Thursday 20 December 2018

የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ መንግስት እና የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት፤ ፀረ -ትግራይ ህዝብ መሆናቸውን ያረጋገጠ አዋጅ አፀደቁ

ከህዳሴ ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ህዝቦች ከእናውቅልሀለን፣ እኛ ላንተ የሚጠቅም ጠንቅቀን እናውቃለን፣ አንተ አታውቅም አርፈህ ተቀመጥ ከሚሉ ገዢዎች ከተላቀቀ ድፍን 27 ዓመታት አልፈዋል፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ህዝብን ባሳተፈና ህዝብን አስተያየት እየሰጠበት በርካታ ህጎች ሲወጡ የነበሩ ሲሆን በልማቱ ዙርያም ካለ ህዝብ ተሳትፎ አንድ እርምጃ መራመድ አይቻልም በሚል እምነት የህዝቡ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መጥቷል፡፡ 

ባለፉት 27 የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዓመታት፣ በሚደረገው የህዝብ ተሳትፎ ላይ የህዝብ ተቃውሞ ባጋጠማቸው ጉዳዮች ላይ አንድም ህግ እንደ ህግ ፀድቆ አያውቅም፡፡ ለህዝብ የሚጠቅም መሆኑ በኢህአዴግ ከፍተኛ እምነት የተጣለበት ጉዳይ ቢሆንም የህዝብ ድጋፍ ከሌለው ቀርቦ እንደ ህግ ሊፀድቅ ቀርቶ ወደ አፅዳቂው የመንግስት ኣካል /ወደ ተወካዮች ምክርቤት/ አይቀርብም፡፡ አንድን ህዝባዊ ወገንተኝነት የተላበሰ ሀይል ስለ ህዝብ መስዋእት ለመክፈል ቆርጦ የወጣ ድርጅት ህዝባዊ ዓላማው ህዝብን በማሳመን እንጂ በማስገደድ አይፈፅምም፡፡ ይህ ሲባል ባለፉት 27 ዓመታት የሚወጡ ህጎች እና የሚተገበሩ የልማት አጀንዳዎች ያለ አንዳች ተቃውሞ ይፈፀሙ ነበር ማለት አይደለም፡፡ ለህዝብ ሲቀርቡ ተቃውሞም ድጋፍም ድምፀ ተአቅቦም ነበሩ፡፡ ነገርግን ተቃውሞም ድምፀ ተአቅቦም ቢኖርም ህዝብ እንደ ህዝብ፣ ክልል እንደ ክልል ተቃውሞ የነበራቸው አንድም ህግ አልፀደቀም፡፡ ሁሉም የሚፀድቁት በአብላጫ ቢሆንም የአናሳ ህዝብ ድምፅ ያላገኙ ከሆኑ አይተገበሩም አይፀድቁም ነበር፡፡ ካጋጠመ በይደር በመታለፍ ሰፊ የማግባብያና የግንዛቤ ስራ ነበር የሚሰራው፡፡ እንዲህ አይነት አካሄድ በመሄድ ነበር ያለፉት 27 ዓመታት የሰላም፣ የመረጋጋት እና የልማት ዓመታት ሆነው ያለፉት፡፡

የኢህአዴግ የትግል ተሞክሮ የሚያሳየው አንድን የሚያማልል እና ህዝብን እንደህዝብ የሚጠቅም መሆኑ የሚታወቅ ተግባር ህዝብ ካልደገፈው ለህዝብ ተብሎ በፍፁም አይተገበርም፡፡ ለመተግበር የተንቀሳቀሰ አመራር በድርጅቱ ከፍተኛ ቅጣት ይወሰድበት ነበር፡፡ ምክንያቱ ያ ተግባር በህዝብ ላይ ችግር ስለሚፈጥር ኣይደለም፤ ተግባሩ በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ዋናው ምክንያቱ ህዝቡ ካላመነበት በምንም ተአምር መተግበር የሌለበት አንዱ የድርጅቱ እሴት በመሆኑ እንጂ፡፡ በልማት ተሞክሮ መሰረት በአንድ ቀበሌ የሚኖር ህዝብ ሳይቀበለው ቀርቶ በሌላ ቀበሌ የሚኖር ህዝብ የተቀበለው የልማት ስራ ሲኖር፤ የተቀበለው ህዝብ ወደ ትግበራ ሲገባ ያልተቀበለው ህዝብ ግን ወደ ትግበራ አይገባም፣ ባመነበት አሰራር ይቀጥላል፡፡ ያ ያልተቀበለው ቀበሌ በሌሎች ቀበሌዎች በመተግበራቸው ለውጥ አምጥተው ሲያይ ወድያውኑ በራሱ ጊዜ እንዲተገብር ጥያቄ ያቀርባል፡፡ በዚህ ጊዜ የሚፈለገው ለውጥ ያመጣል፡፡ በግድ ተግብር ካልነው ግን በቀን የሰራው በለሊት ያፈርሰዋል፣ በመንግስቱ ላይም ቅሬታ ይይዛል፡፡

ኢህአዴግ ይህን ትክክለኛ እሴት በመያዙ ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈለ ቢሆንም፣ አሁን ለደረስንበት ዕድገት የራሱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ ይህ እሴት እየተሸረሸረ ሲመጣም በህዝቦች ላይ ቅሬታ እየተፈጠረ መጥቷል፡፡ ለዚህ የአሁኑ ውድቀትም የበኩሉ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ የሚገርመው ነገር ግን ይህን እሴት እስካሁን ድረስ ይጣስ የነበረው በአመራር እና እንደ ግል ሲሆን አሁን ግን ይህ እሴት እንደ ድርጅት ሲጣስ ማየት ምንኛ ኢህአዴግ ከመርሆዎቹ እና እሴቶቹ ርቆ መሄዱ፣ በዝቅጠት ጎዳና መጓዙ ያሳያል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ እንደ ድርጅት እና እነደ ኮር አመራር የህገመንግስታችን ጠበቃ መሆኑ ያበቃለት እና እንደ ድርጅት ህገመንግስቱን የመጣስ እና የማፍረስ ጉዞ የተያያዘው መሆኑ ያሳያል፡፡ የዚህ እንደ ማረጋገጫነት ማቅረብ የፈለኩት ዛሬ (ታሕሳስ 10፣ 2011 ዓ.ም.) የፀደቀው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሸን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ይህ አዋጅ ኢ-ሕገ-መንግስታዊ ስለመሆኑና በተለይ በትግራይ ክልል ህዝብ በስፋት ቅሬታውን ሲያቀርብ እና ሲጠይቅ ሰንብቷል፡፡ በመገናኛ ብዙሀንም ሲሰራጭ ሰንብቷል፡፡ የትግራይ ህዝብ ይህን አስመልክቶ ያለውን ስጋት በሰላማዊ ሰልፍና በተለያዩ ሚድያዎች ግልፅ ሲያደርግ ወይም ሲያቀርብ፣ መንግስት ይህን ቅሬታ ወይም ስጋቱን ተመልክቶ ሰምቶ እንዲቀርፍለት እና እንዲያስወግድለት በማሰብ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ይህን ቅሬታ ማቅረቡ የታገለለትንና ከፍተኛ መስዋእት የከፈለለትን ህገመንግስት እንዳይጣስ ብሎም አገራችን ወዳልተፈለገ ችግር እንዳትገባ ካለው ስጋት ነው፡፡
ነገር ግን መንግስት ይህን የትግራይ ህዝብ ጥያቄ እንደ የህዝብ ጥያቄ ወስዶ መልስ ከመስጠት እና ግልፅ ከማድረግ ይልቅ በማናለብኝነት ስሜት በትእቢት በመወጠር የህዝቡን ድምፅ ወደ ጎን በመተው ህጉ በድምፀ ብልጫ እንዲፀድቅ አድርጓል፡፡

ህገመንግስታችን በደነገገው መሰረት ዴሞክራሲ ሲባል በስመ ቁጥር ብልጫ ይወሰን አይደለም የሚለው፣ እንደዛም እየተደረገ አልመጣም፡፡ ህገመንግሳታችን የሚለው የሁሉም ህዝቦች ድምፅ እኩል ይደመጣል፣ የሁሉም ህዝቦች መብት እኩል ይከበራል፡፡ አንድን ህዝብ ቁጥሩ በአስር ሚልዮን የሚቆጠር ይሁን በአስር ሺ የሚቆጠር ህዝብ እኩል መብት አለው፡፡

የትግራይ ህዝብ ለዚህ ህገመንግስት መከበር የከፈለው ዋጋ በቁጥሩ ልክ ሳይሆን ከዛበላይ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን በቁጥርህ አናሳ ነህ ተብሎ የማይፈልገው እና በህልውናው ከፍተኛ ስጋት የጣለበትን ኣዋጅ መፅደቁ ኢ-ህገመንግስታዊ ነው፡፡ አሁን እያየነው ያለው አካሄድ በፀረህዝቦች ህዝበኝነት አካሄድ የአንድን ህዝብ መብትና ፍላጎት በቁጥር ብዛት መጣስ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አደገኛ አካሄድ እና አገራችን ከጀመረችው የህዳሴ ጉዞ በማውጣት ወደ ድቅድቅ ጨለማ የሚወስድ መንገድ ማስገባት ነው፡፡ 

የዶ/ር አብይ አሕመድ መንግስት የትግራይን ህዝብ ስጋት ያስገባ ህግ እንዲፀድቅ ማድረጋቸው ለምን አስፈለገ ? እውነት ጠ/ሚ ለትግራይ ህዝብ ሰላም እና መረጋጋት በማሰባቸው ነው ? የትግራይ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ በነቂስ ወጥቶ ጥያቄውን በሰላማዊ ሰልፍ መልክ ጠይቆ እያለ ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ ይህን ችላ ማለታቸው ህዝብ አያውቅም፣ ለህዝብ የሚጠቅም እኔ ነኝ የማውቀው ማለታቸው ነው?

የፈለገው ምክንያት ይሰጠው ህዝባዊነት አያስብልም፣ ህዝባዊነት ለህዝብ የሚጠቅም ማሰብ እና መፈፀም ብቻ አይደለም ኣሳምኖ መስራትም ይጠይቃል፡፡ ቢያንስ ህዝቡን ከማሳመን እና ከማግባባት በፊት በማን አለብኝነት ስሜት፣ ህጉ ህዝብን እንደ ህዝብ እየተቃወመው በፓርላማ ማፅደቅ ፀረ ህዝብነት ነው፡፡ የአንድን ህዝብ መብት መርገጥ፣ የአንድን ህዝብ ጥያቄ ምላሽ መንፈግ ማለት የማንም ህዝብ መብት ኣያከብርም ማለት ነው፡፡
የትግራይ ህዝብ በፀደቀው ህግ ተቃውሞ ያነሳው ይህ ህግ የትግራይን ህዝብ ጥቅም ብቻ የሚነካ የሌላው ህዝብ ጥቅም ያማይነካ በመሆኑ ኣይደለም፡፡ የአንድን ህዝብ መብት የሚነካ ከሆነ የማንም ህዝብ መብት ማረጋገጥ ኣይችልም እና፡፡ ይህ ጥያቄ ለፌደራል ስርኣታችን አደጋ አለው ነው የተባለው፡፡ ለህገመንግስታችን አደጋ አለው ነው የተባለው፡፡ ይህ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማንሳት ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ ዶ/ር አብይ እያደረጉት ያለ ነገር የልጆች እቃ እቃ ጨዋታ፣ የእልህ ጨዋታ ነው፡፡ አገር በዚህ አይመራም፡፡ አገር በጥቂት ቡድን ፍላጎት ብቻ አይመራም፡፡ ኢትዮጵያ የብዙሀን አገር እንደመሆንዋ መጠን የብዙሀን ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ ነው መመራት ያለባት፡፡ የሁሉም ፍላጎት ማሟላት ባይቻል ወይም ቢቸግር እንኳ፣ የአንድን ህዝብ ቅሬታ የሚፈጥር ከሆነ የሌላው ጥቅም ቀርቶ ቅሬታን ማስወገድ ብልህነት እና አስተዋይነት ነው፡፡ የዶክተር አብዪ አካሄድ ግን ግራ ያጋባል፣ የትግራይን ህዝብ ጥያቄ ወደ ጎን በመተው ባልተሟላ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ውስጥ በአብላጫ ድምፅ እንዲፀድቅ ማድረጋቸው በትግራይ ህዝብ ላይ ያላቸው ንቀት ያሳያል፡፡

የተለያዩ እምነቶች እና ብሄር ብሄረሰቦች ያለባት አገር ህዝብን አንድ አድርጎ የመምራት ሀ፣ ሁ፣ መቻቻል ነው፡፡ መቻቻል ማለት ደግሞ ቢያንስ ቅሬታን ማስወገድ ነው፡፡ የዶ/ር አብይ አካሄድ ግን አንድን ህዝብ እንደ ህዝብ፣ አንድን ክልል እንደ ክልል በማግለል፣ ወደ ቅሬታ እንዲገባ በማድረግ ውሳኔዎችን በመወሰን እና ስጋቶችን እንዲበራከቱ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በማንም ተቀባይነት የለውም፡፡

የትግራይ ህዝብ በማስከፋት የኦሮሞ ህዝብ ማስደሰት ይቻላል፣ ወይም የትግራይ ህዝብ በማስከፋት የአማራ ህዝብ ማስደሰት ይቻላል የሚል ፈሊጥ ካላቸው፣ ዶክተሩ በጣም ተሳስቷል፡፡ የትግራይ ህዝብ ካስከፉ የኦሮሞ ህዝብም የአማራ ህዝብም ማስከፋታቸው አልገባቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች አንዱን በመከፋት ሌላውን አይደሰቱም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች አንዱ ተጎድቶ እኔ ከሚጠቀም ይቅርብኝ የሚል ህዝብ ነው፣ አንተ ቆይ እኔ ልሰዋ የሚል ህዝብ ነው፡፡ የዶክተር አብዪ መንግስት፣ የጥቂት ሊሂቃን ጠባቦች እና ትምክህተኞችን ቡድን እርካታ ለማግኘት ሲባል የትግራይ ህዝብ ስጋት የሚጨምር ህግ ማውጣታቸው ምንያክል ፀረ ህዝብ መሆኑ ያሳያል፡፡

በህገመንግስታችን መሰረት አንድን ህዝብ የተቃወመው ህግ ህግ መሆን አይችልም፡፡ ይህ ህግ ተግባራዊ ማድረግ ማለት ደግሞ የህዝብ ሀብት ማባከን ማለት ነው፤ የህዝብ ሀብት ለግል ስሜት ማርኪ ማዋል ማለት ነው፣ የህዝብ ሀብት ለግል ፖለቲካዊ ቁማር ማዋል ማለት ነው፣ በኣጠቃላይ የአገራችን አንድነት ስጋት ውስጥ መክተት ማለት ነው፡፡
የዶክተር አብዪ መንግስት ባፋጣኝ ይህን የትምክህት ባህሪ ካላስወገደ ኢትዮጵያ አንድ አድርጎ መምራት አይችልም፤ የትግራይ ህዝብ ጠላት የሆነ መንግስት የማንም ህዝብ ወዳጅ ሊሆን አይችልም፡፡ ህገመንግስት ማክበር ካልቻለ፣ በህግ የተሰጠው ስልጣን መጠቀም ኣይችልም ማለት ነው፡፡ ዶ/ር አብይ መንግስትን መምራት የሚችለው ህገመንግስቱን ሲያከብር ብቻ ነው፡፡ በምትፈልገው ጊዜ ህገመንግስት እያጣቀስክ መምራት፣ ለዓላማህ የማያሳካ ሆኖ ስታገኘው ደግሞ ህገመንግስት እየጣስክ አገርን መምራት አይቻልም፡፡

ዛሬ ታህሳስ 10፣ 2011 ዓ.ም. የፀደቀው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሸን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በመፅደቁ ምክንያት የፓርላማው እና የዶ/ር አብይ መንግስት ዴሞክራሲያዊነት ሳይሆን የሚያሳየው፤ አሁን ያለው መንግስት ምንኛ ኢ-ሕገ-መንግስታዊመሆኑና ህገመንግስቱም ለድብቅ እኩይ አላማ እየተጠቀመበት ያለ እንደሆነ፣ የትግራይ ህዝብ ድምፅ እንደ የውሻ ድምፅ በመቁጠር ደንታ ቢስነት ያሳያል፡፡ ስለዚህ በዚህ ውሳኔ ግልፅ የተደረገ ነገር ቢኖር የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት ፀረ-የትግራይ ህዝብ መሆኑ ያረጋገጠበት የፓርላማ ውሳኔ ነው፡፡ ፀረ-ትግራይ ህዝብ የሚንቀሳቀስ መንግስት ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የማንም ህዝብ ወገን መሆን የማይችል መንግስት ነው፡፡
አሁንም ህገመንግስት ይከበር !!!
የህዝብ ድምፅ ይሰማ !!!
ህገመንግስት ማክበር የማይችል ሀይል አገርን የመምራት ብቃት የለውም !!!
hidaseethiopia@yahoo.com ወይም hidaseethiopiaa@gmail.com

No comments: