Tuesday 20 November 2018

ስለ ለውጡ የገባው ሰው ካለ ቢያስረዳኝ

ዶ/ር ዮሃንስ አበራ አየለ
(ተ.ፕሮ)

ፈረንጆች አንድን ጉዳይ እግር በግር ሲከታተሉት ይቆዩና የሆነ ቦታ ላይ ሲደበላለቅባቸው "I got lost"፣ ጠፋኝ ሳይሆን ጠፋሁ በማለት ይገልፁታል። ለዚህ ነው የተዘበራረቀብኝ ለኔ ብቻ እንዳይሆን ብየ ራሴን በመጠራጠርና ሌላውን ሰው ሁሉ በማክበር ለዚህ ፅሁፍ አልገባኝም አስረዱኝ የሚል የተማፅኖ ርእስ ያበጀሁለት።
ለኔ እንደሚገባኝ "ለውጥ" የሚለው ቃል በጥሬ ትርጉሙ የግድ በጎ ነገር መምጣቱን የሚያመለክት አይደለም። ለውጥ ወደ ጥሩም ወደ መጥፎም፣ ወደ ታችም ወደላይም፣ ወደኋላም ወደፊትም፣ ሊሆን ይችላል። እንዲሁ በተለምዶ ነው እንጂ ለውጥ ሲባል ከበፊቱ የተሻለ ነገር መጣ ማለት አይደለም። ደርግ "ለውጥ"፣ "የለውጥ ሃዋርያት" እያለ ያመጣብን መአት ያ ሲወገዝ የነበረው ንጉሳዊ አገዛዝ በአንፃራዊነት የተሻለ ሆኖ ይታይ ነበር። ትክክል ባይሆንም ህዝብ በለውጥ ስም የባሰ ነገር ሲገጥመው ከለውጡ በፊት ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ ይመኛል። ይህ ማለት ግን ደርግ አንዳችም ጥሩ ነገር አልሰራም ማለት አይደለም። ስልት በጎደለውና ጭካኔ በሞላበት አግባብ ይሁን እንጂ፣ በተሻለ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር አይተካው እንጂ ያ በህዝብ ፈቃድ ሳይሆን በአምላክ ቅባ-ቅዱስና በዘር ሃረግ ስልጣን የሚያዝበትን፣ መሬት አልባ አራሽ የሰፈነበትን የበሰበሰ የፊዩዳል ስርአት ከስሩ ነቅሎ ሁለተኛ እንዳይመለስ ማድረጉ በታሪክ ተመዝግቦለታል። ይህ ታላቅ ሥራ እንዲኮስስ ያደረገው ግን በቀሪው የህዝቡ ህይወት ላይ ደርግ ሲሰራ የነበረው ክፉ ድርጊት ነበር። ለውጥ አመጣሁ ተብሎ  አንዲት ነገር በስጦታ ሰጥቶ ካስጨበጨበ በኋላ ሰላማዊ ህይወቱን፣ የኢኮኖሚ መሠረቱን፣ ቤተሰባዊና ማህበረሰባዊ ግንኙነቱን ምስቅልቅሉን ሲያወጣበት የኢትዮጵያ ህዝብ የለውጡ አላማ ምን እንደነበረ ጠፋው! በለውጥ ስም እራቱን ባይበላም በሰላም ተኝቶ ማደር ሲያቅተው፣ ልጆቹ በወጡበት ሲቀሩ፣ የፍትህ ስርአቱ ፋይዳቢስ ሆኖ ብረት ያነገበ ሁሉ አሳሪ፣ ፈራጅና ገዳይ ሲሆን፣ ከደርግ "ልዩ" ሶሻሊዝም ውጪ ያለ አመለካከት የሚያስገድል ሲሆንበት ለውጥ ተብሎ በንጉሡ ዘመን እንኳ ያላጣቸው መብቶች ሲያጣ ለውጡ ነውጥ ሆኖበታል።

ኢትዩጵያ ለውጥ ያስፈልጋት እንደነበር የሚያነጋግር፣ የሚያከራክር አይደለም። እንኳንና ኢትዮጵያ የልማት ተራራ ጫፍ ላይ የደረሱት እነ አሜሪካና ጃፓንም ቢሆን ለውጥ ያስፈልጋቸዋል። የለውጥ ጣርያ የለውም። ገደቡ ሰማየ ሰማያት ነው። ባለው መርካትና መርጋት የእንስሳት እንጂ የሰው ፍጡር ባህርይ አይደለም። ኢህአዲግ ስልጣን ላይ ከተቀመጠበት አመት ጀምሮ በሦስት አስርት አመታት ውስጥ በኢኮኖሚው፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማት፣ በውጭ ግንኙነት፣ በወታደራዊ ዝግጁነት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ እኩያ የሌላቸው ስራዎችን አከናውኗል። ይህ በእንዲህ እያለ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ድረስ ያሉት ሃላፊዎችና ባለሙያዎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሲፈፅሙ የኖሩት የመልካም አስተዳደር ግድፈት እጅግ የሚያስመርርና ተስፋ የሚያስቆርጥ ከመሆኑ የተነሳ ህዝቡ በኢህአዴግ የተከናወኑ መልካም ሥራዎችን ለያደንቅ የሚችልበት የቀረ ትእግስት አልነበረውም። አንድ መንግስት በራሱ ህልውና ላይ ሊፈፅም የሚችለው የከፋ ሥራ ቢኖር በአንድ በኩል መልካም ሥራ እየሠራ በሌላ በኩል የሠራውን መልካም ሥራ ጥላሸት የሚያለብስ ድርጊት ሲሰራ ነው። በመልካም አስተዳደር በኩል ለተፈጠረው ችግር ማወፈርያ ሆኖ ገደብ የለሽ ሙስና ሲንስራፋ ህዝቡ የተሰማው ስሜት "ለካ ይህ ሁሉ ልማት ሲባል የነበረው ለራሳቸው ለመዝረፍያ ያዘጋጁት እንጂ ለህዝብ አልነበረም" የሚል ሆነ። ለዚህ የህዝብ አመለካከት ተጠያቂ ኢህአዴግ ራሱ እንጂ ህዝቡ አይደለም። የሠራው መልካም ሥራ የሚያኮስስ ነገር እንዳይፈጠር መጠንቀቅ የነበረበት ራሱ ኢህአዴግ ነው። የመንግስታት ትልቁ ችግራቸው እነሱ የሚሠሩት ሁል ጊዜ ትክክል ህዝቡ የሚያስበውና የሚናገረው ሁሉ ሁልጊዜ አጉል ትችትና ማማረር አድርገው ይወስዳሉ። ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም የኢትዮጵያ ህዝብን "ወርቅ ቢያነጥፉለት ፋንድያ ነው ይላል" ብለው ያዋረዱበት ንግግራቸው የሚያመለክተው የኢትዮጵያ መሪዎች ራሳቸውን ከህዝቡ በላይ አድርገው በማየት ህዝብ የመናቅ አባዜ የተጠናወታቸው መሆናቸው ነው። የሚታወቀው እውነታ ደርግ ባሩድና ቀለሃ እንጂ ወርቅ እንዳላነጠፈ ነው። አንዳንዴም የፈለገ ጥሩ ነገር ቢሠራ የማይዋጥላቸው ተቃዋሚዎች የሚተቹትና ህብረተሰቡ የሚያቀርበውን ትክክለኛ አቤቱታ አደበላልቆ በማየት እውነታውን ለይቶ መፍትሄ ከመስጠት ሲቆጠቡ የህዝቡን ምሬት ያባብሱታል። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የፈለፈለው አመፅ ሁሉንም የኢህአዴግ አባላት ደጋጎችንም ጨምሮ የመልካም አስተዳደር ችግር የፈጠሩ ወንጀለኞ አደረገ፤ እንዲሁም ሙሰኞችን በሙሉ ከትግራይ ክልል ብቻ አድርጎ ሲያበቃ ሌሎች የኢህአዲግ አባላትና አመራሮችን እንደ ጲላጦስ አድርጎ ፈረጀ። የአሁኑን ለውጥ ያነሳሱ ምክንያቶች እጅግ የተለያዩ ነበሩ።
የአዲስ አበባ ዙርያ ያለው የኦሮሞ ገበሬ ያለ በቂ ካሳ ከመሬቱና ከኑሮው ሊፈናቀል ነው የሚል ኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆኑ ማንም ለፍትህ የቆመ ዜጋ የሚቃወመው ጉዳይ፣ ስለ ኢኮኖሚ ፍትህ ሳይሆን አዲስ አበባ ስትስፋፋ በዙሪያዋ ያለው የኦሮሞ ባህልና ቋንቋ ይጠፋል የሚል ጭንቀት፣ ኢትዮጵያን ከሰሜን የመጣ አናሳ (ጥሩ ይሁን መጥፎ በማያስጨንቅ) ከሚያስተዳድራት ኦሮሞና አማራ አንድ ላይ ቢሆኑ የህዝቡ ከግማሽ በላይ ስለሚሆን ኢትዮጵያን በጋራ ያስተዳድራሉ የሚል የሌሎች ክልሎችን ህዝቦች ከመጤፍ የቆጠረና የአለምን የዲሞክራስያዊ ምርጫ መርሆዎችን በማናለብኝነት የረገጠ አስተሳሰብ ያለ ይሉኝታ በመራገቡ፤ የመልካም አስተዳደርና የወጣቶች እስከፊ የስራ አጥነት እንዲሁም ሙስና የመሳሰሉ የከባበዱ ችግሮች መባባሳቸው፤ ተናገርክ ወይም ፃፍክ የተባለውም ነፍጥ ያነሳውም እኩል ለእስር የሚዳረጉበትና ሰው በሰላማዊ መንገድ መታገሉ ይበል የማያሰኝ እየሆነበት አገር ለቆ ሄዶ መንግስት በማንኛውም መንገድ ይሁን እንዲቀየር ቀን ከሌሊት እንዲታገል መገደዱ፤ እንዲያው ህወሓት/ኢህአዴግን እንደመልአክ ቢሰራቸውና ለሰው የተመቹ ቢሆኑም እንኳን እንዲሁ ጭፍን ጥላቻ ያደረባቸው ሰዎች በርካታ በመሆናቸው፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ ህወሓት/ኢህአዴግ ዘረኝነት አስተማረው የሚል ህዝብን እንደጨቅላ ህፃን የሚቆጥር ግን ይህንን ዘረኝነት በተባባሰ ዘረኝነት የሚታገሉ፣ "እሾህን በእሾህ" የሚለውን ዘዴ አለ ሰገባው ፓለቲካ ትግል ውስጥ አስገብተው የተደራጁ ሃይሎች በመጠናከራቸው፤ ወረዳው ዞን ይሁን፣ ዞኑም ክልል ይሁን የሚሉ እንቅስቃሴዎች ሃይል የተቀላቀለበት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑ፤ ኑሮ እየተወደደ በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ህዝቦች ከፍፁም ድህነት መስመር በታች ሲወርዱ ብራቸውን የት እንደሚያጠፉት ግራ የገባቸው ባለፀጎች እየበዙ የማህበረ-ኢኮኖሚው ሚዛኑ ስለተቃወሰ፤ ባንድ በኩል ህገመንግስቱንና እሱን መሠረት አድርገው  የተከናወኑትን  ሁሉ አንቀበልም መሻር አለበት በሚል የመረረ ትግል እያካሄዱ በሌላ በኩል የማንነት ጥያቄ በህገ መንግስቱ መሠረት ይፈታ እያሉ የሚጠይቁ ቡድኖች በመኖራቸው መልስ ሰጪው ከተቃራኒዎቹ ጥያቄዎች ለየትኛው መልስ እንደሚሰጥ በመቸገሩ ቡድኖቹ ፍትሁን ወደ ገዛ እጃቸው በማዛወራቸው፤ ሌሎችም... ለዘመናት ስር ሰዶ የቆየውን ዘውዳዊውን ሥርአት ታሪክ ያደረገው የየካቲት  እንቅስቃሴ እጅግ ሰላማዊ ነበር። በተማሪዎች በሙስሊሞች፣ በመምህራን፣ በወዛደሮች/ላባደሮች ለሳምንታት ሲካሄድ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ እውነትም እንደስያሜው ሰላማዊ ነበር። ህንፃ አልተቃጠለ፣ ሰዎች አልተደበደቡ አልተገደሉ፣ መንገድ አልተዘጋ አውቶቡስና ሌላ መኪና አልተለኮስ። ይህ ማለት ግን ህዝቡ የነበረበት ብሶት አነስተኛ ስለነበረ አይደለም። ህዝቡ፣ ወታደሩ ኑሮው ምስቅልቅል ብሎበት ውስጡ እየተቃጠለ ነበር። ይህ ንዴቱን ግን ንብረት በማጥፋት፣ ሰው በመግደልና በማፈናቀል ሊወጣው ጨዋነቱ ከቶ አልፈቀደለትም።
 ምንጊዜም ቢሆን የህብረተሰብን ብሶት አደባባይ የሚያወጣው ወጣቱ ትውልድ ነው። በቄሮዎች፣ በፋኖዎችና በዘርማዎች የተጀመረው ትግል ከዚህ አኳያ ማየት ይቻላል። ሆኖም ግን እነዚህ የወጣት ቡድኖች የተነሱበት ስርአት የመቀየር አላማና ስርአቱ እንዲቀየር የተጠቀሙበት ዘዴ የሚናበብ አልነበረም። አንደኛ ሥርአቱ ኢህአዲግ የሚመራው እንደመሆኑ የእውነት ሊቀየር ከሆነ የሚቀየረው ባጠቃላይ የአራቱም አባል ድርጅቶች አመራር ነው። በየትም አለም የስሥርአት ለውጥ የሥርአቱን መሪዎች በከፊል በማስወገድ ብቻ እውን ሊሆን አይችልም። ሥርአቱ በስብሶ ከሆነ እንደሙዝ እየመረጡ አይበላም። የሥርአት ቲዮሪ የሚያስተምረን ነገር ቢኖር አንድ የ ማንኛውም ሥርአት አንዱ አካል ተበላሸ ከተባለ ቀሪዎቹ አካላት ጤነኛ ሊሆኑ አይችሉም።
በኢትዮጵያ ውስጥ ሲካሄድ የቆየው "የሥርአት ለውጥ" አንዱ የስርአቱ አካል ላይ ቀሪዎቹ የሥርአት አካላት ጥቃት እያደረሱ ነው። ይህ ከተፈጥሮ ሳይንስ ህግ ጋር የሚገናኝ አይደለም። የወጣቶቹ የስሥርአት ለውጥ ጥያቄ በመጥለፍ የውስጠ ፓርቲ ሽኩቻ መሣሪያ ሆኖ ተቀለበሰ። ጥያቄያቸው ተቀለበሰ አልተቀለበሰ ሲከተሉ የነበሩት የትግል ስልት ግን የህግ የበላይነት የሻረ፣ የግለሰብን የትም የመኖርና የመሥራት ሰብአዊና ሲቢላዊ መብትን የገፈፈ፣ የህዝብና የመንግስትን ሃብትና ንብረት በማናለብኝነት ያወደመ ነበር። ሲወድምና ሲዘረፍ የነበረው የለፍቶ አዳሪ እንጂ የመንግስት ሃላፊዎች ንብረት አልነበረም። ሲገደል፣ ሲቆስልና ሲሰደድ የነበረውም ሥርአቱ ተለወጠ አልተለወጠ እንደድመት "ያው በገሌ" ብሎ የሚኖር ህዝብ ነው። ይህ ከሥርአት ለውጥ ጥያቄው ጋር አራምባና ቆቦ ነው። የሥርአት ለውጥ ጥያቄ የቀሰቀሰው ዋነኛ ጉዳይ የህግ የበላይነት ይስፈን፣ ሥርአቱ በግለሰቦች የግል ጥቅም ፍላጎትና የስልጣን ጥም እንጂ እየተመራ ያለው በህግና ሥርአት አይደለም ተብሎ እንደነበር እናስታውሳለን፤ እንደ "አኒማል ፋርም" ታሪክ አላማዎቹ ሌሊት ሲቀየሩ አድረው ካልሆነ። የህግ የበላይነት ይስፈን ብሎ ህይወቱን ለጥይት እየሰጠ ያለ ወጣት ያለችውንም የህግ የበላይነት እንጥፍጣፊ ካደረቃት "I got lost" እላለሁ።
 ይህ ሁሉ ሲሆን በኢህአዲግ አባል ፓርቲዎች ዘንድ በወጣቶቹ የትግል ስልት ህጋዊነት ላይ ስምምነት  አልነበረም። ከአራቱ ሦስቱ አባል ድርጅቶች የወጣቶቹን ድርጊት እንደ ታላቅ ጀብድ እያሞገሱ ትግሉ የሥርአት ለውጥ ሳይሆን አንዱን አባል ድርጅት የማዳከም ሂደት እንደሆነ የሚያስመስለው መልክ ያዘ። ከዛ በኋላ "ጂኒው ከጠርሙሱ ወጣ"። በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙና የህጋዊ ሥርአት መፍረስ እንደጥሩ አጋጣሚ የቆጠሩ ሃይሎች አገሪቱ አይታው ወደማታውቀው ትርምስ ውስጥ አስገቧት። ተመሳሳይ ጥፋት ሲፈፀም አንዱ ጀግና ካልክ በኋላ ሌላውን ወንጀለኛ ማለት ከባድ ነው። ሁሉንም አካፋዎች አካፋዎች የማለት ድፍረት አጥተን አንዳንዱን አካፋ ዶማ ነህ ብለን ብናቆላምጠው አካፋ ሁሉ ዶማ መባል ስለሚፈልግ ህግና ስርአት የምናሰፍንበትን መላው ይጠፋብናል። አገርም የህገወጦች መፈንጫ ትሆናለች። የተፈቀደ በሚመስል ውንብድና ታላቅዋ የሃረር ከተማ ውሃ ሲዘጋባት ከማየት የከፋ የህጋዊ ሥርአት መፍረስ አለን?  አንድ የኦሮሞ ትውልድ ያላቸው የልብ ወዳጄ የነበሩ (አፈሩ ይቅለላቸው
) ፕሮፌሰር የተሰማቸውን ስሜት በአንክሮ አጫወቱኝ፣እንዲህም አሉ፦ "የትግራይ ህዝብ ምን ነካው? ጥሩ ክርስትያን ህዝብ አልነበረም እንዴ? ይህ ሁሉ ሌብነት ምንድነው?" እኔም ሳይፈሩኝ አቅርበው የልባቸው መናገራቸው የበለጠ አከበርኳቸው። ለጥያቄው ግን መልስ አልሰጠሁም። ለዚህ ምን ተብሎ መልስ ይሰጣል? ሆን ተብሎ እየተስፋፋ ያለውን ህዝብን አዋርዶ ወደታች የመድፈቅ የተቀነባበረ ዘመቻን የአምላክ ድጋፍ ካልተጨመረበት በስተቀር ምን ያደርጉታል።
 ይህን የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች መግበያ በር በሆነው ህዝብ ላይ የነዚህ ሃይማኖቶች ተከታዮች የሆኑ ሰዎች እንደማርያም ጠላት ቆጥረው ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን እስኪጠራጠር ድረስ እየደረሰበት ያለው ውርጅብኝ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ፈፅሞ ያልታየ ነው። "ምንም የለህም ዋጋ የለህም፣ ብትፈልግ ተገንጠል የትም አትደርስም፣ ከኛ ብር ሳታገኝ መኖር አትችልም" እየተባለ አንጋፋ ኢትዮጵያዊ የሆነውን ህዝብ ማራከስ እስከመቼ "ህጋዊ" ሆኖ እንደሚቀጥል እንቆቅልሽ ነው። ስልጣን ላይ ያለው መንግስትም ህዝብ ያህል ክቡር ነገር "ሌባ ሌባ" ሲባል ሃላፊነቱን አውቆ ሥርአት እንደማስያዝ ዝምታን የመረጠበት ምስጢሩ ግልፅ አይደለም። ዝምታ አለመጨነቅ ከመሆን አልፎ ድርጊቶቹን የመደገፍ መልእክትም ሊያስተላልፍ ይችላል። በዲሞክራሲው አለም የህዝብ ክብር የሚጠበቀው ወይንም የማይጠበቀው በቁጥሩ መብዛትና ማነስ አይደለም። አንድም ሰው ቢሆን እንዲከበር የማድረግ የመንግስት ሃላፊነት ነው። ህዝብ በሙሉ ሌባ ሊሆን አይችልም፤ ሌባ የሌለበት ህዝብ ግን  የለም። ሌብነት የግለሰብ ህገወጥነት እንጂ የህዝብ ጉዳይ አይደለም። ሌብነት እንኳና የህዝብ የድርጅት አላማም ሊሆን አይችልም፤ ከአሊባባና አርባ ጭፍሮቹ በስተቀር።
ሙስናን ለማጥፋት የሚደርግን ቅን ዘመቻ የማይደግፍ ጤነኛ ሰው ሊኖር አይችልም። ያለፋህበትን መውሰድ ማንንም ህብረተሰብ የሚቀበለው አይደለም። ስለዚህ አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሙሰኞችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ የሚበረታታ ተግባር ነው። ሆኖም እየታየ ያለው ሁኔታ ስክነት የጎደለው ስሜታዊነት የገዛው ነው። በዚች አገር ስርቆት ታይቶ የማይታወቅና አንድ የተወሰነ ህዝብ በኢትዮጵያ ላይ ያወረደው መአት እየመሰለ ነው። የቴሌቪዥን ቻናሎች በሙሉ ማለት ይቻላል የአየር ጊዜአቸውን እየበላ ያለው የሙስናውና የእስሩ ጉዳይ ነው።  ለመንግስት እኮ ሙሰኞችን ማሰር ከበርካታ ስራዎቹ አንዱ ብቻ ነው። አገሪቱ ጦርነት የታወጀባት ያህል በጥቂት ግለሰብ ሙሰኞች መታስር ወይንም አለመታሰር መተራመስ የለባትም። አንድ ሰው በእንቁላል ስርቆት  ወይንም ሰክሮ ሰው የደበደበ ይሁን በመርከብ ስርቆት ወይም በሰብአዊ መብት ረገጣ ተጠርጥሮ ሲታሰር ፓአ ፖ ሊስና ፍርድ ቤት በማስረጃ እስኪያረጋግጡ ድረስ ታሳሪው የንፁህነት ሰብእናው በህግ የተጠበቀ ነው። ማስረጃ ያለው ሰውም ፍርድ ቤት በምስክርነት ቀርቦ፣ ቃለ መሃላ ፈፅሞ ይመሰክራል እንጂ በየቴሌቪዥን ስቱድዮው እየተጋበዘ በፍርድ ቤት የተያዘውን ጉዳይ በቴቪዥን ስቱድዮ ሌላ መደበኛ ያልሆነ ፍርድ ቤት አይፈጥርም። አሜሪካውያን የህግ ሰዎች እንዲህ አይነቱን ድርጊት "obstruction of justice" (የፍትህን ሥራ ማደናቀፍ) ይሉታል። ቸር ያሰራን፣ቸር ያሰማን።

AP ( አ ፖ) ተጨማሪ :
አሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ የተከሰተው ጉዳይ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከት ነው :: ትግራይ ኢትዮጵያውያን ብቻ የሚመለከት አይደለም :: የኤርትራ ገዥ ፓርቲ የትግራይን ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብህረሰቦች ለመለየትና ለማጥቃት እየሞከረ ነው:; ይሁንና  ሱማሌ አፋር: ጋምቤላና ቤ ን ሻንጉልም በአዲስ አመራሮች በመተካትና አስፈላጊም ሲሆን በሙስና በሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል ማሰር ተጀመሮአል:; የተባለው ለዉጥ ኢህአዴግን አንደ ድርጅት ለመናድና ለማፍ ረስ ያትኮረ ነ ው :: "ተሃድሶ" ወይንም reform ሳይሆን ድረጁትን ጨርሶ ለማፈርስና ለማገድ ያለመ አንቅስቃሴ አየተደረገ ነው :: አቶ አብይ አህመድ በተቃዋሚው ኃይሎች አይተዘውሩ ነው:: አሁን የተፈጥረው ሁኔታ ለግብፅ ይጠቅማል :: ግብፅ የአባይን ግድብ ብቻ መገንባት አይደለም የምትቃወመው:: የኢትዮጵያ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ልዕልነት አንዲኖር አትፈልግም :: ነገሩ የተወሳሰበ ነው :: የኢትዮጵያ ሊህቃን ስለጉዳዩ አንድ አይነት አቆአም እንዲኖራቸው አስፈላጊ ነው :: የደርግ ርዝራዞች አንደ ጥሩ ዜጋና ጀግኖች የሚታዩበት ሁኔታ ተፈጥሮአል:: በተቃራኒው ወያኔዎችና ሌሎች ዲሞክራሳዉያን  ኃይሎች በተለይ በበሄረሰብ የተደራጁ አንደጠላት የሚታዩበት ሁኔታ ነው ያለው:: ይህን በምንም መንገድ መፈቀድ የለብንም :: በወያኔ ይሁን በኢህአዴግ አመራር ስህተት አልተፈፀመም ማለት አይደለም:: ይሁንና አነዚህ ስህተቶች በውሳጣዊ አስራርር ልታረሙይገባል :: ይህም እንደ  የቻይና ኮሙንስት ፓርቲ ማ ለት ነው :: አሁን ግን ሌላ አብዮት አየተካሄደ ያለ ይመስላል ::

No comments: