Thursday 6 December 2018

ኢትዮጵያውያን ምሁራን ለዲሞክራሲ ግንባታ ያላቸው ሚና

ልኡል ገብረመድህን (ከአሜሪካ )

ሰብዕና ረቂቅ የሰው ልማት ውስጣዊ (Internal Essence) ጉልበት ነው ። ሰው ካሉት ረቂቃን ውስጣዊ ጉልበቶች አንዱና ዋናው  እውነተኛ  (Truthful ) ሆኖ መገኘት ነው ። እውነት በሁሉም የሚገኝ ግን ደግሞ ለሁሉም የራቀና ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ማሰብ በሚችሉ ሰብአውያን ልቦና ውሰጥ የሚኖር ታላቅ ሐይል (Force ) ነው ። እውነት የስብዕና የበኩር ልጅ ነው ። ሰዎች ዘላቂነት በሌለው የተወሳሰበ የአመለካከት አድማስ ( perception ) መንደር ሲከትሙ የጎደላቸው ለመፈተሽ በውጫዊ እይታቸው ይጋረዳሉ። እውነት  (Truth )አብዛኛው ጊዜ የሚገኘው ከምሁራን ሰፈር አልያም ከእምነት አባቶች አካባቢ እንደሚሆን የብዙ ሰዎች እምነት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ ። ይህ ሲባል ሌላው የማህበረሰብ አካል እውነት ይደብቅ ይሆናል እንጂ ይዋሻል የሚል አመለካከት በግሌ እምብዛም የለኝም ።ከእውነት ውጭ ሁሉም ከንቱ ነው ።

በእውነት የህይወት ምህዋር ውስጥ (Truth life cycle) ያልገባሰው የስብዕና መዛባት ( Wisdom crisis ) እንዳጋጠመው መገመት አይከብድም ። የስብዕና መዛባት ለማንኛውም ማህበረሰብ ጠቀሜታ የለውም ። በተለይ ያልተስተካከለ የምሁራን ሞያዊ መዛባት ትውልድ የሚበክል በሸታ ከመሆኑም በላይ የማህበረሰብ እድገት (Social development ) የመግታት አቅሙ የላቀ ነው ።ምሁራኖች ምሁራዊ አቅማቸው ከውስጣዊ ሰብዕናቸው ጋር ካልተዛመደ ለእውነት የሚያዳሉ የመሆን አቅማቸው ደካማ ይሆናል ።ምሁራኖች የአንድ አገር ቀዋሚ ጠንካራ ምሶሶዎች መሆናቸው የሚጠራጠር አካል ያለ አይመስለኝም ። የአንድ አገር ሁለንተናዊ  የለውጥ እንቅስቃሴ በፊት አውራሪነት የሚመሩት አገር በቀል ምሁራኖቻችን እንደሚሆኑ የብዙዎቻችን አተያይ እንደሚሆን ላፍታም  ቢሆን ጥርጥር የለኝም ።

ምሁራን እውነትን የመከተል ሞያዊ ሰብዕና እንዲያጎለብቱ የሚያስፈልግበት አንዱ አብይ ምክንያት የትውልድ አደራ ወይም ሀላፊነት ጫንቃቸው ላይ የቆመ መርህ (Social Ethic ) መሆኑ ብቻ ሳይሆን የዜግነት ግዴታቸውም ጭምር መሆኑ ነው ። ምሁራን በአንድም ይሁን በሌላ የተዛባና ኢዲሞክራሲያዊ ለሆነ ፖለቲካ መሳሪያ መሆን የሚጠበቅባቸው የቤት ሥራ አይመስለኝም ። ከምሁራን የሚጠበቀው የተዛባ አተያይና አመለካከት ማስተካከል እንዲሁም እንዳይዛባ መከላከል ይሆናል ። የአንድ አገር የኢኮኖሚ ለውጥ በዋናነት የምሁራን ግባት ሚናው ከፍ ያለ አንደሆነ በእርግጠኝነት መተንበይ ይቻላል ። ያለ ምሁራዊ አሰተዋጽኦ ያደረገ አገር አለም ላይ የለም ። ምሁራን የአንድ አገር ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ የብርሃን ጮራ ( Enlightenment ) ተምሳሌት ናቸው ። በአብዛኛው የማህበረሰብ ክፍልም ተቀባይነት ( Trustworthiness ) እንደሚኖራቸው ይታመናል ።

በኢትዮጵያ የምሁራን አሰተዋጽኦ መሰናክል የበዛበት ነው ። አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ወጥመድ ሰለባዎች ሆኖ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ ፖለቲካም ምሁራን ያማከለ ካለመሆኑ የተነሳ ምሁራን መር ፖለቲካ ተመስርቶ አያውቅም ። የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ባህሪና የኢትዮጵያ ምሁራን የሚጣጣሙበት አሰራር ሆነ አመራር አልነበረም ፣ ወይም አልዳበረም ።ከአብዮቱ ጀምሮ ከዛም በፊት ኢትዮጵያ ለምሁራን የምትመች አገር አልሆነችም ።በአብዮቱ ወቅት የመብትና ማህበራዊ ተጠቃሚነት አንዲሁም በዲሞክራሲ ዙሪያ ይተቹ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ፀረ አብዮተኞች በሚል ሰበብ የደርግ ስረአት ግፍና መከራ ደርሶባቸዋል ። ተገድለዋል ፣ ወህኒ ወርደዋል ፣ ለስደት ተዳርገዋል ። ኢትዮጵያን ምሁራን በዘመነ ኢህአዴግም በለስ አልቀናቸውም ።ምሁራዊ  ትምክህተኞች በሚል አሳፋሪ ምክንያትበርካታ የከፍተኛ ተቋም ምሁራን ከሥራ ምድባቸው በሀይል እንዲወገዱ ተደርጓል ። ይህ አሳዛኝና በዜጐች ህይወት እንደመቀለድ ይቆጠራል ።

በምሁራን የማይመራ ኢኮኖሚ ፣ማህበራዊ ፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ እድገቶችና ለውጦች በተለያዩ ችግሮች የተተበተቡ ከመሆናቸውም ባሻገር የማህበረሰብ የኢኮኖሚ እድገት ጠንቆች ናቸው ። ያለ ምሁራን እውነተኛና ቀጥተኛ ተሳትፎ የተረጋጋ ማህበረሰብ አይኖርም ። ማህበራዊ ግጭትና ያለመረጋጋትእንዲያቆጠቁጥ አንዱ ምክንያት የምሁራን ሰብዕና መጓደል ነው ። የፖለቲካ መሪዎች በውል አስረግጦ የሚያውቁት የሚቃወማቸውና የሚተቻቸዉ ምሁር ጣት መቀሰር ከቻሉም ማሰር እንጂ ተቀራርቦ የመስራት ባህል ይኖራቸዋል ብሎ ለመገመት ያስቸግራል ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምሁራን የሚቀጣ እንጂ የሚያሳትፍ ሆኖ አያውቅም ።ካሳተፈም ለፖለቲካ ስርአቱ የሚያጎበድዱ ወይም ምሁራዊ ሸብዕናቸው የለወጡ እንደሚሆኑ የሚያነጋግር ጉዳይ አይመስለኝም ። በነገራችን ላይ ምሁር የሆነ ሁሉ በፖለቲካ መሳተፍ የለበትም እያልኩ እንዳልሆነ ግምት ኦንዲሰጥልኝ ፍላጎቴ እንደሆነ እገልፃለሁ ።

በፖለቲካ ደርጅት የሚታቀፉ ምሁራን ከሞያዊ ሲቀጥልም ከተፈጥሮ ሰብዕናቸው ውጭየፖለቲካ አጎብዳጅ አይሆኑም ለማለት እንቅፋት ነው ። በርካታ ምሁራን የፖለቲካ ድርጅት ተሳታፊ በመሆን በርካታ አገራዊ ስህተቶች ሲፈፀሙ ማየትና መሰማት ለብዙዎቻችን አዲስ አይደለም ። በሌላ አኳኋን ደግሞ የስብዕና ሀይል የተላበሱ ምሁራን በቅንነት ህዝባቸውና አገራቸው ለመለወጥ የሚተጉ አይኖሩም ብሎ መደምደም የሚቻል አይሆንም ። አንደ ሞያ ባህሪ የሚጠበቅባቸው የዜግነት ግዴታቸው በአግባቡና በታማኝነት ሌትና ቀን የሚሰሩ እንዳሉ ሁሉ ፖለቲከኞች የሚያሳሰቱና የፖለቲካ ስህተት ተባባሪ ምሁራን በርካታ ናቸው ። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ፀረ ዲሞክራሲ አገሮች ፖለቲካው ምሁራን የማኮላሸት ሴራዎች ይሰራል ። በሰማ በል ፖለቲካ የሚመሩ አሻጥረኛ ፖለቲከኞች የምሁር አቅም እንዳላቸው በማስመሰል የህዝቡን ቀል ለመሳብ ሲሞክሩ ማየትም መስማትም የለመደ ነው ።

    በኢትዮጵያ ለሚነሱ መሠረታዊ የማህበረሰብ ውስብስብ ግጭቶችና ያለመረጋጋት አንዱ ምክንያት የኢትዮጵያውያን ምሁራን የበሰለ አገራዊ ተሳትፎ ባለማድረጋቸው የሚመዘዝ መከራ ነው ። ምሁራን ከእውነታው ውጭ የተሳሳቱ የመንግስት መረሃ ግብሮች ሲደግፉ ፣ ሲፈፀሙና ሲያስፈፅሙ ኖሯል ። ይህ አገራዊ ክህደት ነው። የመንግስት የተሳሳተ ፖሊሲ ተባባሪ መሆንና በቀጥታ ተሳታፊ መሆን ሰብዕና ከመሸጥ በላይ ነው ። የመንግስት የተሳሳተ ፖሊሲ ያለመቃወምም የስብዕና ክስረት (,Lose of integrity )ነው ። ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የሚሸመደመዱ ምሁራኖቻችን ሀላፊነት በተሞላበት አኳኋን ተግባራቸው ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ። ከእውነት ጋር መኖር ይኖርባቸዋል ።

   የምሁራን አብይ ተግባር የለውጥ አቅጣጫ ማሳየት ብሎም በተግባር ማከናወን ነው ። ምሁራን ከፖለቲካ አጎብዳጅነት ስፍራ መቀየር ይኖርባቸዋል ። በጥናት ምርምር የተደገፈ ሁለንተናዊ የአገር እድገት ማመንጨት ይኖርባቸዋል ። የዜግነት የሀሳብ ልዕልና እንዲጎለብት ፣ የማህበረሰብ ኑሮ እንዲሻሻል ፣ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት አገር እንዲኖር ፣ የዜግነት ስደት እንዲቀንስ ፣ አምርቶ አደር ምርታማነት እንዲጨምር ፣ ዲሞክራሲና ሰበአዊ መብት የህግ ዋስትና እንዲኖራቸው ፣ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን የምሁራን አሰተዋጽኦና ተሳትፎ ለነገ የሚቆይ ጉዳይ አይሆንም ።

ያለ ገለልተኛ ምሁራዊ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚመጣ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካ ለወጥ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም ። የማህበረሰብ አሜኔታ ያላገኘ ለውጥ አጥቢ ወይም መባቻ ላይ ይቆማል ። የአንድ አገር ሁሉም አቀፍ ለውጦች የሚያቆጠቁጡ የሁሉም ማህበረሰብ ተሳትፎ አንዲሁም የምሁራን ሞያዊ አገልግሎት ቅንጅት ሲፈጥሩ መሆኑ አያጠራጥርም ። ኢትዮጵያ በሃሳብ ነፃነት የሚሞግቱ በርካታ ምሁራን በዉል ያስፈልጋታል ። ኢትዮጵያዊያን ምሁራን የተዛቡ የፖለቲካ አቅጣጫዎች ሰለባ ከመሆን ባሻገር የአገራቸውና የህዝባቸው ሁለንተናዊ ጥቅም ላይ አትኩሮት እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ህዝብ የማያወላዳ አብይ ፍላጎት ነው ።ሞያዊ ሰብዕናቸው ለአገራቸው እድገት ፣ ለህዝባቸው አርአያነት ፣ ለትውልድ መልካምነት ፣ ለመንግስታቸው ረዳትነትን፣ እንዲሁም  ለተተኪው ትውልድ እውነትን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ። ከእውነት ጋር መኖርና ለእውነት መሰዋእትነት መክፈል መለማመድ ይኖርባቸዋል ። ኢትዮጵያቀጣፊና ሰብዕናቸው የሸጡ ምሁራን የምታስተናግድ አገር መሆን የለባትም ።
 
 

No comments: