Sunday 9 December 2018

ዘረኝነትን በጋራ እንታገል!!

ፍስሃ መረሳ  

አገሪቱን የማተራመስ ኣላማ ያነገበ  በስልጣን ላይ ያለው ጥገኛና የውጭ ቅጥረኛው ሃይል እነሆ በዚህ አንድ አመት ባልሞላ አጭር ጊዜ ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ ህዝቦች ከባድ መስዋእትነት የተገነባች አገር በጠራራ ፀሓይ ሲደመርሳትና ስርኣት ኣልባ ኣገር ሲያዳረጋት  በአይናችን እያየን ነው ፡፡ ይህ አገር የማፍረስ ስራ ማእከል ያደረገው አገሪቱ የቆመችባቸውን ዋና ዋና ምሰሶዎችን ማፍረስ እንደሆነና ከሁሉም በፊት ህገመንግስታዊ ስርአቱ እንዳይከበር በማድረግ ዜጎች ህገመንግስታዊ ዋስትና እንዳይኖራቸውና በማድረግ በማንኛውም ጊዜ በስልጣን ላይ ያለው ሃይል የፈለገውን ኣካል  እንዲያስር እንዲቀጣ እንዲፈታ ከስራ ገበታ እንዲያባርር በደቦ ፍርድ እሰከ መግደልና አካል መጉደል የሚደርስ ጥቃት በንፁሃን ዜጎች እንዲያደርስ የፈቀደ ስርኣት አልበኝነት የሰፈነበት አካሄድ እንዲሆን አድርጎታል  ፡፡

እስከአሁን በመጣነው አጭር ጉዞ እያየነው ያለው ነገር ከመነሻው ስልጣን ሲረከብ ጀምሮ ኢህአዴግ አሽባሪና ወንጀለኛ ድርጅት ነው በማለት ከዚህ በፊት በነበረ  አመራር በተለይ  የህወሓት የበላይነት ነበረ በሚል ውሃ የማይቛጥር ምንም መሰረት በሌለው የጥላቻ አካሄድ ሰፊ ዘመቻ በመክፈት እነሆ  በየትኛውም የመንግሥት የስልጣን እርከን የነበረ ነባሩ በተለይ የትግራይ ተወላጅ የሆነውን አመራር ወደ እስር ለማስገባት በማለም ለዚህ ምክንያት ሊሆን የሚችል የፈጠራ ክስ በመመስረት መበቀል የሚል በብአዴን የሚደገፍ ቲም ለማ በሚል የሚጠራ ነውጠኛ ብዱን  አዲስ ስልት  ተይዞ ለዚህ ማስፈፀሚያ የሚሆን አዲስ ድራማ ሲሰራ ቆይቶ እነሆ ለብዙ ወራት የተሰራ ዶክመንተሪ ፊልም  በፌዴራል ዓቃቤ ግጉ ባለፈው ቅርብ ጊዜ ይፋ ተደርጎ ሰምተናል ፡፡


 አንዱ የድራማው ገፀባህሪ የመንግሥት ሃብት የዘረፋ ሰብአዊ መብት የጣሱ ተይዘዋል ይላል የፈዴራል አቃቤ ህግ ሪፖርት መግለጫ ፡፡ ግን መንግሥት ለመሆኑ ወንጀሎች ለመያዝ የሚያስችል ቁርጠኝነት አለው የሚል ጥያቄ የሚነሳበት ሁኔታ ተፈጥራል ፡፡  ይህን ለማየት አንዳንድ ማሳያዎች ማንሳት ተገቢ ይሆናል ፡፡ ከሁሉም በፊት መንግሥት ማንኛውም ህግ ጥሶ የዜጎች ሰብዓዊ መብት የጣሰና  የህዝብ ሃብት የዘረፈ ለመቆጣጠር ፍላጎት ካለው ለምንድነው ነው በቢልዮን የሚገመት ሃብት መንግሥና ህዝብ  እንዲያጣ ያደረጉ ከዚህም በፊት በቁጥጥር ስር የዋሉት የጉምሩክ ባለስልጣናትን እንዲያውም ጉዳያቸው ተጣርቶ እያለ ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲፈቱ የተደረገው ? የሜቴክና የጉምሩክ ባለሥልጣናት ሁሉም ኢትዮጵያውያን አይደሉም እንዴ ? የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ተፈልጎ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም የድሃው ህዝብ ሃብትና ንብረት ያባከኑ አይደሉም እንዴ? እንድያውም የበፊቶቹ በፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኛ ተብለው እያሉ ህገመንግስታዊ ስርአቱ በማይፈቅደው መንገድ የተለቀቁት ለምን ይሆን ? እኔ አልነበርኩበትም እና ከኔ በፊት የነበረ ሁሉ ስራ ቆሻሻ ነውና ህዝብና መንግሥት ቢጎዱም እኔ አያገባኝም ካልተባለ በስተቀር ትናንት ሌቦችና በአገር ክህደት የሚጠየቁ ወንጀለኞች ምህረት ብሎ የለቀቀ መንግሥት አሁን ፀረ ሌቦች ተነስቻለሁ ቢለን በየትኛው መመዘኛ ነው ዘርን ለይቶ ለማጥቃት ካልሆነ በስተቀር ይህ ውሳኔ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው ?
ሌላው  እየተነገረን ያለው ኣዲሱ ፋሽን በሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚጠየቁ ስላሉ በቁጥጥር አውለናል ይላል መግለጫው ፡፡ በዚህ በኩልም የተሰራው ድራማ በጣም አስቂኝ የሆነና ማንም በቀላሉ ሊረዳው የሚችል ህግ የጣሰ የበቀል እርምጃ መሆኑ ግልፅ ነው ፡፡ ለማሰር የተፈለጉ ሰዎችን ለመያዝና ይዞ ለማጥቃት ስለተፈለገ እንጂ ስንት ወንጀለኞች የዜጎች ሂወት ያጠፉ በዘረኝነትና በጥላቻነት ህዝብን አነሳስቶው ሆን ብሎው ህዝብ ከህዝብ እንዲጋጭ ያደረጉ የህዝብና የመንግሥት ሃብት ያወደሙ ፋብሪካ ሳይቀር ያቃጠሉ ግለሰቦች ለአመታት ሰርተው ያመጡትን ሃብት በእሳት እንዲቃጠል ያደረጉ እንዲያውም በሰብኣዊ መብት መርማሪ ኮምሽን ተጣርቶ ለህዝብ ጥፋታቸው ይፋ የሆነ በህግ እንዲጠየቁ የተለዩ ለአብነት የአማራ ክልል መንግሥት ባለሥልጣናት በቅማንትና በትግራይ ተወላጆች በፈፀሙት የዘር ማጥፋት ስራ እንዲጠየቁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ተላልፎ እያለ ከነዚህ በላይ ማን ሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅሞ ነው አሁን በቁጥጥር አውለናል እየተባለ ያለው ? ቂም በቀል ለመወጣትና የሻዕብያ መንግስት ፍላጎት ለማàላት መሆኑ የማይገባው ይኖር ይሆን ፡፡
 በአሁኑ ሰአት በየአካባቢው ዜጎች ያለ ፍርድ በጠራራ ፀሃይ በአደባባይ እንደእንስሳ ታርደው በሚገደሉበት አገር በአስከፊና ዘግናኝ መንገድ ያለ ጥፋታቸው በደቦ ፍርድ በድንጋይ ተደብድበው ዜጎች እየተገደሉ ባሉበት ሁኔታ እነዚህ ወንጀሎች ተቆጣጥሮ ህግ ፊት ማቅረብ ያልቻለ መንግሥት ማንን ለማታለል ታስቦ ነው አሁን ከአንገት በላይ በመጮህ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ መስሎ እየቀረበ ያለው ?  ሌላው እነዚህ የጥፋት ሃይሎች እየሰሩት  እየተከተሉት ያሉ የማደናገርያ ስልት ማንኛውም ዜጋ ሳናጣራ  ኣናስርም  የሚል ተራ ስብከት  ደጋግሞው ሲጠቀሙበት ይሰማል ፡፡ እስኪ በዚህ አጭር ጊዜ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕረዚዳንት የነበሩ ግለሰብ ጀምሮ ሌሎች ያለጥፈታቸው ዘራቸው ብቻ ተቆጥሮ ህገመንግስታዊ ስርአቱ በማፍርስ  የፀጥታ ሃይል በማሰማራት  ያለ ኣንዳች ማስረጃ እስር ቤት የገቡ እስከኣሁን ከኣምስት ወር በላይ ክስ ሳይቀርብባቸው  በቀጠሮ መከራቸውን እያዩ ያሉ ዜጎች ኢትዮጵያውያን አይደሉም እንዴ? ታድያ ማንን ለማታለል ይሆን ሳናጣራ አንይዝም የተባለው ? ህዝቡ ይህን መለየት አይችልም ብለው አስበው ይሆን ?
 ሌላው እየተሰራ ያለው ድራማ ሆን ተብሎ ዘርን በመለየት የተፈለጉትን ሰዎች ለማጥቃት አለማ ያደረገ መሆኑ አንዱ ማሳያ ሊሆን የሚችለው አሁን ተፈፅመዋል እየተባሉ ያሉ  የሰብኣዊ መብት ጥሰትና ኮራብሽን በስፋት እንደተፈፀሙ የሚታመን ከሆነ ማነው መጀመሪያ የሚጠየቀው የሚል መመለስ ተገቢ ይሆናል ፡፡ በርግጥ አሁን ነበሩ እየተባሉ ያሉ ችግሮች በተወሰነ ደረጃ እንደነበሩ የማይካድ ሃቅ ሆኖ ኢህአዴግ በሂወት እያለ ከአሁኑ የበለጠ ትግል ይደረግ እንደነበረ ማንም የማይክደው ሃቅ ነው ፡፡ በከፍተኛ አመራሩ በነበረው የአመራር ጉድለት ግና የሚፈለገው ውጤት ስላልመጣ መጨረሻውም እስከ የአመራር ለውጥ ማስከተሉ ይታወቃል ፡፡ እዚህ ላይ በተለይ ችግር ተፈጥሮባቸዋል እየተባሉ ያሉት የመንግስት መስርያ ቤቶች ሜቴክ የመረጃና የድህንነት ቢሮና ማረሚያ ቤቶች ከሆኑ እነዚ የመንግስት ተቛማት  በቀጥታ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በምክትላቸው የሚመሩ እንደነበሩ እየታወቀ የድሮው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅር ጥፋት ሰርተው ሊጠየቁ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሩ ሰርቷል ተብለው’’ ‘የጀግና መሪ ክብር ተሰጥቷቸው ኒሻን’ አልተሸለሙም እንዴ?

ሰለዚህ አሁን እየተሰራ ያለው ሴራ ለማንም ግልፅና ግልፅ ነው ፡፡ መነሻው በስልጣን ላይ ያለው ሃይል ሊያጠቃውና ሊበቀለው የሚፈልግን ሃይል አላማ በማድረግ ለዚህ የሚሆን ማስመሰያ ከዚህም ከዛም ተለቃቅሞ በዶክመንተሪ ፊልም ተሰርቶ ምንም ጥፋት በሌለባቸው ዜጎች እስር ቤት በማጎር የግል ፍላጎቱን ለማርካት መሆኑ ሂደቱን የተከታተለው ሁሉ ለመፍረድ የሚያቅተው አይሆንም ፡፡ ግን አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ቢኖር ይህ ዘረኛ ኣካሄድ በዚህ ከቀጠለ ውጤቱ የከፋ እንደሚሆንና ከዚህ የጥፋት መንገድም ማንም እንደማይጠቀም ታውቆ ይህ የጥፈት ሃይል የያዘውን አገር የማፍረስ ተግባር በኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል እንዲቆም ማድረግ የማንኛውም አገር ወዳድ ዜጋ ሃላፊነት ስለሆነ በጋራ ተከባብረን የምንኖርባት አገር እንድትቀጥል ዘረኝነትን በፅናትና በጋራ የምንታገልበት ጊዜው አሁን ነው  ፡፡     

No comments: