ሃይሉ  ከወዲሁ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል ፡፡

No comments: