Monday 5 November 2018

የትግራይና አማራ ልኂቃን ውድቀት – ብርሃኑ አበጋዝ (ዶ/ር)

የትግራይና አማራ ልኂቃን ውድቀት አገራችንን ውድ ዋጋ እያስከፈላት ነው፡፡ በዚህች አጭር ጽሑፍ ስለአማራና ትግራይ ወንድማማችነትና እህትማማችነት፣ ስለሁለቱ ሕዝቦች ኅብረትና አንድነት መናገር አልፈልግም፤ በደንብ የሚታወቅ ስለሆነ፡፡ እነኝህ አንድም ሁለትም የሆኑ ሕዝቦች በታሪክ፣ በሃይማኖት፣ በፊደል፣ በሥነ-ልቦና አንድና ያው መሆናቸው የማያጠራጥር ሐቅ ስለሆነ፡፡ የእኔ አጀንዳ በእነኝህ የኢትዮጵያ ምሰሶዎች ላይ ልኂቃኑ ምን ያህል በደል እንዳደረሱባቸውና እያደረሱባቸው እንደሆነ የተወሰኑ ነጥቦችን መፈንጠቅ፣ ይልቁንም ወደለየለት ዝቅጠት እየወረደ የመጣው ልኂቅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁለቱን ወንድምና እህት ሕዝቦች ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊማግዳቸው እየሠራ መሆኑን ለመግለጽ እና አገርና ሕዝብ ወደ ከፋ መከራ ከመግባታቸው በፊት ሁላችንም መፍትሔ የምንለውን ምክረ-ሐሳብ እንድንሰነዝር ለማሳሰብ ነው፡፡
ለመሆኑ በእንዲህ ዓይነት ምስቅልቅል ውስጥ የጨመረን ምንድነው? ይህን አደጋ ኮትኩቶ በማሳደግ ረገደ የልኂቃኑ ሚና ምን ያህል ነው? መፍትሔውስ ምንድነው? በእነዚህና እነዚህን በመሳሰሉት ጥያቄዎች ላይ ጊዜ ሳናባከን ልንወያይባቸው ይገባል፡፡ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ፖለቲከኞች በእነኝህ መሠረታዊ አጀንዳዎች ላይ ልንመክር ልንዘክር ይገባናል፡፡
አስተኔ ምሁራን
***
ተማርን የምንለው ኢትዮጵያዊያን “ምሁር” የሚለውን ትልቅ ማዕረግ የመሸከም አቅሙም የሞራል ልዕልናውም የለንም፡፡ የበቀለበትን ኅብረተሰብ ዕሴት በሚገባ በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ያልመረመረ፣ የውጭውንም ዓለም አቀፍ ሁኔታ በሚገባ ፈትሾ ከአገራዊ ሁኔታው ጋር በማስታረቅ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ዕውቀት ማመንጨት ያልቻለ አካል “ምሁር” የሚለውን መጠሪያ መሸከም ከቶም አይችልም፡፡ ተማርን የምንል ኢትዮጵያዊያን ትልቁ ችግር ይህ ነው፡፡ በአንድ በኩል የበቀልንበትን ኅብረተሰብ ዕሴት በዕውቀት ላይ ተመሥርተን አልመረመርነውም፤ አናውቀውም፡፡ ስለኢትዮጵያ እያወራን ነገር ግን ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ያለን ዕውቀት እጅግ ደካማ ነው፡፡ የአገራችን ባህልና ዕሴት በመናቅ መንፈስ ወደ ውጭ ብናማትርም በአንድ በኩል የውጭውንም መጠንቀቅ አልተቻለንም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከውጭ የቃረምነውን ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አስማምተን መጠቀም አልቻልንም፡፡
በዚህ ምክንያት ተማረ የሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል አብሪ ኮከብ ሆኖ አገርና ሕዝብን ወደፊት ከማራመድና አቅጣጫ ከማሳየት ይልቅ በአውዳሚ አጀንዳዎች ላይ መሰለፍን ግብሩ አድርጓል፡፡ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ደጋግመው እንዳስገነዘቡት የራሱን ጥሎ የሌላውን የሚያንጠለጥል፣ የራሴን ያዝኩ በሚልበት ጊዜም የእኔ ብቻ ይበቃኛል ወደሚል መታበይ የሚወርድ ቅጥ-አምባሩ የጠፋበት የኅብረተሰብ ክፍል ነው፤ “ምሁሩ”፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት የትግራይና አማራ “ምሁራን” ናቸው፡፡ እነኝህ የድሃ ድሃ ከሆኑ ማኅበረሰቦች የወጡ “ምሁራን” ሕዝባቸው ከገባበት የብሉይ ዘመን ድህነት እንዴት መውጣት እንዳለበት የመፍትሔ ሐሳብ ሲያቀርቡ አይታይም፤ ሕዝብ ሊጠቅሙ የሚችሉ የፈጠራ ውጤቶችን ሲያቀርቡ አይሰማም፤ የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነት ስለሚጠናከርበት፣ ሺሕ ዓመታት ያስቆጠሩ የጋራ እሴቶቻቸው ከዘመኑ ጋር ስለሚዘምኑበትና ስለሚጎለምሱበት ሁኔታ አይመክሩም፤ አይዘክሩም፡፡ ከዚህ ይልቅ በሚያሳፍር መልኩ ተማርኩ የሚለው ኀይል ነገሮችን ይበልጥ በማጋጋል ላይ ተጠምዷል፤ ጥላቻና ግጭት የሚፈጥሩ የጥፋት አጀንዳዎችን በማምረት ላይ ተሰማርቷል፡፡
ዛሬ በሚያሳፍር ደረጃ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሳይቀሩ የሚጠበቅባቸውን ተልዕኮ ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ ወጣቱን አክራሪ በሆነ ዘውጌ ብሔርተኝነት ኮትኩተው እያሳደጉት ይገኛሉ፡፡ ገለልተኛ ሆነው ሁሉንም የኢትዮጵያ ልጆች በእኩል ደረጃ በዕውቀት መኮትኮት የሚገባቸው የዩኒቨርሲቲ መምህራን አክራሪና አውዳሚ በሆነ የዘውግ ፖለቲካ ተጠምደው ይውላሉ፡፡ መምህራኑ ለደቀ-መዝሙሮቻቸው አርአያ መሆን ሲገባቸው ፌስቡክ ላይ ወጥተው ጥላቻን ይሰብካሉ፤ ግጭት ቀስቃሽ በሆኑ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፤ በሕዝብ መካከል ጠባሳ የሚጥል ተግባር ይፈጽማሉ፡፡ ስለውይይትና አብሮ ስለማደግ አይጽፉም፤ ስለጋራ ዕሴቶቻችን አይናገሩም፡፡ ሥራቸው ሁሉ ከተማረ ሰው ፈጽሞ የማይጠበቅ ነው፡፡
ሕወሓትና ብአዴን፤ ሥራ ፈጠራ ወይስ ጦርነት?
***
አደጋውና ዝቅጠቱ በ”ምሁራኑ” ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ሁለቱን ክልሎች የሚመሩት የፖለቲካ ድርጅቶችም በሁሉም ረገድ ወድቀዋል፡፡ እነኝህ በትግራይና አማራ ሕዝቦች ስም የተቋቋሙ ድርጅቶች በሁለቱ ሕዝቦች ዘላቂ ግንኙነት ላይ የፈፀሙት ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል በሚገባ ሊጋለጥ ይገባዋል፡፡ ሕወሓት ገና ከፅንሱ ጊዜ ጀምሮ በከፍተኛ ድህነትና ቁስቁልና ውስጥ የሚገኘውን የአማራን ሕዝብ እንደ ጨቋኝ በመሳል፣ ሰነድ አዘጋጅቶ የትግራይን ልጆች ሲያስተምር ኖሯል፡፡ በሁለቱ ወንድምና እህት ሕዝቦች መካከል ለሺሕ ዘመናት የተገነባውን የአብሮነት እሴት ለመናድና ትግራይ ከአማራ ጋር የሚያገናኘው የታሪክም የባህልም ክር የለም የሚለውን በሬ-ወለደ በሕዝብ ላይ ለመጫን ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም፡፡ ሕወሓት ሰፊው የትግራይ ሕዝብ በሁለንተናዊ መልኩ ወንድሙ የሆነውን የአማራን ሕዝብ እንዲጠላ ማድረግ ባይቻለውም ብዙሃኑ የትግራይ ልኂቅ ግን የሕወሓት አውዳሚ ትርክት ሰለባ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕወሓት በአማራ ሕዝብ ላይ ሦስት ዐሥርት ለሚጠጉ ዓመታት መጠነ-ሰፊ ውርጅብኝ ሲያወርድ “ተው አይሆንም፤ ትክክል አይደለም፤” ያለ አካል አልታየም፡፡
ሕወሓት የእጅ ሥራው በሆነው ብአዴን አማካይነት በአማራ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ግፍ ፈፅሟል፡፡ ሆኖም ለጊዜው ካልሆነ በስተቀር ሕዝብን ማሸነፍ አይቻልምና የአማራ ሕዝብ የሚደርስበትን የግፍ ቀንበር ከላዩ ላይ አሽቀንጥሮ ለመጣል ቆርጦ ከተነሳ ማግስት ጀምሮ የብአዴን አመራሮችም ዐይናቸውን በጨው አጥበው የለውጥ ሐዋሪያ ሆነው ቀርበዋል፡፡ ሳያፍሩ ሳይፈሩ የትግሉ ዋና ተዋናዮች እኛ ነን እስከማለትም ሄደዋል፡፡ ትናንትና ከሕወሓት ጋር በመሆን ሕዝብ ሲያሸብሩ የነበሩ ግለሰቦች ኮታቸውን ቀይረው “የለውጥ ኀይል” የሚል ማዕረግ ተሰጥቷቸው እንደ ጀግና እየተወደሱ ይገኛሉ፡፡ በጥቅም ኔትዎርክ ተሳስረው ሕዝብ ሲያማርሩ የኖሩ ግፈኞች የመደመር ፊታውራሪዎች ለመሆን በቅተዋል፡፡
የትግራይን ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ደም ያቃባው ግፈኛው የሕወሓት ቡድንም እየተወደሰ ነው፡፡ ከአማራ ወንድሙ ጋር ሊያፋጀው ቆርጦ የተነሳውን ግፈኛ ቡድን የትግራይ ልኂቅ አቅፎ ደግፎ ይዞታል፡፡ በአማራ ሕዝብ ላይ መጠነ-ሰፊ በደል ያደረሰውን ብአዴንንም የአማራ ልኂቅ እንደ ለውጥ ኀይል ቆጥሮ እየተንከባከበው ነው፡፡ ብአዴንና ሕወሓት በበኩላቸው የልኂቃኑን ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ስሜት ቀስቃሽና ኮርኳሪ የሆኑ የማንነት አጀንዳዎችን በማጦዝ ላይ ይገኛሉ፡፡

ወጣቱ የሚፈልገው ሥራ ነው፤ ጥራት ያለው ትምህርት ነው፡፡ ሕዝቡ የሚፈልገው ከገባበት የብሉይ ዘመን የድህነት አረንቋ መውጣት፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃና የጤና ተቋማትን በአቅራቢያው ማግኘት ነው፡፡ ሕዝብ መሠረተ-ልማት ነው እየጠየቀ ያለው፡፡ በሰላም ወጥቼ የምገባበት ሰላማዊ ሁኔታ ይኑር እያለ ነው ያለው ሕዝባችን፡፡ ችግሩ፣ ሕዝብ የሚጠይቀው ሌላ ሕወሓትና ብአዴን የሚሰጡት መፍትሔ ሌላ መሆኑ ነው፡፡ እነኝህ ያረጡ የፖለቲካ ድርጅቶች ለስሙ “ጥልቅ ተሐድሶ” አድርገናል እያሉ ለማደናገር ቢሞክሩም በምንም ዓይነት መልኩ የመታደስ ምልክት አይታይባቸውም፡፡ ስለሆነም ዋና ዋናዎቹን የሕዝብ ጥያቄዎች ተቀብለው ለመፍታት ጥረት እያደረጉ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ የማኅበራዊ ሚዲያ አክቲቪስት የሚያነሳቸውን አጀንዳዎች በመለቃቀም በአላፊ-ጠፊ አጀንዳዎች ላይ ሲንጠላጠሉ ይስተዋላል፡፡
ድርጅቶቹ አንዱ ሌላውን የሚጎነትል መግለጫ በማውጣት ላይ የተጠመዱት የአክቲቨስቶችን ቀልብ ለመሳብና ድጋፍ ለማሰባሰብ እንደሆነ በደንብ ይታወቃል፡፡ ዘለቄታዊ በሆኑና ሕዝብ ሊጠቅሙ በሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ሳይሆን የማኅበራዊ ሚዲያ ፊት እያዩ በጭፍጫፊ ጉዳዮች ለማተኮር የተገደዱት አዳዲስ አስተሳሰቦችንና አሠራሮችን የማፍልቅ አቅማቸው ስለመከነ እና ስላረጡ ነው፡፡ በመሠረቱ፣ የሁለቱም ድርጅቶች ቦታ መንግሥታዊ ሥልጣን ሳይሆን የታሪክ ቅርጫት ብቻ ነው፡፡
ወልቃይትና ራያ፤ የአጭር ጊዜ መፍትሔ
***
በትግራይና አማራ ክልሎች መካከል ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል፡፡ ዜጎች በትግራይ ልዩ ኀይል አልሞ ተኳሾች በጠራራ ፀሐይ እየተገደሉና ታፍነው እየተወሰዱ ሲሆን፣ ሁለቱን ክልሎች የሚያገናኙ መንገዶችም እየተዘጉ ነው፡፡ ውጥረቱ ወደ ለየለት የእርስ በርስ ጦርነት እንዳያመራ ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሊመከር ሊዘክር ይገባል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የሁለቱ ዘውጌ ማኅበረሰቦች ልኂቃን ከገቡበት አረንቋ ወጥተው የችግሩ ሳይሆን የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ ያስፈልጋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል የሚከሰት ግጭት ከፍ ያለ ውድመት እንደሚያስከትል ሳይታለም የተፈታ በመሆኑ ጉዳዩ በመንግሥትም በኩል ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
በእኔ አስተያየት የወልቃይትና ራያ ጥያቄ ሁለቱን ክልሎች ወደ ግጭት ሊስገባቸው አይገባም፡፡ ጉዳዩ በንግግር፣ የሁለቱን ወንድም ሕዝቦች አብሮነትና ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ መልኩ ነው ሊፈታ የሚገባው፡፡ ይህ ደግሞ በሁለቱም ወገን በኩል ቅንነቱና ቁርጠኝነቱ ካለ በደንብ ይቻላል፡፡ እንደ መነሻ ወይም እንደ አጭር ጊዜ መፍትሔ ሊቀመጥ የሚገባው፣ በእነዚህ አካባቢዎች ትግርኛና አማርኛ ቋንቋዎች በጋራ የመንግሥት ተቋማት የሥራ ቋንቋዎች እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ የፖለቲካ ኀይሎችና ልኂቃኑ አርቆ የማሰብ አቅማቸው እጅግ ደካማ ስለሆነ ነው እንጂ አማርኛም ትግርኛም ተመሳሳይ ፊደል የሚጠቀሙ፣ ሁለቱም በርካታ የግዕዝ ፊደላትን የሚወርሱ እህት ቋንቋዎች ስለሆኑ፣ በድንበር አካባቢ በሚገኙ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ትግርኛና አማርኛ የጋራ የሥራ ቋንቋዎች ቢሆኑ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጅ የሚሆን ወገን የለም፡፡
ወልቃይትና ራያ ውስጥ አማርኛ ቋንቋ በመንግሥት ተቋማት እንዳይሠራበት ማድረግ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ብቻ ሳይሆን፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል የማይበርድ ግጭት እንዲቀሰቀስ ምክንያት የሚሆን ጠንቀኛ አካሄድ ነው፡፡ መታረም አለበት፡፡ ከፍ ብየ እንደገለጽሁት [የአጭር ጊዜ] መፍትሔው ሁለቱንም ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋ ማድረግ እና ሁሉም ዜጋ በፈለገውና በመረጠው ቋንቋ አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራር በብዙ የአውሮፓ አገሮች የተለመደና ትልቅ ሸክም የሚያስቀር የሰለጠነ መንገድ በመሆኑ ሊከብደን አይገባም፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ኬላዎች፣ ፍርድ ቤቶች፣ ሲቪል ሰርቪሱ ወዘተ. በአማርኛና በትግርኛ ቋንቋ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ለሁለቱ ክልሎች ግንኙነት የመጀመሪያው መልካም እርምጃ ነው፡፡ ዜጎች በሚችሉትና በሚፈልጉት ቋንቋ አገልግሎት የማግኘት ሙሉ መብት አላቸው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ያንን መብት ዕውቅና መስጠትና ወደ ተግባር መቀየር ነው፡፡
ኦዴፓ፤ አዲሱ ሕወሓት?
***
ሕወሓት ሦስት ዐሥርት ለሚጠጉ ዓመታት በሥልጣን ላይ ተንፈራጦ የኖረው አማራንና ኦሮሞን በማጋጨት ሲሆን፣ ይህን ተልዕኮ ሲያስፈፅመው የቆየው ደግሞ በብአዴንና ኦሕዴድ አማካይነት ነበር፡፡ የአማራና ኦሮሞ ልኂቃን እርስ በርሳቸው ሲናቆሩ ሕወሓት በገላጋይነትና ሸምጋይነት እየገባች ሥልጣኗን አራዝማለች፡፡ አሁን ያ ሁሉ አቅሟ የለም፤ ያለጥርጥር ድርጅታዊ መበስበስ ገጥሟታል፡፡
አደጋው፣ ዶ/ር ዐቢይ የሚመሩት ኦዴፓ የሕወሓትን ሚና እንዳይወስድ ነው፡፡ የማያጠራጥረው ሐቅ፣ በብአዴንና ሕወሓት መካከል የሚደረግ ሽኩቻ ከማንኛውም አካል በላይ ተጠቃሚ የሚያደርገው ኦዴፓን የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ እነ ዶ/ር ዐቢይ ሕወሓትን መተካት ፍላጎት ካላቸው ደግሞ በአማራና ትግራይ ክልሎች መካከል የሚታየው ግጭት መፍትሔ እንዲያገኝ አይፈለግም፡፡ የአማራና ትግራይ ልኂቃን ይህንን ሁኔታ በአንክሮ መከታተል ይኖርባቸዋል፡፡
ለማናኛውም፣ ኢሕአዴግ ራሱን የእኩል ድርጅቶች ግንባር ማድረግ ካልቻለና እንዳለፉት ዘመናት አንዱ ድርጅት ገንግኖ ከወጣ፣ ለምንመኘው የዴሞክራሲ ሽግግር ምዕራፍ ትልቅ አደጋ ነው፡፡ ሁላችንም በዐይነ ቁራኛ ልንከታተለው የሚገባን ጉዳይ ይመስለኛል፡፡

 የአክሱም ፖስት አስተያየት
 ችግሩ ያለው የአማራ  ሊህቃን ላይ ነው:: አሁንም ችግሩን  ህዝብን በሐሰት ወሬ በማዋከብ ለመፍታት መሞከር  በ"አማራ" ጎጠኞች በኩል አርማት መደረግ አለበት::ትግራይ የጠየቀውና የያዘው ታሪካዊ ቦታዎቹን  ነው:: በኦሮሞዎች የታየዘውን የአማራዎች  መሬት አንዲመለስ መደረ ግ አለበት:; ለዚህም ዋናዉ ተንቀሳቃሽ የአምራ ፖለቲከኞች መሆን ይኖረባቸዋል:: ትግራይ በማስረጃ በተመሰረተ የኦሮምና የአማራ ግዛት መካለል አንዲኖር ማደረግ አለባት:: አስካሁን የታየው ግን ለአምራ ይልቅ 
ለኦሮሞዎ ች  ህወሓት ስትወግን  ነው :: ይህ መታረም አለበት ! አሁን "ኦሮሞ " ተብሎ የሚጠራው ግዛት መቀየር አለበት:; አንደዚሁም ሶማሌ ተብሎ የ ሚጠራው ግዛት ወደ ቀድሞ የመጠርያው ስሙ አንድቀየር መደረግ አለበት:: የ ውስጥ የአስተዳደር ግዛት መወሰን  ያለበት የታሪክ ማሰርጃ ላይ መሰረት ባደረገ  መንገድ አንጂ በስሜትና  ለግዚያው ፖለቲካ ጥቅም ተብሎ መሆኑ አደገኛ ነው:;

No comments: